የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በዲኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ ቅድመ ዝግጅት መጀመሩ ተገለፀ

አዲስ የተቋቋመው የፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመሆን ከሱፐር ስፖርት ኃላፊዎች ጋር ሊጉን በቀጥታ በዲኤስ ቲቪ እንዲተላለፍ ውይይቶች መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

ትላንት በአዳማ ከተማ በተደረገው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ሀሳባቸውን በዕለቱ የሰጡ ሲሆን ከተቻለ ዘንድሮ ካልሆነ ደግሞ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በቀጥታ በዲኤስ ቲቪ እንዲተላለፍ ከሱፐር ስፖርት የበላይ አካላትን ከመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ጋር በመሆን በአካል አግኝተው መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጉዳዩ ዙርያ በሰጡት አስተያየት “ከዲኤስ ቲቪ ሰዎች ጋር ተነጋግረናል ፕሮፖዛልም አምጡ ብለውናል። አሁን ላይ ያን ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ሊጉን ተመራጭ እና ሳቢ አድርጎ ለዓለም ህዝብ ለማሳየት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የፕሪምየር ሊጉ መጠሪያ ስፖንሰር መኖር አለበት፣ ከዛም ባለፈ ከአዲዳስ ጋር በመነጋገር የሊጉ አርማ ያለበት የመጫወቻ ኳስ ለማቅረብ እየተንቀሳቀስን ነው። ያን ለማድረግ ደግሞ ፕሪምየር ሊጉን የሚወክል አርማ (logo) በፍጥነት መሠራት ይኖርበታል፤ ያ ከተጠናቀቀ በኋላ ዕቅዳችንን ተግባራዊ እናደርጋለን። እነኚህን ተግባራት ፈፅመን በቀጥታ ስርጭት መተላለፍ ከቻለ እመኑኝ እግር ኳሳችን ያኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ ይሆናል።” በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ