በሱዳን ፕሪምየር ሊግ ዛሬ አመሻሽ ላይ በተደረገ ጨዋታ አል ሜሪክ ኮስቲ አሃሊ ሸንዲን 4-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አስገራሚ ምሽትን አሳልፏል፡፡ ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ሸንዲ በአል ሂላል 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ በ55ኛው ዲቂቃ ተቀይሮ በመግባት በቀኝ አማካይ ስፍራ በመጫወት ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው አዲስ ዛሬ ግን በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ በጨዋታው ላይ ቋሚ ሆኖ የተሰለፈው አዲስ በሁለተኛው አጋማሽ ከኳስ ውጪ የኮስቲ ተጫዋችን ሲማታ በመታየቱ በቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡
ለኮስቲ የድል ግቦች ሞታዝ፣ አይመን እና ኮትዲቯሪያዊው ዲኮር (ሁለት) አስቆጥሯል፡፡ ሸንዲን ከባዶ መሸነፍ ከመታደግ ውጪ ፋይዳ ያልነበራት ግብን ትውልደ ናይጄሪያዊው ኬሌቺ ኦሶኑዋ (በፍፁም ቅጣት ምት) እና ናድር ኤል ጣይብ ለመረብ አዋህደዋል፡፡
የሱዳን ፕሪምየር ሊግን ሰባት ጨዋታ ያደረገው ካርቱም አል ዋታኒ በ19 ነጥብ ሲመራ አል ሜሪክ እና አል ሂላል በ16 እና 13 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው፡፡ አምስት ጨዋታ ያደረገው አሃሊ ሸንዲ በዘጠኝ ነጥብ ሰባተኛ ነው፡፡
ሸንዲ በዘንድሮው የካፍ ኮንፌድሬሽን ላይ ተሳታፊ ሲሆን በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ተሸንፏል፡፡ ውሉን በዓመቱ መጀመሪያ ያራዘመው ቀድሞው የዋሊያ ኮከብ አዲስ በያዝነው የውድድር ዘመን አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡