አአ ከተማ ዋንጫ | ሰበታ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በአዲስ አበባ ከተማ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ በ9 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከሰበታ ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በመጀመሪያ ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ኤሌክትሪኮች ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል። ደቂቃዎች አየገፉ በሄዱ ቁጥር በሂደት ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ሰበታዎች በአንፃሩ ቀሪውን የመጀመሪያ 45 ደቂቃዎች በተሻለ ጫና በመፍጠር በርከት ያሉ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።

በአንድ ሁለት ቅብብል እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን በቀጥተኛ አጨዋወትን ምርጫቸው ያደረጉት ሰበታዎች ጥሩ የሚባል አጋማሽ በማሳለፍ ከተለያየ አቅጣጫ ጥቃት ሲሰነዝሩ የነበሩ ሲሆን በተለይም በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያ 11 ተሰላፊነት የተካተቱት በኃይሉ አሰፋ፣ አሲ ባድራ እንዲሁም ቫኑ ዲያዋራ ያደረጓቸው መከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበረ።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር በጨዋታ እንቅስቃሴሜ ሆነ በግብ እድሎች በመጠኑም ቢሆን የተቀዛቀዘ ነበር። ብዙም ማራኪ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በኃይሉ አሰፋ ከቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ኳስ ማስቆጠር ቢችልም ኳሷ ከጨዋታ ውጭ በሚል በዳኛው ሳትፀድቅ ቀርታለች።

ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማ ነጥቡን ወደ 4 በማሳደግ ምድቡን መምራት ሲጀምር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንድ ነጥብ ከምድቡ ግርጌ ይገኛል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኤሌክትሪኩ ስንታየሁ ዋለጮ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ሊመረጥ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ