“የምድቡን ከባድ ቡድን ማሸነፋችን በራሱ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው የሚሆነን” አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ


ኢትዮጵያ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ለ2021 የካሜሩኑ አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታ ኮትዲቯርን 2-1 ካሸነፈች በኋላ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” ጨዋታውን እንደተመለከታችሁት ነው። ከተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራ ጋር አሸንፈን ወጥተናል።” ያሉት አሰልጣኝ አብርሀም ቡድናቸው ከአህጉሪቱ ታላላቅ የእግርኳስ ሀገራት የምትመደበው ኮትዲቯርን ማሸነፋቸው ለቀጣይ የብሔራዊ ቡድኑ ጉዞ ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

“በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ውስጥ ወይም ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ መልካም ምዕራፍ አድርገን ነው የምናስበው። የምድቡን ከባድ ቡድን ማሸነፋችን በራሱ ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው የሚሆነን። ቀጣይ ጨዋታዎችን በከፍተኛ መነሳሳት መንፈስ እየተዘጋጀን እንድንሰራ ያደርገናል። ”

አሰልጣኙ በመጨረሻም ለድሉ መገኘት አስተዋፅኦ አድርገዋል ያሏቸውን በዚህ መልኩ አመስግነዋል። “ተጫዋቾቹ በሜዳ ውስጥ የተሰጣቸውን ሁሉ ተቀብለው በማድረግ ትልቅ ስራ ሰርተዋል፤ ላመሠግናቸውም እፈልጋለሁ። ከቡድኑ ጀርባ የነበረው የባህር ዳር እና የአካባቢዋን ህዝብ ከሩቅ ቦታ መጥተው የደገፉንን ሁሉ እጅግ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ