የሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ወግ – በኤርሚያስ ብርሀነ

የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ብሄራዊ ቡድናችን ደቡብ አፍሪካ ላይ ተዘጋጅቶ ለነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ ተደጋግሞ ሲሰማ የነበረው ንግግር “ሃገራችን- ኢትዮጵያ ከሰላሣ አንድ ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ተመለሰች!” የሚል ነበር፡፡ ይህ ጽሁፍ በ1974 ዓ.ም ሊቢያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሃገራችን ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ባስቻለው ያ-ጀግና ቡድን ዙሪያ ያውጠነጥናል፡፡  ከዚህ ታላቅ ቡድን ጋር በተያያዘ ያሳለፍኩትን የራሴን ገጠመኝና ትውስታዬን መፃፍ ፈልጌ ይኸው እንዲህ አሰናድቼዋለሁ፡፡

ባለፈው ሳምንት ትዝታዬን ሳካፍላችሁ ” 1973 ዓ.ም- እግር ኳሳችን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡” ብያችኋለሁ፡፡ ይህን ያልኩበትን ምክንያት በዚህኛው ጽሁፌ ለማሳየት እሞክራለሁ። በእርግጥ ዛሬ የፃፍኩት ስለ እያንዳንዱ ተጫዋች እና ስለጨዋታዎቹ ሳይሆን በጨዋታው ዙርያ ስለተከሰቱት ኹነቶች እና ገጠመኞቼ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ጽሁፉ ዘለግ ሊል ችሏል፡፡ በጣም የሚረዝምባችሁ ከሆነ እለፉት፤ የወደዳችሁት ደግሞ እስከ መጨረሻ አንብቡት። እኔ የፃፍኩት በሙሉ ከኳስ ጨዋታዎቹ ጋር የተያያዘውን ነገር ብቻ ነው፡፡ የዛሬው ትዝታዬን  ከዚህኛው ትውልድ የቅርብ ጊዜ ጣፋጭ ትውስታ ጋር ስለማገናኘው፣ ወጣቶቹም እንዲሁ የተመለከቱት ጨዋታ ስላለ፣ እነርሱም ትዝታቸውንና ልምዳቸውን ቢያካፍሉን ደስ ይለኛል።

በነገራችን ላይ ይህን ጽሁፍ የጻፍኩበት ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም አሉኝ፡፡ የመጀመሪያው ደስ የሚለውን የኳስ እና የስታዲየም ትዝታዬን መለስ ብዬ ለማየት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌሎችም የራሳቸውን ትዝታ መለስ ብለው እንዲቃኙ ለመኮርኮር ማድረግም ሌላኛው ምክንያቴ ይሆናል፡፡ ሦስተኛውና ዋነኛው ደግሞ
በትንሽ ወይም ያለምንም ክፍያ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉት ምርጦቹ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች ታሪካቸው በደንብ የተነገረ አይመስለኝም፡፡ የመጻፍ ችሎታ ያለው፣ የእግር ኳሳችንን ታሪክ በደንብ የሚያውቅ አካል ይሄን ፅሁፍ አይቶ የቀደሙትን ጀግኖች ኳስ ተጫዋቾቻንን ታሪክ በተሻለ መንገድ እንዲፅፈው ለማነሳሳት ይሆናል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾቻችን እኮ በጣም ብዙ ታሪክ አላቸው!  አንድ ምሳሌ ልስጥ፡፡ ከተጫዋች ተጫዋች መለየቴ አይደለም እንደው ድንገት ስለመጣልኝ ነው፡፡ ሙሉዓለም እጅጉ የሚገርም ተጫዋች ነበር፡፡ በተለያዩ የክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚነገር ታሪክ ሰርቷል፤ በአስገራሚ ብቃት እግርኳስን ለረጅም ጊዜ ተጫውቷል፡፡ ለአብነት ያህል በ1973 ዓ.ም ንጉሴ ገብሬ ሩዋንዳ ላይ፣ 1974 ዓ.ም መሐመድ ኡስማን (ሚግ) ጊኒ ላይ፣ 1980 ዓ.ም ገብረመድህን ሃይሌ ዚምባብዌ ላይ ላስቆሯቸው ወሳኝ ግቦች አመቻችቶ ያቀበለው (Assist-ያደረገው) እርሱ ነው፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች ቡድናችን አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ያስቻሉት ጎሎች ሲቆጠሩ ምርጥና የተሳኩ ተሻጋሪ ቅብብሎችን በመከወን (Cross-በማድረግ) ትልቁን ድርሻ የተወጣው ሙሉዓለም እጅጉ ነው፡፡ ያ ታሪክ በደንብ የተነገረ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም የመጻፍ አቅሙ ያላችሁ፣ የእግር ኳሳችንን ታሪክ የምታውቁና ዋናዎቹ የታሪኮቻችሁ ባለቤቶች የሆናችሁ- ተጫዋቾቻችን ስለ ቀደመው ትዝታችሁ እንድትነግሩንና እንድትፅፉልን ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡

በ1974 ዓ.ም ሊቢያ ላይ በሚደረገው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በማጣሪያ ጨዋታ  ሩዋንዳን መግጠም ነበረብን። በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ቡድናችን በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ 1-0 አሸነፈ- የገባው ጎል መጠን ቢያንስም የሚገርም ኳስ ታይቷል፡፡ አንድ ነገር ስለ ቡድናችን የምመሰክረው በዚያን ወቅት በኳስ ስንበለጥ አይቼ አለማወቄን ይሆናል- በተለይ ሜዳችን ላይ! በአዲስ አበባው ጨዋታ ማራኪ የኳስ እንቅስቃሴ አይተን፣ ከእረፍት መልስ ከሙሉዓለም የተላከለትን የተመጠነ ተሻጋሪ ኳስ (Cross) ንጉሴ ገብሬ በሚገርም ሁኔታ በግምባሩ ገጭቶ ቡድናችንን አሸናፊ ያደረገችውን ጎል አገባ ። በነገራችን ላይ ሩዋንዳ ያኔ ጠንካራ ቡድን ነበር፡፡ የእኛ ቡድን ደግሞ በርካታ የእግርኳስ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾችን ያካተተና የበለጠ ጠንካራ ቡድን ነበር፡፡ ይህን ሩዋንዳም ሄዶ የመልሱን ጨዋታ አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፍ አስመስክሯል፡፡ ውጤቱን በትክክል ባላስታውስም- ሩዋንዳ በሜዳው 1-0 አሸንፎን በአምስት-አምስት ፍፁም ቅጣት ምት ቡድናችን ረቶ እንዳለፈ ትዝ ይለኛል፡፡ (ከተሳሳትኩ ከእኔ በተሻለ የሚያስታውሱ ስላሉ ቢያርሙኝ ደስ ይለኛል፡፡)

ሩዋንዳን ካለፍን በኋላ ቀጣይ ተጋጣሚያችን ጊኒ ሆነች። በዚያን ጊዜ ጊኒ ከአፍሪካ ጠንካራ ከሚባሉት ቡድኖች አንዷ ነበረች። ከጨዋታው በፊት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የጊኒን ተጫዋቾች ታሪክ ይዞ ወጣ። ብዙዎቹ በፈረንሳይና እና በሌሎች ትልልቅ ሊጎች የሚጫወቱ ነበሩ። በገናና ክለቦች ይጫወቱ ስለነበሩ የጊኒ ተጫዋቾች መስማት ለእኛ ለደጋፊዎቹ ትንሽ ጭንቀት ፈጠረብን። አዲስ ዘመን ጋዜጣ የጊኒን ተጨዋቾች ማስተዋወቁ ጥሩ ቢሆንም እነርሱን ብቻ ሰማይ-ሰቅለውው ስለ እኛ ቡድን አለማንሳታቸው በተመልካቾች ላይ ፍርሃት ቢያሳድርም በተጫዋቾቻችን ላይ ግን ቁጭት ሳይፈጥር እንዳልቀረ መገመት ከባድ አልነበረም።

እንደማይደርስ የለምና የጨዋታው ጊዜ ደርሶ ቡድናችን ወደ ጊኒ ተጓዘ። ጨዋታውንም በሬዲዮ ለማስተላለፍ ደምሴ ዳምጤ (ይመስለኛል) ከቡድኑ ጋር አብሮ ሄደ። ጨዋታው እሁድ ዕለት ወደ አመሻሹ አካባቢ እንዲካሄድ ጊዜ ተቆርጦለታል፡፡ የቡድናችንን ጨዋታ ለመስማት ሁላችንም ሬዲዮናችንን ከበን ተቀመጥን።  የጨዋታው ሰዓት ቢደርስም ኢትዮጵያ ሬዲዮ ግን በቀጥታ ሥርጭት ጨዋታውን ሊያስተላልፍ አልቻለም-ብዙ ጠበቅን፡፡ በመጨረሻም በቴክኒክ ችግር ምክንያት ጨዋታውን በቀጥታ ማስተላለፍ እንዳልቻሉ አረዱን። ጊዜው መሽቶ ስለነበረ የቡድናችንን ውጤት ለመስማት እስከ ጠዋት መጠበቅ ግድ ሆነብን፡፡ በማለዳ ዜና ላይ “የኢትዮጵያ ቡድን አቻው ከጊኒ ጋር 2-2 ተለያየ፡፡” የሚለውን ዜና ስሰማ ማመን ነው ያቃተኝ። ቡድናችንን ባውቀውም፣ ከጨዋታቸው አልፎ ልምምዳቸውን ሁሉ ብከታተልም ያ አዲስ ዘመን ላይ ስለ ጊኒ ተጫዋቾች ያነበብኩት ችሎታ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮብኝ እንደ ብዙዎች ሁሉ እኔንም ሃሳብ ውስጥ ከቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ጀግኖቹ ተጫዋቾቻችን ያን የመሰለ ድል ስላስመዘገቡ ደስታም ኩራትም ተሰማኝ። ቡድናችን ጊኒ ድረስ ሄዶ እንደዚያ ዓይነት ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡ ትልቅ ቡድን እየተፈጠረ እንደነበር የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ታዲያ እኔም ይሄን ድል አድራጊ ብሄራዊ ቡድን ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝቼ መቀበል እንዳለብኝ ተሰማኝና ከጓደኞቼ ጋር ተነጋግረን ወደዚያው ለመሄድ ተስማማን፡፡ በማግስቱ አብረውኝ ቦሌ መሄድ የቻሉት ጓደኞቼ ሰለሞን በርሄ እና ዮናስ ወ/ገብርኤል ነበሩ፡፡ በማዳው ከእነርሱ ጋር ለገሃር ተገናኝተን 42-ቁጥር አውቶቡስ ተሳፍረን ቀጥታ ቦሌ ደረስን። ነገር ግን በቦታው ስንደርስ ገና ንጋት ስለሆነ መሰለኝ ብዙም ሰው አልተገኘም ነበር። እየቆየ ግን ብሔራዊ ብድናችንን ለመቀበል የሚተም ህዝብ መምጣት ጀመረ፡፡ እኛም መመልከቻ ሰገነቱ ላይ ሆነን ቡድናችንን ይዛ የምትጣውን አውሮፕላን ብዙ ጠበቅን፡፡ ከጉጉታችን ብዛት አውሮፕላን ባረፈ ቁጥር “ይኼኛው ነው-ይኼኛው ነው፡፡” እያልን ሰዓቱን ገፋነው፡፡ በኋላ ግን አንድ ዜና ሰማን፤ የተጫዋቾቻችን መምጫ ሰዓት ለውጥ እንደተረገበትና ከሰዓት በኋላ ወደ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ እንደሚደርሱ ሲነገረን በነገሩ ትንሽ ቅር ተሰኘኝ፡፡ በዕለቱ የምሳችን ነገር አሳሳቢ ሆነብን (በእያንዳንዳችን ኪስ የነበረው  የአውቶቡስ መሳፈሪያ 15-ሳንቲም ብቻ ነበር። ስለዚህም በጠቅላላው ሦስታችን ኪስ ውስጥ  የተገኘው 45-ሳንቲም ያው ለሁላችንም የአውቶቡስ ትራንስፖርት ክፍያ ከመሆን ውጪ ለምንም አይበቃንም ነበር፡፡) እንዲያም ሆኖ የብሔራዊ ቡድናችን ውጤት አስገራሚ ነበርና ምንም ያህል መጠበቅ ቢኖርብን እዚያው ቆይተን ለመቀበል ወሰንን፡፡ በውሳኔያችንን ተስማምተን ብዙም ሳንቆይ እኔ የማውቀውን ሰው አየሁና ሰላምታ ላቀርብ ወደ እርሳቸው ሄድኩ። እኚህ ሰው በዚያን ጊዜ የአውራ ጎዳና ባለስልጣንና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ቀለታ ተስፋሚካኤል ነበሩ። እግርኳስ በጣም ይወዱ ነበርና ከአራት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ነበር እንደኛው ቡድናችንን ሊቀበሉ የመጡት ። ሰላም ካልኳቸው በኋላ የቡድናችን መምጫ ሰዓት እንደተቀየረና እሳቸውም ወደ ሥራ ሊመለሱ ስለሆነ እኔንም ወደቤቴ እንደሚያደርሱኝ ነገሩኝ። ምርጫዬ ከጓኞቼ ጋር መቆየትና ቡድናችንን መቀበል ቢሆንም እሳቸው ያሉትን እምቢ ላለማለት እየከፋኝም ቢሆን አብሬያቸው ወደ ቤቴ ተመለስኩ፤ እርሳቸውም ቤቴ አደረሱኝ።

የዚያኑ ቀን- አመሻሹ አካባቢ ከቤታችን ደጃፍ አቅራቢያ የትግል ፍሬ ቡድን ባለስልጣናት ቢሯቸው ፊት ለፊት ቆመው ሲያወሩ አየሁና መንገዱን ተሻግሬ ወደ እነርሱ ጠጋ አልሁ። ፊታቸው ላይ የመከፋት ስሜት ይታያል። “ምን ሆናችሁ ነው?” ብዬ መጠየቁን ድፍረት ይሆንብኛል በሚል ስጋት ተውኩት። እዚያው ጥቂት ጊዜ እንደቆምሁ ጋሽ ልዑልሰገድ (የትግል ፍሬ ምክትል-ቡድን መሪ ) ለብሄራዊ ቡድን ተመርጠው የነበሩት አራቱ የትግል ፍሬ ተጫዋቾች ሸዋንግዛው ተረፈ፣ ዳዊት ኃይለአብ፣ አቦነህ ማሞ እና ንጉሴ አስፋው ከቡድኑ ጋር እንዳልመጡና እዚያው ጊኒ እንደቀሩ ሲነገሩኝ ክው አልሁ፡፡ ይህን መርዶ መሳይ ዜና ስሰማ እንዴት እንደነገጥኩ እና ምንያህል እንዳዘንኩ መቼም አልረሳውም። ከዚያም ወደ ሰፈር ወጣ አልሁና ጠዋት አብረውኝ ቦሌ የሄዱት ጓደኞቼን ሳገኝ ሌሎች ሦስት ተጫዋቾችም ከጊኒ እንዳልተመለሱ ነገሩኝ። እነዚህም ተጫዋቾች አፈወርቅ ጠናጋሻው ፣ ግርማ ከበደ እና አያሌው ሞገስ ነበሩ። የብሔራዊ ቡድናችንን ውጤት ሰምተን ከሰኞ ማለዳ ጀምሮ በደስታ የቆየነው ልጆች በሰባቱ ተጫዎቾቻችን ወደ ሃገራችን አለመመለስ አዘንን። ከሁሉም በላይ የእኔ ሃዘን ከፋ፤ ምክኒያቱም አራት ምርጥ ተጫዋቾቹን ያጣው እንደ ነፍሴ የምወደው ትግል ፍሬ ነበር፡፡ ቡድኔ እነዚህን ሁሉ ከዋክብት ተጫዋቾቹን አጥቶ ምንያህል ሊዳከም እንደሚችል ማሰብ እጅጉን ከበደኝ። በነገራችን ላይ በጊኒው ጨዋታ አፈወርቅ፣ ተስፋሚካኤል፣ አቦነህ ፣ ንጉሴ አስፋው እና ሌሎቹም የብሔራዊ ቡድናችን አባላት የሚገርም ብቃት እንዳሳዩና ምርጥ ጨዋታ እንደተጫወቱ ከዚህም-ከዚያም ከመስማታችን ውጪ እስከ ዛሬ ድረስ ስለዚያ ጨዋታ በደንብ አልተነገረም፡፡ ስለ እነዚያ ተጫዋቾቻን ጀግንነትም በዝርዝር የተገለጸ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለ እውነቱ ያ ታሪክ መነገር አለበት፤ በሰፊው ሊወሳ ይገባዋል፡፡ ጓደኞቼ፣ ወዳጆቼና የታሪኩ አካላት ስለ ጊኒው ጨዋታ አንድ ቀን ጽፋችሁ በአግባቡ እንደምታስነብቡን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያን የመሰለ ጨዋታማ እንዲሁ ዝም ተብሎ መረሳት ወይም መቅረት የለበትም፡፡

ለማንኛውም የመልሱ ጨዋታ በመስከረም 1974 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኖ አሰልጣኝ መንግሥቱ ወርቁ ኳስ ወደ ማቆሙ የተቃረበው ካሣሁን ተካን ጨምሮ አርባ ተጫዋቾች መርጦ ናዝሬት ለዝግጅት ሄደ። ጊዜው የክረምት ወቅት በመሆኑ አዲስ አበባ ለዝግጅት ስለማትመች ናዝሬት ተመራጭ ከተማ ሆነች። ከተወሰኑ ቀናት የልምምድ ቆይታ በኋላ በዝግጅት ላይ ከነበረው ቡድን ሃያ አምስት ተጫዋቾች (ይመስለኛል) ተመርጠው ለተሻለ ዝግጅት ወደ ሶቪየት ህብረት ተጓዙ። በሶቭየት ህብረት ከአንድ ወር በላይ (ይመስለኛል) ከቆዩ በኋላ ወደ ሃገራችን ሲመለሱ አሰልጣኝ መንግስቱ እዚያው ሶቭየት በትምህርት ላይ የከረመውንና ቀደም ሲል ለድሬዳዋው ኢትዮ ሲሜንት የተጫወተውን ጥበበ ታደገን ወደ ብሔራዊ ቡድናችን ቀላቅሎት ስለነበር ተጫዋቹ ወደ አዲስ አበባ ከቡድኑ ጋር ተመለሰ። (ጥበበ ታደገ ከጊኒ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ በግራ ተከላካይ መስመር ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡)
ጨዋታው የሚካሄድበት ቀን ሲደርስ ፌዴሬሽኑ አዲስ አሰራር አመጣ። የትኬት ሽያጭን ከአትራፊዎች እጅ ለማውጣት ሲል “የስታዲየም መግቢያ ትኬት ከአንድ ሳምንት በፊት በመታወቂያ ነው የሚሸጠው፡፡” የሚል አዲስ ደንብ አወጣ። በዚያን ጊዜ መታወቂያ የሚሰጠው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና ከዚያ በላይ ለደረሰ ሰው ነበር። እኔ ደግሞ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ባልፍም ገና መስከረም ወር መጀመሪያ በመሆኑና ትምህርትም ስላልተጀመረ መታወቂያ አልነበረኝም። ስለዚህም አንድ መላ መፍጠር ነበረብኝ፡፡ ታላቅ እህቴ የ ተማሪ ስለነበረች ከመታወቂያዋ ላይ የእርሷን ፎቶ ገንጥዬ የራሴን አደረኩ፤ ለማህተሙም የሆነ መላ አገኘሁለትና “መታወቂያን” ይዤ ትኬቴን ገዝቼ የጨዋታውን ቀን መጠበቅ ጀመርኩ። እንደማይደርስ የለምና የጨዋታው ቀን ደረሰ ።

ስታዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሏል፤ በዘፈንና በጭፈራ ደግሞ እጅጉን ደምቋል፤ ህዝቡ ቡድናችንን ለመደገፍ ግልብጥ ብሎ መጥቶ አስደሳች ድባብ ተፈጥሯል። ጨዋታው ተጀመረ! ጊኒዎች ጥሩ ይጫወቱ ጀመር። የእኛ ልጆችም እ፡በደንብ ለመንቀሳቀስ ቻሉ። ነገርግን ጊኒዎች ቀድመው አገቡብን። ያ ሁሉ ጭፈራ ባ’ንዴ ቆመ። እስክስታ ስንወርድ የነበርነው ሁሉ አርፈን ቁጭ አልን፤ ተመልካቹ ፀጥ-ረጭ አለ፡፡ ቡድናችን ብዙ ታገለ፤ በርካታ የግብ ሙከራዎችን አደረገ፤ ግን ጎል ከየት መጥቶ! ምንም ግብ ሊገኝ አልቻለም። ደቂቃዎች ነጎዱ፤ እንዲህ-እንዲህ እያለ ጨዋታው ወደ ማለቂያው ላይ ሊደርስ ሆነ፤ ጭንቀታችን በረታ፡፡ ጊኒዎች ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ተቃረቡ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ልማደኛው ሙሉዓለም እጅጉ ከርቀት ያሻማውን ኳስ መሐመድ ዑስማን (ሚግ) ከጊኒ ተከላካዮች መካከል ከፍ ብሎ ዘሎ በግንባሩ በመግጨት ቡድናችንን አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጠረ። ስታዲዮሙ በአንድ እግሩ ቆመ። ወደ ሊቢያ ለመሄድ ያቺ ጎል በቂ ነበረች፡፡ ሆኖም የጨዋታ ማገባደጃ ፊሽካው ድምጽ ገና አልተሰማምና ከጎሏ ደስታ መልስ ሁላችንም ጊኒ እንዳያገባ ከፍተኛ ስጋት ያዘን፤ የቀሩትን ደቂቃዎች በጭንቀት መቁጠር ጀመርን። ጥቂት ደቂቃዎች እንዳለፉ የጨዋታውን ማለቅ ዳኛው በፊሻካቸው አበሰሩ፡፡ እኔና ሁለት ጓደኞቼ (ኢሳይያስ ብርሃኑ እና መስፍን በዛብህ) ጊዜ ማባከን አልነበረብንም፡፡ ወዲያውኑ ከስታዲየሙ ሮጠን ወጣን፤ በ ሲ-ሜዳ በኩል አቋርጠን ቡድናችን ወዳረፈበት ወደ ጊዮን ሆቴል አመራን፤ ወደ ውስጥም ዘልቀን ገባን፡፡ ደጋፊዎች ገና ከስታዲየሙ ስላልወጡ ወደ ሆቴሉ ለመግባት ችግር አልገጠመንም። ረዘም ካለ ጥበቃ በኋላ ቡድናችንን የያዘው አውቶቢስ በህዝብ ጭፈራ ታጅቦ ጊዮን ሆቴል ደረሰ። ህዝቡ ቁጥር-ሥፍር  አልነበረውም። ተጫዋቾቹ ወደ ሆቴሉ ከገቡ በኋላ አብሯቸው ወደ ጊዮን የገባው ገብቶ-ቀሪው በርካታ ህዝብ ወደ መጣበት ተመለሰ። እኛ ቀድመን በመግባታችን ኃይላትን፣ ጥበበን፣ ዳኙን፣ ጋሜን፣ ተስፋሚካኤልን፣ ሙሉዓለምን፣ ንጉሴ ገብሬን፣ ተረፈ ደጉን፣ ተስፋዬ ዘለቀን፣ አስፋው ባዩን፣ ካሣሁን ተካን፣ ሚግን፣ ኃይሉ ጎሹን፣ ተስፋዬ ከበደን፣ ኤርሚን፣ ተፈራን፣… ብቻ የቻልነውን ሁሉ በማቀፍና በመሳም ደስታችንን አብረን ለመግለፅ ቻልን። የዚያን ቀን ህዝቡ ቡድኑን አጅቦት ሲመጣ አንድ ዘፈን በጣም ይደጋገም እንደነበረ አስታውሳለሁ። “አይረሳም ትዝታው- አይረሳም!” የሚል፡፡ በዚያች ዕለት ማንም ሰው ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ሠላሳ አንድ ዓመታት ይፈጀበታል ብሎ የገመተ የለም፡፡ ግን ፈጀበት!

አሁን ደግሞ ሰላሣ አንድ ዓመታት ወደፊት እንሂድ፡፡ ቀኑ እ.አ.አ September 8, 2012 ቅዳሜ ነበር፡፡ ጓደኛዬ (ፍቅርሽ-Fikrsh Y) በጠዋት ደውሎ “ብሔራዊ ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሱዳን ጋር ይጫወታል፡፡ ጨዋታውን እንየው፡፡” አለኝ። እኔም በደስታ ተስማምቼ ጨዋታውን የምናይበት ቦታ ፍለጋ ማሰስ ጀመርን፡፡ ብዙ ቦታ ፈለግን አጣን። በመጨረሻም ሌላው ጓደኛችን ግርማ በርሄ ደውሎ ስካይላይን አካባቢ ያለ የሱዳኖች ሬስቶራንት ጨዋታውን በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ነግሮን ዘላለም በሻሻ (ዞላን) ጠርተን ቦታው ስንደርስ እውነትም ጨዋታው በቀጥታ ይተላለፋል። ውጤቱ አስደንጋጭ ሆነብን። ሱዳን 3-1 እየመራች ነበር። አካባቢያችን የነበሩት ሱዳናውያን በደስታ ሰከሩ። ትንሽ ቆይቶ ግን ቡድናችን በሚገርም ሁኔታ ሁለት ጎል አግብቶ ጨዋታው 3-3 ሆነ። ተጫዋቾቻችን በጣም ጥሩ እየተጫወቱና እያጠቁ ሳሉ ዳኛው ሁለት ፍፁም ቅጣት ምት ለሱዳን ሰጥተው ሱዳን 5-3 አሸናፊ ሆነች። ቡድናችን ቢሸነፍም እኛ ግን በቡድናችን ብቃት ተስፋ አደረብን። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አዲስ አበባ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ ተሰብስብን ለማየት ተቀጣጥረን ተለያየን። October 14, 2012 ደረሰ፡፡ እኛም በጠዋት ወሳኙን የመልስ ጨዋታ ለማየት በርከት ብለን ባቢሎን ፉትቦል ካፌ ተገኘን። ጨዋታው ተጀመረ! ቡድናችን ያጠቃል- ግን ጎል የለም። ሳላዲን ሞከረ፤ አዳነ ሞከረ፤  ጌታነህ ሞከረ፤ ጎል ግን አልተገኘም። 0-0 እረፍት ሆነ። ያ ውጤት ሱዳንን ያሳልፈዋል። ከእረፍት መልስ ቡድናችን ማጥቃቱን ቀጥሎ ጌታነህ ያሻማውን አዳነ አገባ። ደስታውና ጭፈራው ቀለጠ። ነገርግን ሌላም ተጨማሪ ጎል ያስፈልግ ነበረና ያቺ ግብ ብቻ በቂ አልነበረችም። አንበሳው ሳላዲን ሰዒድ ሱዳን ግብ ክልል ውስጥ ያገኛትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀየራት፡፡ ግቧ ለቡድናችን ሁለተኛ ሆና ኢትዮጵያችን ደቡብ አፍሪካ ላይ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ እንድትሆን አስቻለች፡፡ ብዙ ጨፈርን፤ የሚገርመው እኔ እየጨፈርኩ የማስበው ከሠላሳ ዓመታት በፊት (መሐመድ ኡስማን) ሚግ ጊኒ ላይ አግብቶ ቡድናችንን ወደ ሊቢያው አፍሪካ ዋንጫ የወደሰችውን ጎል ነበር። በዚያን ዕለት ተሰባስበን ደስታችንን እየገለፅን ከነበረነው ጓደኛማቾች መሐል ከኔ ሌላ ምናልባት ማኅደር ብቻ የጊኒውን ጨዋታ ሊያስታውስ ይችል ይሆናል። ሌሎቹ የዚያን ጊዜ በጣም ልጆች ነበሩ። ኧረ ያልተወለዱ ሁሉ ይኖሩበታል። ብቻ በደስታ አብረን እየጨፈርን እኔም ከሠላሳ ዓመታት በፊት ጊዮን ሆቴል ህዝቡ ሲዘፍነው የሰማሁትን “አይረሳም ትዝታው -አይረሳም”ን በውስጤ እየዘፈንኩ ምሽቱን ተያያዝነው። ባንዲራችንን ይዘን በየቦታው እየሄድን በጭፈራ ደስታችንን ገለፅን።

በዚያ ሁሉ ደስታ መሐል ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኳስ ስጫወት እጄ ላይ በደረሰብኝ ጉዳት ምክኒያት በማግስቱ (October 15, 2012) ቀዶ ጥገና ለመድረግ በ6፡00 AM ሃኪም ቤት መገኘት እንደነበረብኝ ትዝ ያለኝ 3፡00 AM ላይ ነበር። መቼም ወዳጅ አያሳጣ- አንጠልጥለው ቤት ወስዱኝ። ብዙም ሳልተኛ ነጋ። በእግዚአብሄር እርዳታ ሳላረፍድ በጠዋት ሃኪሙ ጋር በቀጠሮዬ ሰዓት ደረስኩ። የድካሙ ነገር ግን አይወራም። ለኳስ ምን ያልሆነው አለ!

ይኸው 1973 ዓ.ምን (1981) ከ2004 ዓም (2012) ጋር አገናኘሁላችሁ፡፡

ጥያቄ ካላችሁ አለሁ።

የምታስታውሱት ነገር ካለ፣ ማስተካከያ፣ እርማት፣ አስተያየት ካላችሁ በደስታ እቀበላለሁ፡፡
አክባሪ ወንድማችሁ፦ ኤርምያስ ብርሃነ

ቀዳሚ መኮንን (ቀዴ) ለታሪኩ ማስረጃ እንዲሆነኝ  ካንተ ማህደር ፎቶዎች ተበድሬያለሁ!


ስለ ፀሃፊው

ጸሃፊው በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ያደገና ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የተደረጉ የዚያን ዘመን የሃገራችን እግርኳስ ጨዋታዎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ፣ የጨዋታዎቹን አጠቃላይ ገጽታዎች በጥልቀትና በስፋት የሚያስታውስ እግርኳስ አፍቃሪ ነው፡፡ ከ1981 ዓ.ም በኋላ ነዋሪነቱን በአሜሪካ አገር ቢያደርግም አሁንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሃገሩን እግር ኳስ ከመከታተል ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ