ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ፡ አአ ከተማ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ጅንካ ከተማ አስደናቂ ውጤት አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደዋል፡፡ የጅማ ክለቦች ውጤታማ ሳምንት ሲያሳልፉ አዲስ አበባ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ ጅንካ ከተማ ደግሞ ፌዴራል ፖሊስ ላይ ጎል አዝንቧል፡፡

አበበ ቢቂላ ላይ ሀላባ ከተማን ያስተናገደው አአ ከተማ በሰፊ ውጤት በማሸነፍ ወደ ያለፈው ሳምንት ሽንፈቱን አካክሷል፡፡ አአ ከተማ 4-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ዮናታን ብርሃነ የመክፈቻዋን ግብ ሲያስቆጥር አምበሉ ሙሃጅር መኪ የመጀመርያውን አጋማሽ በ2-0 መሪነት እንዲያጠናቅቁ ያስቻለች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የነባው ኃይሌ እሸቱ 3ኛውን ሲያስቆጥር ፍፁም ካርታ የማሳረጊያውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ጅማ አባ ቡና ወደ ነቀምት ተጉዞ በድል ሲመለስ የአባ ቡና ድል በአስገራሚ መገጣጠም ታጅቧል፡፡  ባለፈው ሳምንት መሪው አአ ከተማን 3-1 ያሸነፈው አባ ቡና ነቀምትንም በተመሳሳይ 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ አአ ከተማ ላይ ሁለት ግብ ያስቆጠረው አጥቂው ኦሜ መሃመድ በነቀምት ላይም ሁለት ግቦች አስቆጥሯል፡፡ ቀሪዋን አንድ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ኪዳኔ አሰፋ ሲሆን የነቀምት ግብ ስታየሁ እጅጉ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ጅማ ላይ ጅማ ከተማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 3-0 በማሸነፍ ከ3 ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ የቀይ ለባሾቹን ግቦች ከመረብ ያሳረፉት ሳሙኤል አሸብር ፣ መላከ መስፍን እና ዝናቡ ባፋ ናቸው፡፡ ድሉ ጅማ ከተማ ደረጃውን ወደ 4ኛ እንዲያሻሽል አግዞታል፡፡

ጅንካ ከተማ ፌዴራል ፖሊስን 5-0 በማሸነፍ የሳምንቱን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የጅንካን የድል ግቦች ዋቁማ ሁለት ፣ ኪዳነ ማርያም ፣ ደለሞኒ እና መኮንን አንድ አንድ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የውድድር ዘመኑን በከባድ ሽንፈት የጀመረው ጅንካ በፍጥነት አገግሞ 10 ነጥቦች በመሰብሰብ ደረጃውን ወደ 5ኛ ከፍ አድርጓል፡፡

ከሳምንታት በፊት አሳ በመዝነቡ መነጋገርያ ርዕስ ሆና የሰነበተችው ድሬዳዋ ላይ ዛሬ የጎል ዝናብ ዘንቧል፡፡ 8 ግቦች በተስተናገደበት ጨዋታ ድሬዳዋ ፖሊስ አርሲ ነገሌን አስተናግዶ 4-4 ተለያይቷል፡፡ የእንግዳውን ቡድን ግቦች ሚልዮን ይስማ ሁለት ደረሰ ተሰማ እና ጌታአለም ማሙዬ አንድ አንድ ግብ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የድሬዳዋ ፖሊስን ግቦች እዩኤል ሳሙኤል እና ብሩክ ግርማ አንድ አንድ ሲያስቆጥሩ አምበሉ ዮርዳኖስ አባይ ሁለት ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ባለፉት 3 ጨዋታዎች 4 ግብ ከመረብ ያሳረፈው ዮርዳኖስ ከአመታት በኋላም የግብ አዳኝነት ብቃቱ አብሮት እንዳለ አስመስክሯል፡፡

ደቡብ ፖሊስ አሁንም ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ሀዋሳ ላይ ነገሌ ቦረናን ያስተናገደው ደቡብ ፖሊስ 1-1 ተለያይቶ ወራጅ ቀጠናውን ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተጋርቷል፡፡ የደቡብ ፖሊስን ግብ ወንድሜነህ አይናለም ሲያስቆጥር የነገሌ ቦረናን ግብ ዳግም በቀለ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ባቱ ላይ ባቱ ከተማ ናሽናል ሴሚንትን አስተናግዶ ካለግብ አቻ ሲለያይ ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከ ወራቤ ከተማ በተመሳሳይ ካለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ሻሸመኔ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ካለግብ አቻ ተለያይቶ ከመሪዎቹ ያለውን ርቀት የማጥበብ እድሉን አበላሽቷል፡፡

የምድብ ለ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

B

ፎቶ – አዲስ አበባ ከተማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *