ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ወልዋሎ በትግራይ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኋላ በተጫዋቾች ጉዳት እና ሌሎች ምክንያቶች ተከታታይ ነጥብ ጥለው በውጤት ማጣት ላይ የሚገኙ ወልዋሎዎች ከመሪዎቹ ላለመራቅ ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ ተሸነፈ

 

በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ውጤታማ የማጥቃት ጥምረት ፈጥረው በርካታ ግቦች ማስቆጠር ችለው የነበሩት ወልዋሎዎች ባለፉት ጨዋታዎች የሚከተሉት የረጃጅም ኳስ አጨዋወት ውጤታማ ሊያደርጋቸው አልቻለም። አጨዋወታቸው በተጋጣሚ ቡድኖች ተገማች ከመሆኑ አልፎ ለአጨዋወቱ የሚሆኑ የ50/50 ኳስ ማሸነፍ የሚችሉ ተጫዋቾች አለመያዛቸውም ለአጨዋወቱ አለመሳካት እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል።

በመጀመርያዎች ጨዋታዎች በካርሎስ ዳምጠው ተገጭተው በሚወርዱ ሁለተኛ ኳሶች አጨዋወቱን ለመተግበር ጥረት ያደረጉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተጫዋቹ በጉዳት በማጣቸው ምክንያት ቀጥታ ወደ ሳጥን በሚሻሙ ረጃጅም ኳሶች አጨዋወቱን ለመተግበር ቢሞክሩም አስፈሪው ጥምረት መመለስ አልቻሉም።

አሰልጣኙ በዚህ ጨዋታም የማይቀየረው የረጃጅም ኳስ አጨዋወት ይዘው ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ የተጋጣሚን አጨዋወት ለመግታትም እንደተለመደው ያልተጠበቀ የቅርፅ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።

ወልዋሎዎች ዓይናለም ኃይሉ እና ካርሎስ ዳምጠውን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ

በተሸነፉባቸው ጨዋታዎች ጭምር ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ከጨዋታ ጨዋታ ማሻሻሎች እያሳዩ የሚገኙት ቡናማዎቹ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ደረጃቸው ላይ ለውጥ ስለሚያመጣ ከዚ ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣትን አልመው ይገባሉ።
እስካሁን በሊጉ ላይ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ለመጫወት ያልተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይም ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ አጨዋወቱን ተግብረውታል። በነገው ጨዋታም ተጋጣሚያቸው ወልዋሎ በባለጋራ ሜዳ ተጭቶ ይጫወታል ተብሎ ስለማይታሰብ ኳስን መስርቶ ለመጫወት ይቸገራሉ ተብሎ አይታሰብም። በአንፃሩ ቡድኑ ወደ ራሱ ሳጥን ተጠግቶ እና ክፍተት ሳይሰጥ የሚከላከለውን ወልዋሎ ላይ የግብ ዕድል ለመፍጠር ፈተናው ቀላል አይሆንለትም።

በሜዳቸው ባደረጋቸው ጨዋታዎች አልፎ አልፎ ከአጨዋወታቸው በመውጣት በቀጥተኛ ኳሶች የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ የታዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጫወቻ ሜዳው አመቺነት እና ስፋት አንፃር ምቹ ሁኔታዎች ስላሏቸው በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ እንቅስቃሴዎች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በጨዋታውም ቡናዎች ከመሀል ሜዳ ይልቅ በባለጋራ ሜዳ ያለው ፈተና በብቃት ማለፍ ከጨዋታው ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ያስችላቸዋል።

በቡና በኩል በቅጣት አቤል ከበደ የማይኖር ሲሆን ጉዳት ላይ የሚገኘው አቡበከር ናስርም ጨዋታው ያልፈዋል። በአንፃሩ ተመስገን ካስትሮ ከረጅም ወራት ጉዳቱ አገግሞ ከቡድኑ ጋር መጓዝ ችሏል።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአራት ጊዜያት ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና 3 በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ወልዋሎ ድል አስመዝግቧል። ቡና 4 ሲያስቆጥር ወልዋሎ 2 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ

ምስጋናው ወ/ዮሐንስ – ሳሙኤል ዮሐንስ – ገናናው ረጋሳ – ሄኖክ መርሹ

ፍቃዱ ደነቀ – አቼምፖንግ አሞስ

ብሩክ ሰሙ – ሚካኤል ለማ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

አስራት ቱንጆ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አሕመድ ረሺድ

አማኑኤል ዮሐንስ – ዓለምአንተ ካሣ – ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን

ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – ሀብታሙ ታደሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ