ሙጂብ ቃሲም ስለ ሐት-ትሪኩ እና ወቅታዊ አቋሙ ይናገራል

ትላንት ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ፋሲል ከነማ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 5-0 ማሸነፉ ይታወሳል። በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው ሙጂብ ቃሲምም ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ተጫዋቹ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል።

ስለ ሐት-ትሪኩ

በጣም ነው ደስ ያለኝ። የመጀመሪያ ጨዋታችን ከሜዳችን ውጪ ነበር፤ ያም ቢሆን የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ከአዳማ አንድ ነጥብ ይዘን መጥተናል። ጨዋታውም ጠንካራ ነበር። በሜዳችንም የተሻለ የማሸነፍ ሞራል ይዘን በመመለስ በዛሬው ጨዋታ የተሻለ ነገር አሳይተን ወጥናል። ሦስት ጎልም በማስቆጠሬ እጅግ በጣም ነው ደስያለኝ።

ከእረፍት መልስ ስለመሻሻላቸው

የመጀመሪያው አጋማሽ ጎል ካስቆጠርን በኋላ ትንሽ ወደ ኋላ አፈግፍገን የተጫወትነው። ያም የሆነው ምክንያት ትንሽ አየሩ ከባድ ነበር። ለረዥም ጊዜም ከዚህ ሜዳ ርቀን ስለተመለስን ያም ተፅእኖ አድርጎብናል። በይበልጥ የተሻለ ደግሞ ጎል አግብተን መውጣት እንዳለብን ኮቹም ነግሮን ነበር። ያንን አሻሽለን በመግባት የተሻለ አስቆጥረናል።

ከቡድኑ እና ከሙጂብ ምን እንጠብቅ

ያው በጣም አሪፍ አጀማመር ነው የጀመርነው፤ የተሻለ ነገር ዘንድሮ እንሰራለን። የተሻለ ነገር ጠብቁ፤ ለዋንጫ እንጫወታለን። በኔ በኩል ፈጣሪ ያውቃል፤ አብረን የምናየው ይሆናል።

ከሽመክት ስለነበረው መናበብ

በጣም አሪፍ ነው! ብዙ እንግባባለን በጣም ጎደኛዬም ነው። ዐምናም አንድ ላይ ነበርን፤ ሜዳ ላይም ሆነ ልምምድ ላይ ጥሩ ተግባብተን እየሰራለን እንጫወታለን። ያን መግባባት ይመስለኛል ሜዳ ላይ ያያየችሁት።

ከረጅም ወራት በኋላ ከደጋፊ ጋር መገናኘት

ለዐፄዎቹ ደጋፊዎች ቃላት ያጥረኛል! ለእኔ ራሱ በጣም ዕድለኛ ነኝ በዚህ ደጋፊ ፊት መጫወቴ። በጣም አድናቆት እና ክብር አለኝ ፣በጣም ነው የምወዳቸው ማከብራቸው። የተለዩ ናቸው።

የሚና ለውጥ

ብዙ ጊዜ የአሰልጣኞች ውሳኔ ነው፤ የተጫዋቾችን ኳሊቲ አይተው መወሰን የሚችሉት። እኔን እንደተጫዋች ያለኝን ነገር ተረድቶኝ የነበረው ውበቱ ነው። እንድተገብረውም ስላደረገኝ በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ