ሴካፋ ሴቶች ዋንጫ | ኢትዮጵያ ከምድብ መውደቋን ስታረጋግጥ ዩጋንዳ እና ኬንያ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

በታንዛኒያ ዳሬ ሠላም እየተደረገ ባለው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ከምድብ አንድ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ ኢትዮጵያ በኡጋንዳ 1ለ0 ተረታ ከምድቡ መውደቋን አረጋግጣለች። ኬንያ ደርዘን ግብ ጅቡቲ ላይ አስቆጥራ በማሸነፍ ከዩጋንዳ ጋር ወደ ግማሽ ፍፃሜው መግባቷንም አረጋግጣለች፡፡

8:00 ላይ በጀመረው የኬንያ እና የጅቡቲ ጨዋታ ኬኒያ 12ለ0 ረምርማለች፡፡ አራት ፍፁም ቅጣት ምቶች በተሰጡበት በዚህ ጨዋታ ማዋሊማ ጄርካ እና ሜርሲ ኤሮ እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰሩ አጥቂዋ ጀንትሪክ ሺካንጉዋ ደግሞ አራት ግቦችን ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ቀሪዎቹን ግቦች ቪቪያን ማካሀ እና ጀነት ቡንዲ አንድ አንድ ግቦችን አክለው ጨዋታው በሀራምቤ ከዋክብት 12ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

10:30 በዕለቱ ሁለተኛ የምድቡ ጨዋታ ሉሲዎቹ በዩጋንዳ 1ለ0 ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡ በጨዋታው ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ቢስተዋልም ሉሲዎቹ በመከላከሉ አሁንም ባሳዩት ድክመት ሀሲፋ ናሱማ በግራ በኩል የሰጠቻትን ኳስ በ73ኛው ደቂቃ ፋውዚያ ናንጂባ እየገፋች በቀኝ በኩል በመግባት ለኡጋንዳ ብቸኛዋን ግብ ዩጋንዳ ድል አድርጋለች።

በዚህም መሠረት ዩጋንዳ እና ኬንያ በምድቡ ቀሪ የእርስ በእርስ ጨዋታ እየቀራቸው አስራአራት ንፁህ ግብ በመያዝ በእኩል ስድስት ነጥቦች ለግማሽ ፍፃሜ ሲያልፉ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ከምድቡ መውደቃቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ውድድሮች ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ብትችልም በዘንድሮው ውድድር ከምድቧ ተሰናብታለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ