ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ተከናውነዋል። በዚህም በስምንቱ ጨዋታዎች በንፅፅር ጥሩ አቋም ያሳዩ 11 ተጫዋቾችን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን በሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።

አሰላለፍ፡ 4-4-2


ግብ ጠባቂ

አቤር ኦቮኖ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሀድያ ሆሳዕና በዓመቱ የመጀመርያው የሜዳ ውጭ ድል እንዲያስመዘግብ ትልቅ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሦስት ሙከራዎች በማክሸፍ ቡድኑ ግቡን ሳያስደፍር እንዲወጣ የጎላ ድርሻ የነበረው ይህ ተጫዋች ይህ ብቃቱ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን እንዲገባ አስችሎታል።


ዓለምብርሃን ይግዛው (ፋሲል ከነማ)

ወሳኝ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ያሬድ ባየህና እንየው ካሳሁንን ያጣው ፋሲል ከነማ የተከላካይ መስመሩን ክፍተት ለመሸፈን በተደረገ የተጫዋቾች የቦታ ሽግሽግ ከቀደመው ቦታው ወደ የቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሸጋገረው ወጣቱ ዓለምብርሃን አዲሱ ሚናውን በሂደት እየተላመደ መጥቷል። በእሁዱ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ላይ ተጋላጭ በነበረው የቀኝ መስመር ላይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ከነበረው ስኬት ባሻገር ወደፊት እንዲሁም ወደ መሀል እየሰበረ በመግባት ጥሩ ቀን አሳልፏል።


ምኞት ደበበ (አዳማ ከተማ)

ይህ ግዙፍ የተከላካይ መስመር ተጨዋች ቡድኑ በሜዳው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። በተለይ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥቃቶችን ለመሰንዘር አስበው የገቡትን የሀዋሳ ከተማ ተጨዋቾች የተቆጣጠረበት መንገድ የሚደነቅ ነው። ተጨዋቹ ቡድኑን በአምበልነት ከመምራቱ በተጨማሪ ቁልፍ ቁልፍ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ክልል በመላክ ቡድኑን ለመጥቀም ጥሯል። ከዚህ ውጪ ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር ላለበት ቡድኑ ወደፊት ሰብሮ በመግባት የጎል ዕድል ለመፍጠር ተግቷል።


ደስታ ጊቻሞ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ከወልዋሎ ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ካሳዩ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ይህ ተከላካይ የተጋጣሚ ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ የሆነውን ረጃጅም ኳስ በማክሸፍ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። የተከላካይ ክፍሉ በመምራት እና አደረጃጀቱን በማስተባበር ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የመከላከል ቅርፅ እንዲይዝ ጉልህ ድርሻ የነበረው ይህ ተጫዋች በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ሲገባ የመጀመርያው ነው።


ረመዳን የሱፍ (ስሑል ሽረ)

ከዐምና ወዲህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ጎልተው በመውጣት ላይ ከሚገኙ የመስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው ረመዳን በዚል ሳምንት ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ላሳካው ድል ወሳኝ ሚና መጫወት ችሏል። በጨዋታው ጥሩ ከመንቀሳቀሱ ባሻገር ቡድኑ ቀዳሚ የሆነበትን የመጀመርያ ጎል ማስቆጠር የቻለው ረመዳን ለሁለተኛ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ሊካተት ችሏል።


አማካዮች 

ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ (መቐለ 70 እንደርታ)

አማካዩ በጉዳት እየታመሰ ለሚገኘው የመቐለ 70 እንደርታ በጭንቅ ወቅት የተገኘ ሁነኛ ተጫዋች ሆኗል። ከጥልቅ የሚነሳ አማካይ እንዲሁም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ መስመር እየወጣ በተለያዩ ሚናዎች በአግባቡ እየተወጣ የሚገኘው ተጫዋቹ ከአምናው በተሻለ እያገኘ የሚገኘውን የጨዋታ ደቂቃዎች በአግባቡ በመጠቀም ላይ ይገኛል። በእሁዱ የወልቂጤ ጨዋታም የተጋጣሚው የማጥቃት አማካዮች በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ቀን አሳልፏል።


አበባየሁ ዮሐንስ (ሲዳማ ቡና)

አማካዩ በዚህ ሳምንት ሲዳማ ቡና በባህር ዳር ላይ ላሳካው ድል ያበረከተው አስተዋፅኦ ለሁለተኛ ጊዜ በምርጥ 11 ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል። ተጫዋቹ የሲዳማ ቡና የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የነበረ ሲሆን ወደ ማጥቃት ወረዳው ተደጋጋሚ ኳሶችን ከማድረስ ባሻገር አንድ ጎል አስቆጥሮ ለሌላ አንድ ጎል ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ ችሏል።


አብዱልከሪም ወርቁ (ወልቂጤ ከተማ)

አየዐምና የከፍተኛ ሊጉ ክስተት የነበረውና በአካለ መጠን ደቀቅ ያለው ነገርግን የፈጣን አዕምሮ ባለቤቱ አብዱልከሪም እንደ በቅርብ ጨዋታዎች የቡድኑን የመሀል ሜዳ የፈጠራ ብቃት ሲያሳድግ ተስተውሏል። በዚህኛው ሳምንት ወልቂጤ ምንም እንኳን በመቐለ ቢሸነፍም እንደ ቡድን የተሻሉ በነበሩት ወልቂጤዎች ያመከኗቸው አስቆጪ የጎል እድሎች መነሻ አብዱል ከሪም ነበር።


ጋዲሳ መብራቴ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በከፍተኛ ፍላጎት እየተጫወተ የሚገኘው የመስመር አማካዩ ጋዲሳ ፈረሰኞቹ ድሬዳዋ ከተማን ሲያሸንፉ ደምቆ መዋል ችሏል። ከጠባብ አንግል ግሩም የቅጣት ምት ጎል ከማስቆጠር በዘለለ አንድ ኳስ ለጌታነህ ከበደ አመቻችቶ ያቀበለው ጋዲሳ ለመጀመሪያዋ ግብ መቆጠርም ከፍተኛ ሚናን በመወጣት በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው።


አጥቂዎች

ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ)

ፋሲል ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በሜዳው በረታበት ጨዋታ ሙጂብ ቃሲም አሁንም ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን አስመስክሯል። በጨዋታው ሁለቱም የፋሲል ግቦች አንዱን ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ አክርሮ በመምታት እንዲሁም ሌላኛውን ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በ9 ግቦች መራ የሚገኘው ሙጂብ ከሁለተኛው ሳምንት በኋላ በምርጥ 11 ውስጥ መካተት ችሏል።


ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ከሰሞኑ በማጥቃት ረገድ መሻሻል ባሳየው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን እያሳየ የሚገገኘው ጌታነህ በትላንቱ ጨዋታ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ወደ ጎል ማስቆጠር ተግባሩ ከመመለሱ ባሻገር ተጎድቶ እስኪወጣ ድረስ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥም ለሁለተኛ ጊዜ መካተት ችሏል።


ተጠባባቂዎች

ሀብቴ ከድር (ሀዋሳ ከተማ)

ዐወል መሐመድ (ወልቂጤ)

ነፃነት ገብረመድህን (ስሑል ሽረ)

ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)

ባኑ ዲያዋራ (ሰበታ ከተማ)

ሀብታሙ ታደሰ (ኢትዮጵያ ቡና)

አማኑኤል ገ/ሚካኤል (መቐለ 70 እንደርታ)

© ሶከር ኢትዮጰያ