ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፫) | አሰልጣኞች ትኩረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አንደኛ ሳምንትን የተመለከቱ አሰልጣኞች ተኮር ጉዳዮችን እነሆ!
* ጀብደኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አመስጋኙ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቨ

በ11ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጠባቂው የሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በሀገራችን አውድ በንፅፅር የተሻለ የፕሬሲንግ አጨዋወትን አስመልክተዋል። ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ወቅት አንስቶ እየገነቡት የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የሚያስችል በቂ የማጥቃት አማራጭ የሌለው በተቃራኒው ለደህንነቱ አብዝቶ የሚጠንቀቅ ቡድን በመሆኑ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ጫና በርክቶባቸው ሰንብቷል። ረቡዕ የተመለከትነው ቡድን ግን ግምቶቾን ባፋለሰ መልኩ በጀብደኝነት ፕሬስ የሚያደርግ መሀል ለመሀልም ሆነ በቀጥተኛ አጨዋወት ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ሆኖ ተመልክተነዋል ፤ ይህም አጨዋወት በሂደት የሚቀጥል ከሆነ ቡድኑ ወደ ተሻለ የውጤት መንግድ ይመራዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተው የነበሩትን የክለቡ ተጫዋቾችን ዳግም ከመልበሻ ቤት እንዲወጡ ማድረግ በስታዲየሙ ተገኝተው ድጋፍ ሲሰጧቸው ለነበሩ የክለቡ ደጋፊዎች ዳግም ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደረጉት መንገድ ከሰሞኑ ተቃውሞ ላይ ለሰነበቱት አሰልጣኝ ይበልጥ መነሳሳት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

* “ተሸንፎ ሚዲያዎችን መሸሽ” ሊቀረፍ ያልቻለው የአሰልጣኞች ልማድ

በዚህ ሳምንት ከተደረጉት ጨዋታዎች መካከል አዳማ ከተማ በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፈበት እንዲሁም ወልዋሎ በሲዳማ በሰፊ ውጤት ከተረታበት ጨዋታ ተከትሎ የሁለቱ ተሸናፊ ቡድን አሰልጣኞች ለመገናኛ ብዙሃን ሀሳባቸውን ለማጋራት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

እስካሁን አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ያልተበጀለት የድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቅ በአሰልጣኞች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።

* ምክንያት ከመደርደር ነፃ የሆነው ካሳዬ አራጌ

በመጀመሪያው አጋማሽ በባከኑ እድሎች ነጥብ ጥለናል ብለው ያምኑ ይሆን ተብለው የተጠየቁት አሰልጣኝ ካሳዬ ሰበብ በመደርደር ለተካኑ አንዳንድ የሀገራችን አሰልጣኞች ጠቃሚ መልዕክት አስተላልፏል።

” ጨዋታው እስከሚጠናቀቅበት 90ኛው ደቃቃ ድረስ ጎል የማስቆጠር እድል አለህ። የግድ የመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ላይ አይደለም ግብ ማስቆጠር የነበረብን። የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀው 0-0 ነው። ስለዚህ በሁለተኛው አጋማሽ እድሉ ነበረን። በመጀመሪያ አጋማሽ ብንመራ እንኳን በሁለተኛው እድሉ ነበር። ስለዚህ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከኑት ኳሶች ምክንያት አይሆኑም፤ ምክንያቱም 90 ደቂቃ እስኪያልቅ እድሉ ስላለ ።”

* ስለ ዳኝነት ቅሬታ

የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በመቐለ ከተሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በአጠቃላይ ስለ ጨዋታው ሒደትና ተፈፀመ ስላሉት የዳኝነት በደል ይህንን ብለዋል

“የተጫወትነው ሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ ጋር ነው። ከሜዳው እና ከደጋፊው እንደመጫወቱ መጠን ትንሽ ጠንካራ እንደሚሆን ገምተን ነበር። ነገር ግን ይዘነው የገባነው መንገድ መተግበር በማንችለበት ሁኔታ በተጀመረ በአስራ ሶስተኛ ደቂቃ ላይ ተጫዋቻችን በቀይ ካርድ በመውጣቱ የተለየ ነገር መስራት አልቻልንም። ዳኛው ጠቅላላ መንፈሱ ስለረበሸው እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። ዳኛው ሳያየው ረዳት ዳኛው በነገረው ነው የወሰነው።”

* ስለ ጫና

የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ቡድኑ ድቻን በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ቢያሸንፍም ቡድን ጫና ውስጥ ስለመሆኑ ይናገራሉ

“ይሄን አጨዋወት የጀመርነው በዚህ ጨዋታ አይደለም። አዲስ አበባ ከሰበታ ጋር ስንጫወት ከእረፍት በኃላ ያደረግነው እሱን ነው። በዛ ጨዋታ ከእረፍት በኃላ የነበረው ቡድን ነው የገባው። ዛሬ ያየነውም እሱን ነገር ነው፡፡ የተሻለ ነገር ነው፡፡ በይበልጥ በራስ መተማመን ስትጨምር እንደዚህ አይነህ አጨዋወት ይኖራል፡፡ ግን አሁን የጫናው ነገር በጣም ከባድ ነው። ከውጪ ያለው ነገር ይከብዳል። ተጫዋቹንም ከመስመር ያወጣዋል። ምን ያህል ተቋቁመን እንጫወታለን የሚለው ነገር ነው እንጂ ተጫዋቾቹ ጥሩ ናቸው፡፡

* ስለ ስታዲየም ነውጥ

ወልቂጤ ከተማ ከሜዳው ውጪ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታበት ጨዋታ በኃላ የወልቂጤው አሰልጣኝ ድግአረግ ይግዛው በስታዲየሙ ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል።

“ጨዋታው ላይ ግብ ከተቆጠረ በኋላ ድንጋይ ውርወራ ነበር። በዚህም ረዳቴ ተመቷል፤ እኛም ወደሜዳ ገብተን ነው የተርፍነው። መጨረሻ ላይ የተፈጠረው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። ወደ አላስፈላጊ ድርጊት ነበር ያመራው። ልዩ ኃይሉ ባይቆጣጠረው እንዲሁም የቡድኑ (ሆሳዕና) አመራሮች እርዳታ ባይደርጉ ኖሮ ችግር ይባስ ነበር። በዚሁ አጋጣሚ የሆሳዕና ወጌሻ የሆነው አቶ ቢንያም ያደረገው መልካም ተግባር በኔም በቡድኔም እንዲሁ በወልቂጤ ደጋፊ ሥም አመስግናለው።”

* የዮሐንስ ሳሕሌ ስታዲየም አለመገኘት

የወልዋሎ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በዲሲፕሊን ኮሚቴ በተላለፈባቸው ቅጣት ምክንያት ትላንት ወልዋሎ በሲዳማ ቡና 5ለ0 ሲረታ በሜዳ ላይ አልተገኙም ነበር። አሰልጣኝ ዮሐንስ ከሰሞኑ ሀዋሳ ላይ ቡድኑን ይዘው ልምምድ ሲያሰሩ የነበረ ሲሆን ትላንት ከጨዋታው በፊት ፕሪማች ላይ ለተጫዋቾቹ መመሪያ ሰጥተው አሰላለፍ ካወጡ በኋላ ቡድኑ ሲዳማ ቡናን ሊገጥም ወደ ሜዳ ሲጓዝ አሰልጣኙ ወደ ሆቴል አምርተው ጨዋታውን ግን አለመከታተላቸው ታውቋል። አንድ አሰልጣኝ ቅጣት ሲተላለፍበት ሊመራ ከሚችልበት ቴክኒክ ቦታ ላይ አለመገኘትን መገደብ ሆኖ ሳለ በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን በመከታተል ለቀጣይ ቡድኑን ማዘጋጃ ግብዓት መውሰድ እና በሕግ የተፈቀዱ ተግባራትን መከወን አለመቻላቸው አግራሞትን ያጫረ ሆኗል።

© ሶከር ኢትዮጵያ