ከፍተኛ ሊግ | ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስምንት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም አምስት ወጣቶችን አሳድጓል

የከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ተሳትፎው የስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የሦስት ነባሮችን ውል በማደስ አምስት ወጣቶችን አሳድጓል።

ከአዲስ ፈራሚዎቹ መካከል አጥቂው በረከት ይስሀቅ አንዱ ነው። የቀድሞው ሀዋሳ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች አምና በደቡብ ፖሊስ ቆይታ ያደረገ ሲሆን ከዚህ ቀደም መጫወት ወደ ቻለበት ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ዳግም ተመልሷል፡፡

ተከላካዩ እሸቱ መና የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞ የደደቢት ተስፋ ቡድን ተጫዋች በሀዋሳ እና አዳማ ከተማ መጫወት የቻለ ሲሆን በሁለት አጋጣሚዎች ደግሞ በወላይታ ድቻ የተሳኩ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ በክረምቱ የጦና ንቦቹን ከለቀቀ በኋላ ለደቡብ ፖሊስ ለመጫወት ከስምምነት የደረሰ ቢሆንም ሳይቀላቀል ቀርቶ ወደ አንዋር ያሲን ቡድን አምርቷል።

ከ2004 ጀምሮ ያለፉትን ሰባት አመታት በፋሲል ከነማ በቀኝ መስመር ተከላካይነት በመጫወት ያሳለፈው እና ዘንድሮ ከክለቡ ጋር የተለያየው ፍፁም ከበደ ሶስተኛው የክለቡ ፈራሚ ነው፡፡

ሌሎቸ ክለቡን በአዲስ መልክ የተቀላቀሉ ታምራት ዳኜ ግብ ጠባቂ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ ልደቱ ጌታቸው ተከላካይ ከአውስኮድ፣ ጅላሎ ከማል አማካይ ከጅማ አባቡና፣ ፃዲቅ ተማም ከለገጣፎ አጥቂ፣ ሀብታሙ ፈቀደ ከለገጣፎ አጥቂ ሲሆኑ በክለቡ ነባር የሆኑት አምበሉ አዲስ ነጋሽ ግብ ጠባቂው ዮሀንስ በዛብህ እና የቡድኑ የተስፋ ቡድን ፍሬ የሆነው አማካዩ ስንታየው ዋልጬ ለተጨማሪ ዓመት ውላቸውን አራዝመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከቢ ቡድኑ እና ከተስፋ ቡድኑ ፀጋ ደበሌ፣ አንዋር ሙራድ፣ ብስራት ታምሩ፣ አደም አባስ እና ሲሳይ ማስረሻ የተባሉት ወጣቶችን ማሳደግም ችሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ