ዜና እረፍት | አንጋፋው አሰልጣኝ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ሥማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱ አንጋፋ አሰልጣኞች መካከል የነበሩት ወንድማገኝ ከበደ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አሰልጣኝ ወንድማገኝ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከጤና እክል ጋር በተያያዘ ከሙያው ርቀው ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቀዩ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ህይወታቸው ማለፉን ለማወቅ ተችሏል።

በተጫዋችነት ዘመናቸው ግብ ጠባቂ የነበሩት ወንድማገኝ ከበደ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድንን ጨምሮ በርካታ የሀገሪቱን ክለቦች ያሰለጠኑ ሲሆን በብሔራዊ ቡድኑ የተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ሰርተዋል። ከኤሌክትሪክ ጋርም በ1985 የኢትዮጵያ ቻምፒዮን ሆነዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለእግርኳስ ቤተሰቡ መፅናናትን ይመኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ