ሪፖርት | ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቡሩንዲን ጥሎ ወደ ቀጣይ ዙር አለፈ

ፓናማ እና ኮስታሪካ በጣምራ ለሚያዘጋጁት የ2020 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ዛሬ ያከናወነው ቡድኑ ቡሩንዲን 2-1 በድምሩ ደግሞ 7-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር አልፏል።

በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት በመከተል ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ጫና መፍጠር ጀምሯል። በዚህም ቡድኑ በ7ኛው ደቂቃ ወደ ቡሩንዲዎች የግብ ክልል ሲያመራ የተገኘን የቅጣት ምት ቤቲ ዘውዴ ወደ ግብ መትታ ለጥቂት ወጥቶባታል። በተመሳሳይ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም የተገኘን የቅጣት ምት በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው አረጋሽ ከልሳ ወደ ግብ መትታ ግብ ጠባቂዋ አምክናባታለች። ከእነዚህ ሁለት የቅጣት ምቶች በተጨማሪ ቡድኑ በ17ኛው ደቂቃ በምርቃት ፈለቀ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ለማድረግ ጥሮ ግብ ጠባቂዋ ኢራኮዝ ጂያኒኒ የግብ ክልሏን ለቃ በመውጣት አፅድታዋለች።

የግብ ክልላቸውን መጠበቅ ላይ ተጠምደው የዋሉት ቡሩንዲዎች እስከ 20ኛው ደቂቃ ምንም ሙከራ ሳያደርጉ ዘልቀዋል። በዚህ ደቂቃም የተገኘን የቅጣት ምት ማኒሺሚዊ ኢቭሊኒ ለማስቆጠር ሞክራ አባይነሽ ኤርቄሎ አምክናባታለች። ግብ ማስቆጠር እጅግ ፈልገው የነበሩት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህም በ22ኛው ደቂቃ ቡድኑ በረድኤት አማካኝነት ጥሩ ኳስ ወደ ጎል ሞክሮ ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላም ምርቃት የቡሩንዲ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅም ወደ ግብ ደርሳ ነበር። 

ፍፁም የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያዎች በ27ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። በቀኝ መስመር የተሰለፈችው ሥራ ይርዳው ከመስመር የተቀበለችውን ኳስ በጥሩ ብቃት ወደ ግብነት ቀይራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ይህ ጎል ይበልጥ ያነሳሳቸው ባለሜዳዎቹ ከሶስት ደቂቃ በኋላም ተጨማሪ ጎል አስቆጥረዋል። በቡሩንዲ የግብ ክልል አካባቢ የተገኘን የቅጣት ምት አረጋሽ ከልሳ በድንቅ አመታት አስቆጥራለች።

በአጋማሹ ቀሪ ደቂቃዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን የገቱት የፍሬው ተጨዋቾች ኳስ ለመቆጣጠር ሞክረዋል። በተቃራኒው ሲሰነዘርባቸው የነበሩት ጥቃቶች ለጊዜውም ቢሆን ጋብ ያለላቸው ቡሩንዲዎች በ49ኛው እና በ42ኛው ደቂቃ በተገኘ የቆመ ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። ነገር ግን ቡድኑ ፍሬያማ ሳይሆን አጋማሹ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን መሪነት ተጠናቋል።

ብዙም የግብ ሙከራዎች (ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር) ያልተስተናገዱበት የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ10ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምት ግብ አስተናግዷል። ረጃጅም ኳሶችን በመስመር በኩል በመላክ ጥቃቶችን ለማድረግ የጣሩት ተጋባዦቹ ቡሩንዲዎች ያገኙትን የቅጣት ምት በዴቪን ኒሆሪንበሪ አማካኝነት አስቆጥረዋል። 

ይህንን ግብ ያስተናገዱት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በመጠኑ ለመረጋጋት ተስኗቸው የተዘበራረቀ አጨዋወት መተግበር ጀምረዋል። ነገር ግን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው በቶሎ ተጨዋቾችን በመቀየር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥሯል።
ኢትዮጵያዎች ግቡን ካስተናገዱ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በተሻገረ የመዓዘን ምት ግብ ለማስቆጠር ጥረው መክኖባቸዋል። በተለይ ረድኤትን ቀይራ የገባችው ዮርዳኖስ መስመሮችን በመቀያየር የምታደርገው እንቅስቃሴ በመጠኑ ቡሩንዲዎችን ሲፈትን ታይቷል። ይህቺው ተጨዋች በ74ኛው ደቂቃ የተሻገረን የመዓዘን ምት ለማስቆጠር ጥራ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባታል። ከዚህ በተጨማሪ ሌላኛዋ ተቀይራ የገባችው ሲሳይ ከሥራ የተቀበለችውን ኳስ አክርራ መትታ የቡድኗን መሪነት ከፍ ለማድረግ ሞክራለች።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በመስመር ላይ አጨዋወት ጨዋታውን የቀጠሉት ተጋባዦቹ አቻ ለመሆን ጥረቶችን አጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህም በ82ኛው ደቂቃ የምስራች ከግራ መስመር የተገኘን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ መትታ ወጥቶባታል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል በቀኝ መስመር በመገለዝ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርጓል። በተቃራኒው ቀስ በቀስ እየተዳከሙ የመጡት ኢትዮጵያዎች በ89ኛው እና በተጨመረው 3 ደቂቃ በምስራች እና በነፃነት አማካኝነት ለግብነት የቀረበ ጥቃት ሰንዝረዋል።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። 7-1 በሆነ የድምር ውጤት ወደ ቀጣይ ዙር ያለፈው ቡድኑ በቀጣይ የዙምባቤ አቻውን ይገጥማል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

error: