“ከእኛ የሚጠበቀው የያዝነውን ነገር ይዘን መሞት ነው” ይሁን እንደሻው

ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ዳግመኛ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት በሁለት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ይሁን እንደሻው ከትላንቱ ድል በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን አጋርቷል።

እስካሁን ለዋሊያዎቹ ብዙም የመጫወት እድል አላገኘህም። በተለይ ምርጥ አቋም ላይ በነበርክባቸው ወቅቶች ለብሔራዊ ቡድን አለመመረጥህ ስለ ፈጠረብህ ስሜት ንገረኝ?

ያው በወቅቱ የነበሩት አሰልጣኞች ለሚከተሉት የጨዋታ ታክቲክ እኔን ያልፈለጉኝ ይሆናል። ሆኖም ይህንን ጊዜ እጠብቀው ነበር። ፈጣሪ የፈቀደለት ተሳክቶልኝ ይህው ዳግም ወደ ለብሔራዊ ቡድን ለመጠራት ችያለው። ደግሞ መምጣትም ብቻ አይደለም የመጫወት እድሉን ስላገኘው የምፈልገውን ነገር እያደረኩ ነው። በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ነገር ማድረግ እፈልጋለው።

ከተከላካዮች ፊት ተሰልፈህ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ጥሩ ነገሮችን ሰርተሀል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጎልተህ ለመውጣትህ የተለየ ምስጢር አለ?

የተለየ ምስጢር የለም። በየትኛውም ቦታ ብጫወት ለእኔ ችግር የለብኝም። ሆኖም አሰልጣኙ በሚሰጠኝ ትዕዛዝ ተጫወት ባለኝ ቦታ እጫወታለው። በአጭርም፣ በረዥም ኳሶች መጠቀም በሚገባኝ ጊዜ የምችለውን ነገር ለማድረግ እታገላለው። ከምንም በላይ ግን አሰልጣኙ ሜዳ ላይ የሚሰጠኝ ነፃነት የበለጠ ብሔራዊ ቡድኑን እንድላመድ እና አቅሜን አውጥቼ እንድጫወት ረድቶኛል።

ከአንተ አጠገብ ኳስን በመቆጣጠር የተሻለ ክህሎት ያላቸው እንደነ ሽመልስ በቀለ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ሱራፌል ዳኛቸው ዓይነት ተጫዋቾች መኖራቸው የበለጠ ሚናህን እድትተገብር አግዞኛል ትላለህ?

አዎ በሚገባ! ብቻህን ኳስ ይዘህ የሚቀበልህ ሰው ከሌለ ትርጉም የለውም። ኳሱን የሚቀበሉህ እና የፈጠራ ክህሎታቸው የተሻሉ የሆኑ ተጫዋቾች አብረውህ ሲኖሩ ነፃነት ይሰማሀል፤ ነገሮችም ይቀሉሀል። እግርኳስ የቡድን ስራ ነው፤ ኳሶች የማይበላሹ ከሆነ በእግርህ ኳሶች እያንሸራሸርክ የሚቆይልህ ከሆነ እና ራሱን ነፃ አድርጎ የሚቀበል ተጫዋች ከጎንህ ካለ በራስ መተማመንህ እየጨመረ ይመጣል። ቡድናችን ውስጥ ኳስ እንዳይበላሽ ነው ለራሳችን ቃል የገባነው። ወደ ፊትም የሚበላሹ ኳሶችን እየቀነስን ከሄድን ኢትዮጵያውያን በምንታወቀው አጭር ኳስ መጫወት ከቻልን ውጤታማ እንሆናለን። አጠገቤ ያሉት ተጫዋቾች ደግሞ ለዚህ አጨዋወት አመቺ ናቸው። እነርሱ ከኔ ፊት ብዙ ነገር ስለሚያቀሉልኝ ይመስለኛል በጥሩ ብቃት ሁለቱን ጨዋታ እንድጫወት የረዳኝ።

ብዙ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ቀድሞ ጎል ከተቆጠረብን የመደናገጥ እና የመውረድ ነገር ይስተዋላል። ዛሬ (ትላንት) ግን ተረጋግታችሁ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጋቹ ጥረት አስገራሚ ነበር። ይሄ የስነ ልቦና ጥንካሬ ከየት የተገኘ ነው።

ሲጀመር ይህ ነገር በኮትዲቯር ጨዋታ ሳይሆን ማዳጋስጋር ላይም ነበር። ምክንያቱም ገብቶብን ኳስ መጠለዝ የሚባል ነገር አልነበረም። ከአሰልጣኙ የሚሰጠን ተልዕኮ አለ የያዝነውን ነገር ይዘን መሞት እና ባለን ነገር በሚያዋጣን አጨዋወት እስከ መጨረሻው ድረስ መቀጠል አለብን ብለን ስላመንን እንደምናገባ እርግጠኛ ነበርን። ምክንያቱም ሜዳችን ላይ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት እንኳን አላሰብንም። በእርግጠኝነት ለማሸነፍ ነው የገባነው፤ ይህን የምልህ ስላሸነፍን አይደለም። ቡድኑ ወስጥ እንደ ግዴታ ቆጥረነው ነው የገባነው። ከዚህ ሁለት ጨዋታ አራት ነጥብ ለመያዝ ነበር ዕቅዳችን ፈጣሪ አልፈቀደውም። በማዳጋስካር ተሸነፍን እዚህ ደግሞ በሜዳችን የሚደረግ ጨዋታ በመሆኑ ለማሸነፍ መግባት አለብን ብለን ሁላችንም ተማምነን እዚህ ነጥብ ካልቻልን በኋላ ለምናልመው ግብ መሳካት ችግር ስለሆነ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ መግባታችን ይመስለኛል ውጤታማ ያደረገን። እንዳየኸው የቡድን መንፈስ በሚረብሽ ሰዓት ነው ጎል የገባብን። ሆኖም ሁሉም ተጫዋች ማሸነፍን አልሞ ወደ ሜዳ መግባት፣ እርግጠኛ መሆኑ እና ከተሰጠን የአጨዋወት ሚና ሳንወጣ መቀጠላችን ጎሎችን እንድናገባ አስችሎናል።

ሜዳ ላይ ከኳስ ውጭ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እየተመለከትኩ ነበር። ስህተቶች ሲሰሩ የመምከር ጥሩ ነገሮች ሲደረጉ የማበረታታት ነገር አይብህ ነበር። በብሔራዊ ቡድኑ ሁለት ጨዋታ ሳይሆን ከቡድኑ ጋር አብረህ የቆየ ትመስል ነበር። ይህ ነገር አስገርሞኛል። እንዴት አመጣኸው ከቡድኑ ጋር ቶሎ መላመዱን?

ሲጀመር አብረውኝ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በሙሉ ለዚህ ነገር ፍቃደኛ ናቸው። ብትቆጣ እሺ ነው የሚሉት። ምክንያቱም ሁሉም ለአንድ ዓላማ ነው ወደ ሜዳ የገባው፤ ትንሽ ትልቅ የሚባል ነገር የለም። ይህ ነገር ደግሞ በጣም ተመችቶኝ ስለ ነበር። ለዛ ይመስለኛል ደፍሬ ይህን እንዳደርግ ያነሳሳኝ። ለብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ አዲስ ልሁን እንጂ ማ ምን ምን ኳሊቲ እንዳለው አውቃለው። አብረን በአንድ ሊግ ነው የምንጫወተው፣ ሁሉም ወጣት ተጫዋች ነው። ስለዚህ ተመሰጋግኖም ተወቃቅሶም ውጤት ለማምጣት ሁሉም አንድ መሆኑ ነው ይመስለኛል።

ከቀጣይ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ጉዞ እንዴት ይሆናል?

የወደፊቱን ፈጣሪ ነው የሚያቀው። ከእኛ የሚጠበቀው የያዝነውን ነገር ይዘን መሞት ነው። አሁንም ቢሆን ያሉት ጅማሮዎች ደስ ይላሉ። ማዳጋስካር ሜዳ ያደረግነው ጨዋታ ሜዳ አልመረጥንም፤ የያዝነውን ይዘን ነው የሄድነው። የተለየ ነገር አላደረግንም ሜዳችንም ላይ የያዝነውን አጨዋወት ነው ያስቀጠልነው። ለዚህም ነው በውጤታማ የሆነው። በቀጣይ ከፈጣሪ ጋር የተሻለ ነገር እናደርጋለን ብዬ አስባለው። ምክንያቱም ቡድኑ ውስጥ ያለው መንፈስ ደስ ይላል። ሁሉም ታሪክ ለመስራት ነው ራሱን እያዘጋጀ ያለው። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያለውን ግንዛቤ ኢትዮጵያ ጨዋታ ሲኖራት ዛሬ ትሸነፋለች የሚለውን አስተሳሰብ ሁሉ ይህ ቡድን ለመቀየር ነው ቁርጠኛ ሆነን እየሰራን የምንገኘው። ሜዳ ላይም ቁርጠኝነቱ፣ ተነሳሽነቱን አይተኸዋል። ስለዚህ የሚከብድ ነገር የለም። ኳስ ነው እግርኳስ የሚፈቅደውን ካደረግን፣ የራሳችንን መንገድ ይዘን ከተጓዝን ሁሉን ማድረግ እንችላለን ብዬ አስባለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ