“የዛሬው ውጤት አንድ ደረጃ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተጠጋንበት ነው” ሽመልስ በቀለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ጠንካራዋ አይቮሪኮስትን 2-1 ካሸነፈች በኋላ አምበሉ ሽመልስ በቀለ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ከወትሮው በተለየ መልካም እንቅስቃሴ አድርጎ ያሸነፈውን ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ የዋለውና ወሳኟን የማሸነፍያ ጎል ያስቆጠረው ሽመልስ በቀለ ለድሉ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን አመስግኗል። “በመጀመሪያ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን። ሲቀጥል እዚህ አጠገቤ የሚገኘውን አሰልጣኛችንን ማመስገን እፈልጋለሁ። በራስ መተማመኑ ፣ ወጣቶችን ሰብስቦ ዕምነት ጥሎባቸው ይሄን ያህል ውጤት ስላመጡ ፤ የኛ ውጤት ሳይሆን የእርሱ ውጤት ነው ማለት እችላለው። እናም በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኛችንን ማመስገን እፈልጋለሁ። ተጫዋቾቹ በጠቅላላ ወጣት ተጫዋቾች ናቸው ፤ ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። ብሔራዊ ቡድን ሲባል ውጤት ሲኖር ብቻ ሳይሆን ውጤት ሲጠፋም መደገፍ አለባችሁ። ተጫዋቾችንም ማመስገን እፈልጋለሁ። ” ብሏል።

የዋሊያዎቹ አምበል አክሎም የዛሬው ድል ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ያለውን ዋጋ “የዛሬው ውጤት አንድ ደረጃ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተጠጋንበት ነው። ለኔ በዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ብቻ ሳይሆን ስድስት ነጥብ እንዳገኘን ነው የምቆጥረው። ” በማለት ገልጾታል።

ሽመልስ በመጨረሻም ይህን ብሏል። ” ጥሩ የአሰልጣኞች ስብስብ ፣ ጥሩ የተጫዋቾች ስብስብ እንዲሁም ጥሩ የህክምና ቡድን አለን። እኛ ተያይዘን እስከሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ውጤት እናመጣለን። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም ስታድየም ተገኝተው ለደገፉን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ