ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ መቐለ 70 እንደርታን ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ከተማን በመርታት ወደ መሪነቱ ተመልሷል።

መቐለ ላይ የተደረገው የመቐለ 70 እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በእንግዶቹ 4-2 የበላይነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የጨዋታው የመጀመርያ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ረጃጅም ኳሶች ምርጫቸው አድርገው ነበር የገቡ ሲሆን ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ባለሜማዎቹ ናቸው። በአምስተኛው ደቂቃም ባለሜዳዎቹ መቐለ በዮርዳኖስ ምዑዝ አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል።

ከግቡ በኃላ ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዩት እንግዶቹ ሀዋሳዎች በዘጠነኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል። መሳይ ተመስገን የተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅማ አምልጣ በመግባት ግብ አስቆጥራ ቡድኗን አቻ ማድረግ ችላለች። ከግቡ በኃላ ፍፁም ብልጫ የነበራቸው እንግዶቹ በተደጋጋሚ ግዜ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም መሳይ ተመስገን በመልሶ ማጥቃት የተጋጣሚ ተጫዋቾች አምልጣ ሄዳ መታው ተከላካዮች ተረባርበው ወደ ውጭ ያወጧት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። መደበኛ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ደቂቃም ዙፋን ደፈርሻ ከማዕዝን የተሻማው ኳስ በግንባሯ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች።

ጥሩ አጀማመር አድርገው የኃላ ኃላ የተዳከሙት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ሀዋሳ ከተማዎች ግብ ከማስቆጠራቸው በፊት መሪ መሆን የሚችሉበት ዕድል አምክነዋል። አበባ ገብረመድኅን ከመስመር ተሻምቶ የሀዋሳ ተጫዋቾች የጨረፉት ኳስ ከግቡ አፋፍ ላይ አግኝታ ነበር ያልተጠቀመችበት።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የሀዋሳዎች ብልጫ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ እንግዶቹ አጨዋወታቸው ቀይረው ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ሲሆን መቐለዎችን እንደመጀመርያው አጋማሽ በረጃጅም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በአርባ ሰባተኛው ደቂቃም መሳይ ተመስገን ከመጀመርያው ግቧ በተመሳሳይ መንገድ የራሷ ጥረት ታክሎበት ግሩም ግብ በማስቆጠር ለቡድኗ ሥስተኛው ለራሷ ሁለተኛው ግብ አስቆጥራለች።

ሀዋሳዎች ከግቡ በኃላም በኳስ ቁጥጥር ተሽለው በመታየት በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ካሰች ፍስሐ እና ዙፋን ደፈርሻ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በተለይም ዙፋን የደረገቻት ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጣች እንጂ የግብ መጠኑን ከፍ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተዳክመው እና የተጋጣሚን አጥቂዎች ለመቆጣጠር የተቸገሩት መቐለዎች በረጅሙ ወደ ብቸኛ አጥቂዋ ዮርዳኖስ ምዑዝ በሚሻገሩ ኳሶች ከፈጠሯቸው ተጋጠሚን ያላስቸገሩ ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ንፁህ የግብ ዕድሎች አልፈጠሩም። ሆኖም አስካለ ገብረፃድቃን በአንድ አጋጣሚ ያደረገችው ሙከራ ተከላካዮች ተደርበው ባያወጡት ጎል የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነበር።

በጨዋታው መገባደኛ ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች አንዳንድ ግቦች አክለዋል። መቐለዎች በፍፁም ኪሮስ ግብ ሲያስቆጥሩ እንግዶቹ በዓይናለም አሳምነው አማካኝነት አራተኛ ግባቸው አስቆጥረዋል። ፍፁም የተሻማውን ኳስ በግርግር መሀል አግኝታ ስታስቆጥር ዓይናለም ከመሳይ ተመስገን ጋር አንድ ሁለት ተጫውታ ነው ጎሉን ያስቆጠረችው።

ዛሬ በተደረገ ሌላ ጨዋታ በአካዳሚ ሜዳ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ከተማን 2-0 በማሸነፍ መሪነቱን ዳግም ተረክቧል። ትዕግስት ያደታ እና ህይወት ደንጊሶ የንግድ ባንክ የድል ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ