የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2012 የውድድር ዘመን የአንደኛው ዙር ዳሰሳችንን ቀጥለን በዚህ ፅሁፍ ሀዋሳ ከተማን እንመለከታለን፡፡

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደአዲስ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን በሊጉ እየተሳተፈ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ባለፉት አራት ዓመታት በሜዳ ላይ ማራኪ የሆኑ እንቅስቃሴን ቢያሳይም ከውጤት አንፃር ደካማ ጊዜያትን ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡ ዓምና አሰልጣኝ አዲሴ ካሳን ከቀጠረ በኋላ በአንፃሩ በሜዳ ላይ የሚታወቅበት አጨዋወት ቢቀርም በጠንካራ መከላከል እና የመልሶ ማጥቃት ወትሮ ከሚዳክርበት የስጋት ቀጠና ተላቆ በሊጉ መሐል ላይ ሰፍሮ ዓመቱን አገባዷል፡፡ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ በቅድመ ዝግጅት ውድድር ወቅት አዳዲስ ያስፈረማቸውና ከወጢት ቡድን ያሳደጋቸውን ተጫዋቾች አካቶ በአዳማ ከተማ ዋንጫ ላይ ራሱን በመፈተሽና የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ቡድኑ በሊጉም ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በሚመስል መልኩ ወደ ዋናው ውድድር ገብቷል፡፡

ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ሀይቆቹ በሜዳቸው ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ ሦስት ነጥብን በመጨበጥ ዓመቱን በድል ከመጀመራቸው በተጨማሪ በሁለተኛው ሳምንት አዲስ አዳጊው ሀዲያ ሆሳዕናን ከሜዳቸው ውጪ ገጥመው ነጥብ በመጋራት እንዲሁም በሦስተኛው ሳምንት በሜዳቸው ባህር ዳርን 1ለ0 አሸንፈው ድንቅ አጀማመር ማድረግ ቢችሉም በአምስተኛው ሳምንት የሊጉ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በኢትዮጵያ ቡና 4ለ1 ከተሸነፉ በኋላ የወጥነት ችግር በሰፊው ሲንፀባረቅባቸው እና በርካታ ግቦች አስተናግደው ሽንፈት ሲገጥማቸው ተስተውሏል። በዚህም ከቡናው ሽንፈት በኋላ ባሉ አራት ጨዋታዎች ላይ ሦስት አቻ እና አንድ ሽንፈት በማስተናገድ ከጥሩ አጀማመራቸው ለመንሸራተት ተገደዋል።

ቡድኑ በ9ኛው ሳምንት ወልቂጤን 3-1 አሸንፎ ወደ ድል ከተመለሰ በኋላ እስከ አንደኛው ዙር ፍፃሜ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በሜዳው ተቸግሮም ቢሆን የሚያሸንፍ እና ከሜዳው ውጪ በቀላሉ የሚሸነፍ ቡድን ሆኗል። በሜዳው ወላይታ ድቻን በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ሲያሸንፍ ለረጅም ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች የተጫወተው ጅማ አባ ጅፋርን ከከፍተኛ ትግል በኋላ አሸንፏል። ፋሲል ከነማንም 2-0 ከመመራት በማንሰራራት 3-2 መርታት ችሏል። በተቃሳኒው ከሜዳው ውጪ በመቐለ 5-1 እንዲሁም በስሑል ሽረ 3-0 የተሸነፉባቸው ጨዋታዎች የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት አቋማቸውን የሚገልፁ ነበሩ።የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ዓምና ሀዋሳ በዚህ ወቅት ባደረጋቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በሰባቱ አሸንፎ፣ በአምስት ተሸንፎ በሦስቱ አቻ ተለያይቶ 24 ነጥቦችን በመያዝ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር አንደኛውን ዙር ያጠናቀቀው፡፡ ከዓምናው አንፃር በአንድ ደረጃ ዝቅ ያለው ቡድኑ በ2 ነጥቦችም ዝቅ ያለ ሲሆን ጎል በማስቆጠር ረገድም ከዓምናው በ4 ጎሎች ሲቀንሱ የተቆጠረባቸው ጎል በአንፃሩ በ9 ከፍ ያለ ሆኗል። ይህም ቡድኑ የመከላከል ሪከርዱ ከመውረዱ ውጪ ውጤቱ ከዓምናው ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

የቡድኑ አቀራረብ

በየሳምንቱ ግምትን ከሚያፋልሱ የፕሪምየር ሊጉ ቡድኖች መካከል ሀዋሳ አንዱ ነው፡፡ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ቅርፅ እና አቀራረብ የሌለው ሲሆን የተጫዋቾች ምርጫ እና የአደራደር መለዋወጦች የቡድኑ የአንደኛው ዙር መገለጫ ነበር። አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በተደጋጋሚ አሰላለፋቸውን መለዋወጣቸው እንዳለ ሆኖ 4-3-3 / 4-2-3-1 በአመዛኙ ምርጫቸው አድርገው ሲቀርቡ ተስተውሏል። ኳስ የማይቆጣጠር፣ ቀጥተኛ ማጥቃትን ምርጫው ያደረገ ቡድንም ሚዛን ሊደፋ የሚችል የቡድኑ አቀራረብ ነበር። ፈጣን የመስመር ሽግግር በማድረግ በተሻጋሪ ኳሶች የጎል እድሎችን መፍጠር ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ እና ረጃጅም ኳሶች የቡድኑ የአንደኛ ዙር መገለጫ ነበሩ።

በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ ከሌሎች ቡድኖች አንፃር አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ አመዛኝ ስብስባቸውን የተጠቀሙ ሲሆን ተጫዋቾችን በወጥነት ያለመጠቀም እና በተፈጥሯዊ ቦታቸው እንዲጫወቱ አለማድረጋቸው በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው። በዚህም በግብ ጠባቂነት በብቃታቸው መዋዠቅ ምክንያት ቤሊንጋ ኢኖህ እና ሀብቴ ከድር እየተፈራረቁ ግባቸውን የጠበቁ ሲሆን በተከላካይ ሥፍራ የዳንኤል – መሳይ – ላውረንስ – ኦሊቨር ጥምረት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ተጣምረዋል። አክሊሉ ተፈራ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ተስፋዬ መላኩ ደግሞ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ዋነኞቹ ተሰላፊዎች በማይኖሩበት ወቅት ተክተው ተሰልፈዋል።

በየሳምንቱ በሚቀያየረው የአማካይ ክፍለ ጥምረት አለልኝ አዘነ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ሄኖክ ድልቢን የተጠቀሙት አሰልጣኙ አንድ ጊዜ በሦስት ሌላ ጊዜ በሁለት አማካዮች ሲጠቀሙ ይስተዋላል። መስፍን ታፈሰ፣ ብርሀኑ በቀለ እና አክሊሉ ተፈራ ከመስመር እየተነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ብሩክ በየነ በብቸኛ የፊት አጥቂነት አልፎ አልፎም ከሄኖክ አየለ እና የተሻ ግዛው ጋር በመጣመር የውድድር ዓመቱ ተጋምሷል።ጠንካራ ጎን

የቡድኑ ቀጥተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የቡድኑ ጠንካራ ጎኑ ነው። በመስመር በኩል በሚደረጉ ፈጣን ሽግግሮች ተደጋጋሚ የጎል ዕድል የሚፈጥረው ቡድኑ በፊት መስመር ላይ የብሩክ በየነ ብቻ ጥገኛ መሆኑ ከዚህ የበለጠ ጎል እንዳያስቆጥር ገድቦታል። ወደ ቀኝ መስመር ባደላው የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ የመስመር ተከላካዩ ዳንኤል ደርቤ የሚያደርጋቸው የፊት ለፊት ሩጫዎች ዋንኛ የማጥቃት መሳርያ ሲሆኑ ከፊቱ የሚሰለፉት የመስመር ተጫዋቾች በተለይም መስፍን ታፈሰ ወደ ውስጥ አጥብበው በመግባት የሚፈጥሩት አደጋ የሚጠቀስ ነው። የማጥቃት እንቅስቃሴውን በጎል በማጀብ ድንቅ አጋማሽ ያሳለፈው ብሩክ በየነ ከቡድኑ ጠንካራ ጎኖች ጀርባ ሊጠቀስ የሚገባው ነው።

የአማካይ ክፍሉ አንፃራዊ ጥንካሬም አንደኛው ዙር ሊታይ የሚገባው ነው። በተለይም አለልኝ አዘነ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ሄኖክ ድልቢ በሚሰለፉበት ወቅት የቡድኑ የማጥቃት ሽግግርን በመምራትና ኳሶችን በማሰራጨት የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

ሀዋሳ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ዘንድሮም በወጣቶች ላይ ያለው እምነት በመልካም ጎኑ የሚነሳ ነው። ከሞላ ጎደል ከታች ባደጉ ተጫዋቾች የተገነባው ቡድኑ ዘንድሮም ለተባረክ ኢፋሞ እና ፀጋአብ ዮሐንስ የመጫወት እድል ከመስጠቱ ባሻገር አምና ተስፋ ሰጪ ብቃታቸውን ያሳዩት ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ ዘንድሮ ወደ ወሳኝ ተጫዋችነት እንዲሸጋገሩ በር ተከፍቶላቸዋል።

ደካማ ጎን

ቡዱኑ በመጀመሪያው ዙር በርካታ ግቦችን ካስቆጠሩ ክለቦች መካከል ሊጠቀስ ቢችልም የኋላ መስመሩ በቀላሉ ጎሎችን የሚያስተናግድ ነው። ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን እና ተጣማሪዎቹም ያለፈለት ዓመታት በጋራ የተሰለፉ ቢሆኑም ጎሎች በብዛት ማስተናገዱ አስገራሚ ነው። በአማካይ በጨዋታ 1.6 ጎሎች የሚያስተናግደው የኋላ መስመሩ የመስመር ተከላካዮቹ ለማጥቃት ወደፊት በሚያመሩበት ወቅት የሚተዉትን ክፍተት በቶሎ ካለመድፈን እና ኳስ ከእግራቸው ሲወጣ በቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን ካለመያዝ የመነጨ መሰረታዊ ችግር እንዳለ ሆኖ በትኩረት ማጣት እና የደጋፊዎች ተቃውሞ የበረተበት ቤሊንጋ ኢኖህ ተደጋጋሚ ስህተቶች በርካታ ጎሎችን አስተናግደዋል።

ቡድኑ ጥሩ እና ሊሻሻል የሚችል የማጥቃት አጨዋወት ቢኖረውም ጎሎች የማስቆጠር ተግባር ለብሩክ በየነ ብቻ የተተወ መስሏል። በእርግጥ በጉዳት ምክንያት የአጥቂ መስመሩን በአግባቡ መጠቀም ባይችሉም በርካታ አማራጭ ያለው ስብስብ በመሆኑ ለሁለተኛው ዙር ማሻሻል የሚጠበቅባቸው ክፍተት ነው።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ በፊት ቡድኑ የአሰልጣኝ ለውጥን በማድረግ ቀዳሚ ተግባሩ አድርጓል። ከ2011 ክረምት ጀምሮ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ድረስ በአሰልጣኝነት ክለቡን ሲመሩ የነበሩትን አሰልጣኝ አዲሴ ካሳን ከኃላፊነት በማንሳት በክለቡ ከዚህ ቀደም መጫወት የቻለውና ባለፉት አራት ዓመታት ከሴቶች ቡድን አንስቶ ከ17 እና 20 ዓመት ቡድኖች ውስጥ ቆይታ የነበረው ብርሀኑ ወርቁን ጊዜያዊ አሰልጣኝ በማድረግ ሾሟል፡፡ አሰልጣኙ የተበታተነውን የቡደኑን ትኩረት ወደ አንድ በማምጣት ወጥ የሆነ ውጤት እንዲያስመዘግብ መርዳት የመጀመርያ ተግባሩ እንደሚሆን ሲጠበቅ አለልኝ አዘነን በቅጣት የሚያጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአማካይ ክፍሉን መዋቅር እንደ አዲስ ማደራጀትና የኋላ መስመሩን ተጋላጭነት መቀነስ የአሰልጣኙ ቀጣይ ስራዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የመጀመሪያው ዙር ኮከብ ተጫዋች

ብሩክ በየነ፡ ለቡድኑ በዚህ ስፍራ ላይ መገኘት ግንባር ቀደሙን ድርሻ የሚወስደው ይህ ወጣት አጥቂ ነው። ቡድኑ ካስቆጠራቸው ግቦች ግማሹን ያስቆጠረው ብሩክ በተክለ ሰውነቱ ዓይን ውስጥ ባይገባም በተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆነ ተጫዋች ነው። 9 ጎሎችን በሊጉ ያስቆጠረው ብሩክ አራት ጎል የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸትም ከአጠቃላይ 18 ጎሎች በአስራ ሁለቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ፀጋአብ ዮሐንስ፡ ከ17 ዓመት በታች እስከ 20 ዓመት በታች ቡድን በመሐል ተከላካይነት እና አምበልነት ተጫውቷል፡፡ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካቶም ድንቅ ብቃቱን ካሳየ በኋላ ነበር ወደ ሀዋሳ ዋናው ቡድን ያደገው። ተጫዋቹ በዋናው ቡድን ምንም እንኳን ወጥ የሆነ የመሰለፍ ዕድሎችን ባያገኝም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ተስፋ ሰጪ አቅሙን ማሳየት ችሏል። አቅሙን እያሳደገ ከመጣም ዘንድሮ ለሳሳው የተከላካይ መስመር መፍትሄ እንደሚሆን ተስፋ የሚጣልበት ነው።

©ሶከር ኢትዮጵያ