ሪፖርት | ሲዳማ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ በመቅረብ ስሑል ሽረን በሰፊ ልዩነት ረቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው ሳምንት የዛሬ ብቸኛ መርሐ-ግብር ሀዋሳ ላይ በዝግ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና ስሑል ሽረ ጨዋታ በሲዳማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡና በ2011 የውድድር ዘመን ከደቡብ ፖሊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ በታየው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የተነሳ ተጣለበት ቅጣት የዛሬውን ጨዋታ ያለ ተመልካች ያደረገ ሲሆን ከመጀመሪያ ሽንፈት በሚገባ ማገገሙን ያረጋገጠበትን ጣፋጭ ድል ተጎናፅፏል፡፡

ሲዳማ ቡና ወደ ሶዶ አምርቶ በሊጉ ጅማሮ በወላይታ ድቻ በተሸነፈበት ጨዋታ ከተጠቀመው የመጀመርያ አስራ አንድ በሦስቱ ላይ ለውጥ በማድረግ ክፍሌ ኪአን በግሩም አሰፋ፣ ብርሀኑ አሻሞን በሰንደይ ሙቱኩ፣ ዮሴፍ ዮሀንስን በዳዊት ተፈራ ሲተካ ስሑል ሽረ ኢትዮጵያ ቡናን ባለፈው ሳምንት 1ለ0 በረታበት ጨዋታ የተጠቀመውን ሙሉ ስብስብ ዛሬም ወደሜዳ ይዞ ገብቷል፡፡

ተመጣጣኝ እና ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ዕረፍት አልባ በሆነ ሁኔታ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። ይሁንና ሲዳማ ቡና በረጃጅም ኳስ እና በፈጣሪ አማካዩ ዳዊት ተፈራ እግር ከሚነሱ ዕድሎች ጥቃት ቢሰነዝሩም ለሀብታሙ ገዛኸኝ የሚደርሱ መልካም አጋጣሚዎች ተጫዋቹ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ሳይሳኩ ቀርተዋል። ሀብታሙ አስር ጊዜ ያህል ረዳት ዳኛው የጨዋታ ውጪ ምልክት ያነሱበት አጋጣሚም አስገራሚ ነበር፡፡

ሦስት የውጪ ዜግነት ያላቸውን አጥቂዎች ከፊት ያደረጉት ሽረዎች በተለይ በሁለቱም መስመሮች በፈጣኖቹ ዲዲዬ ሊብሪ እና አብዱለጢፍ መሐመድ አማካኝነት ወደ ሳጥን የሚልኳቸው ተሻጋሪ ኳሶች አስፈሪ የነበሩ ሲሆን የሲዳማ ቡና ተከላካዮች እየተረባረቡ ሲያወጡ የነበሩባቸው አጋጣሚዎችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም። 13ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከቅጣት ምት በቀጥታ መቶ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበትም የመጀመሪያዋ ሽረዎች ያደረጓት ሙከራ ነች፡፡ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ 20ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ በኩል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያሳለፈለትን ኳስን ይገዙ ቦጋለ ሲመታው ብረት የመለሰበት የመጀመርያ አስደንጋጭ ሙከራ ነበር፡፡

ስሑል ሽረዎች በተደጋጋሚ በጋናዊው የመስመር አጥቂ አብዱለጢፍ መሀመድ አስፈሪ አጋጣሚን ፈጥረዋል። በተለይ 30ኛው ደቂቃ አብዱለጢፍ በቀጥታ በግራ አቅጣጫ ለሙሉዓለም ረጋሳ ሰጥቶት አማካዩ ለዲዲዬ ሰቶት አይቮሪኮስታዊው በቀጥታ መቶ ከግቡ ጠርዝ ጊትጋት በግንባር ያወጣት ሽረን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል ነበረች፡፡

በ34ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከተደጋጋሚ የጨዋታ ውጪ እንቅስቃሴ ተመልሶ ያገኛትን መልካም ዕድል ወደ ግብ ክልል በረጅሙ ሲልካት ይገዙ ቦጋለ ኳሷ ሳታርፍ ደርሶባት አስቆጥሮ ቡናን መሪ አድርጓል፡፡ ሲዳማዎች ግብ ካገቡ በኃላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ባመሩበት ሰዓት ሊነጠቁ በመቻላቸው 44ኛው ደቂቃ ረመዳን የሱፍ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ከመስመር እየገፋ በመግባት ነፃ አቋቋም ለነበረው ዲዲዬ ለብሪ አመቻችቶለት ዲዲዬም ለሽረ አስቆጥሮ 1ለ1 ሆነዋል፡፡ በጭማሪ የእረፍት ሰዓት መውጫ አዲስ ግደይ መሪ ሊያደርጋቸው የሚችሉበትን መልካም ዕድል ቢያገኝም አልተጠቀመም፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ስሑል ሽረዎች ከነበራቸው የመጀመሪያ አጋማሽ ጥንካሬ ወርደው ሲገቡ ሲዳማ ቡናዎች የሀብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይን አቅም በአግባቡ የተጠቀሙበት ነበር፡፡ ሽረዎች ረጃጅም ኳሶችን ገና የዳኛው ፊሽካ ከተሰማ ጀምሮ ለመጠቀም ቢያልሙም ሜዳውን አጥብበው ሲጫወቱ በነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ቁጥጥር ስር በቶሎ ገብቶባቸዋል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ተቆጣጥሮ በፍጥነት አመቻችቶ አዲስ ግደይ በአግባቡ በመጠቀም ባለሜዳዎቹን መሪ አድርጓል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ 57ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን አሻምቶ ዲዲዬ በቀጥታ ከግብ ጠባቂው መሳይ ጋር ተገናኝቶ መሳይ ከግቡ ጠርዝ እንደምንም ያወጣበት ኳስ ሽረን በድጋሚ አቻ ለማድረግ የቀረበች ነበረች፡፡ ብዙም ሳይቆይ 59ኛው ደቂቃ ላይ አበባየው ዮሀንስ በግራ በኩል በረጅሙ የጣለውን ኳስ የስሑል ሽረ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሎ ግብ ክልሉን ለቆ በመውጣቱ ሀብታሙ ገዛኸኝ በፍጥነት አግኝቷት የሲዳማ ቡናን መሪነት አስተማማኝ ያደረገች ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡

ሽረዎችን ሙሉዓለም ረጋሳን አስወጥተው ሀብታሙ ሸዋለምን ካስገቡ በኃላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ራሱ ሀብታሙ አግኝቶ ያመከናት እና ፎፋና ከመስመር ሰቶት ዲዲዬ በቀጥታ መቶ መሳይ አያኖ አቅሙን ተጠቅሞ ያወጣበት ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም 82ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ላይ በተሰራ ጥፋት በሳጥኑ ጠርዝ የሰጠውን ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ በግሩም ሁኔታ ለራሱ ሁለተኛ ሲዳማ ቡናን 4ለ1 ማሸነፉን ያበሰረች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከግቡ በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ እንግዳው ቡድን ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቶ ሲዳማ ቡና የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ያለ ደጋፊዎቹ አሳክቷል፡፡

*ከእረፍት መልስ ጨዋታው እየተደረገ ባለበት ሰዓት ከግቡ ትይዩ ለመቀየር ሲያሟሙቁ የነበሩ ተጫዋቾች በሜዳው አቅራቢያ ሲፀዳዱ ያስተዋልን ሲሆን ይህም ስታዲየሙ በቂ የመፀዳጃ ቤት አለመኖሩን የሚያመላክት ከመሆኑ ባለፈ ተጫዋቾች ራሳቸው በሚጫወቱበት ሜዳ ላይ እንዲህ አይነት ተግባር ማድረጋቸው ለቀጣይ ሊታረም ይገባዋል እንላለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: