“የኮትዲቯርን ቡድን እንደጠበቅነው አላገኘነውም” አስቻለው ታመነ

በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የአሰልጣኝነት ዘመን በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ያደረገው እና በዛሬው ጨዋታ ጥሩ የተንቀሳቀሰው አስቻለው ታመነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

የዛሬው ጨዋታ እንዴት ነበር?

ጨዋታው በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር። ቅዳሜ በማዳጋስካር በተሸነፍንበት ጨዋታ ቡድኑ ጠንካራ እንደነበር እና እለት ከእለት እየተሻሻለ እንደመጣ ተመልክታችኋል። ዛሬም ይህ ነገር ነው የታየው። የገጠምነው ትልቅ ቡድን ቢሆንም በልጠን ጥሩ ተጫውተናል።

ስለተጋጣሚያችሁ ቀድሞ የነበራችሁ እና በሜዳ ላይ ያያችሁት ነገር እንዴት ትገልፀዋለህ?

የኮትዲቯርን ቡድን እንደጠበቅነው አላገኘነውም። ቡድኑ በትልቅ ደረጃ እና በትላልቅ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾችን የያዘ ቡድን ነው። ግን በሜዳ ላይ ያየነው ነገር ቡድኑ ብዙም አስፈሪ እንዳልሆነ ነው። መጀመሪያም እኛ አክብረናቸው እንጂ ፈርተናቸው ወደ ሜዳ አልገባንም። በአጠቃላይ ሰጥተናቸው የነበረው ግምት እና ሜዳ ላይ ያየነው ነገር አይገናኝም።

የብሄራዊ ቡድኑን (የኢትዮጵያ) እንቅስቃሴ እንዴት ትገመግመዋለህ?

ቡድኑ በጣም ጥሩ ነበር። እኛ ከእነሱ ተሽለን የተንቀሳቀስነው ኳስ ይዘን በመጫወታችን ነው። ከላይ እንደገለፅኩልህ እነሱ (ኮትዲቯሮች) ጥሩ አልነሩም። እኛ ግን ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረን፣ በልጠን፣ በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረን አሸንፈናል።

በግል በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰሃል። በተለይ ውሳኔዎችህ እና በራስ መተማመንህ ግሩም ነበር። ይህ በዛሬው ጨዋታ ከምን ሊመነጭ ቻለ?

እኔ ብዙ ጊዜ ጨዋታ ስጫወት ተረጋግቼ ነው። በክለብ ስትጫወት የምትከተለው አጨዋወት እና በብሄራዊ ቡድን የምትከተለው አጨዋወት ይለያያል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ደግሞ ተረጋግተን ኳስ ይዘን እንድንጫወት ይፈልጋል። ይህንን ጨዋታ ደግሞ ለማከናወን ኳስ ከኋላ መመስረት አለበት። ለዚህ ደግሞ እኔ በጥሩ የራስ መተማመን ዛሬ ተጫውቻለው።

የቡድኑን እድገት እንዴት ትገመግመዋለህ (በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ስር)?

አብርሃም መብራቱ ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ እኔ በሁሉም ስብስብ ውስጥ አለሁ። ቡድኑ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ የመጣ ቡድን ነው። ትንሽ የሚቀረው ልምድ ነው። በተለይ ወደ ጎል ስንሄድ መረጋጋት አይታይብንም። ይህ ደግሞ በሂደት እና በልምምድ የሚቀረፍ ነው። አንድ ብሄራዊ ቡድንን በአንድ ዓመት አትገመግመውም። ይህም ቡድን ጊዜ ይፈልጋል። ጠቅለል ለማድረግ ግን ቡድኑ ወደፊትም የሚያድግ እና የሚለወጥ ብሄራዊ ቡድን ነው።

የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድን ነው?

ቡድኑ ዛሬ እንደ ቡድን ተጫውቶ ማሸነፉ ቡድኑን ሙሉ እና ጥሩ ቡድን አያስብለውም፣ ክፍተቶች አሉብን ብዬ አስባለሁ። እርግጥ እኔ ተጨዋች ነኝ። ሜዳ ውስጥ ነው የምጫወተው። ስለዚህ ከእኔ የተሻለ አሰልጣኙ ያሉትን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች ይለያል። ግን በግሌ ቡድኑ ግብ የማግባት ችግር አለበት ብዬ አስባለሁ። የአጨራረስ ችግራችንን ብናስተካክል ጥሩ ነው። እርግጥ ይህ ጉዳይ ከልምድ የመጣ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን ወደፊት እንደሚስተካከል አስባለሁ። የቡድኑ ጠንካራ ጎን በወጣቶች የተገነባ መሆኑ ነው። የተጨዋቾቹ ህብረት እና ፍላጎት የሚገርም ነው። ስለዚህ እንደእኔ ጠንካራ ጎናችን የጨዋታ ፍላጎታችን እና ህብረታችን ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ