6ኛ ሳምንቱን በያዘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደዋል፡፡ ወልድያ በድጋሚ ሽንፈት አስተናግዶ ሲንሸራተት መቐለ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ባለመሸነፍ ጉዟቸው ቀጥለዋል፡፡ አዲስ አበባ ፖሊስም መሪነቱን አስጠብቋል፡፡
በአሰላ ስታድየም የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በ9፡00 የሚደረግ በመሆኑ ቀደም ብሎ 7፡00 ላይ የተደረገው የሙገር ሲሚንቶ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ጨዋታ በፖሊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አዲስ አበባ ፖሊስ የምድቡ መሪ ሆኖ የቀጠለበትን ብቸኛ ግብ ከእረፍት በፊት ከመረብ ያሳረፈው ልማደኛው አባይነህ ፌኖ ነው፡፡
ትግራይ ስታድየም ላይ ወልድያን ያስተናገደው መቐለ ከተማ 1-0 አሸንፏል፡፡ የመቐለን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ሙሉጌታ አዳሙ ነው፡፡ ድሉ እስካሁን ሽንፈት ያላስተናገደው መቐለን ከመሪው በ1 ነጥብ አንሶ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጠው ድንቅ አጀማመር አድርጎ የነበረው ወልድያ ወደ 5ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ስታድየም ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ያስተናገደው ባህርዳር ከተማ 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ለባህርዳር ከተማ ተዘራ ጌታቸው ሁለት ሲያስቆጥር ተስፋሁን ፣ ውብሸት እና ፍፁም አንድ አንድ ግብ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የአዲግራቱን ክለብ አንድ ግብ ኢሳያስ ታደሰ ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡
ወሎ ኮምቦልቻ ቡራዩን 1-0 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ ኮምቦልቻ ላይ በተደረገው ጨዋታ የወሎ ኮምቦልቻን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ሱልጣን ጣዕመ ነው፡፡
ፋሲል ከተማ ተከታታይ ጨዋታ በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ ወደ ሱሉልታ የተጓዘው ፋሲል 2-0 ሲያሸንፍ አብዱራህማን ሙባረክ እና መሃመድ አብደላ የአፄዎቹን የድል ግቦች ከመረብ አሳርፏል፡፡ ፋሲል ከተማ የሱሉልታ ስታድየም ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ በሌላ አማራጭ ስታድየም ጨዋታው እንደደረግ ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው ጥያቄ ተገባይነት ባለማግኘቱ ሱሉልታ በውድድር ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ በራሱ ሜዳ ጨዋታ አድርጓል፡፡
አበበ ቢቂላ ላይ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ሰበታ ከተማን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል፡፡ ጨዋታው ከሁለቱም በኩል በርካታ ሙከራዎች ያስተናገደ ሲሆን ሰበታ ከተማ በናትናኤል ጋንጂላ ግብ መሪ መሆን ችሎ ነበር፡፡ ዘንድሮ ድንቅ እንቅስቃሴ እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ኄኖክ ታደሰ ለውሃ ስፖርት ግብ አስቆጥሮ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ ከእረፍት መልስ ዮሴፍ በቀለ ግብ አስቆጥሮ ውሃ ስፖርትን ባለድል አድርጓል፡፡
ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን መድንን በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አስመዝግቧል፡፡ ደብረብርሃን ላይ በተደረገው ጨዋታ የሰሜን ሸዋን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው እሱባለው አንለይ ነው፡፡
ከዚህ ምድብ በዚህ ሳምንት ግብ ያልተቆጠረበት ብቸኛ ጨዋታ የሆነው ጨዋታ በአክሱም ተካሂዶ አክሱም ከተማ ከአማራ ውሃ ስራ ካለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡
የምድብ ሀ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-
ፎቶ – ከላይ ውሃ ስፖርት ከታች ፋሲል ከተማ