ቲፒ ማዜምቤ የካፍ ሱፐር ካፕ ሻምፒዮን ሆነ 

የዲ. ሪ. ኮንጎ ክለብ የሆነው ቲፒ ማዜምቤ የቱኒዚያው ኤቷል ደ ሳህልን 2-1 በማሸነፍ የካፍ ሱፐር ካፕ ዋንጫን ለሶስተኛ ግዜ ዛሬ አሸንፏል፡፡

የካፍ ሱፐር ካፕ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ መካከል የሚደረግ ሲሆን ቲፒ ማዜምቤን እና ኤቷል ደ ሳህልን ያገናኘው የዘንድሮው ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል፡፡ ሉሙቡምባሺ በሚገኘው ስታደ ቲፒ ማዜምቤ በተደረገው ጨዋታ ጋናዊው አጥቂ ዳንኤል አዲጂ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ በማሳረፍ ለማዜምቤ ዋንጫውን ማንሳት ቁልፍ ሚና ተወጥቷል፡፡ ኤቷል ደ ሳህልን ከመሸነፍ ያላዳነች ግብ መሃመድ ሳክኒ የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አስቆጥሯል፡፡

የዓምና የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊዎቹ ቀያዮቹ ሰይጣኖች በአህመድ አካቺ እና አሊያ ቢሪጉዪ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርግም ከመሸነፍ መዳን አልቻሉም፡፡ በአንጻሩ ቲፒ ማዜምቤ ውጤቱን ማስፋት የሚችሉበትን አጋጣሚዎች በጆናታን ቦሊንጊ እና ሳሊፍ ኩሊባሊ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ የቻን 2016 የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ሚቻክ ኤሊያ በሁለተኛው አጋማሽ በመግባት ለማዜምቤ መጫወት ችሏል፡፡

ፈረንሳዊው አዲሱ የቲፒ ማዜምቤው አሰልጣኝ ሁበርት ቬሉድ በኮንጎው ክለብ የመጀመሪያ ዋንጫቸውን አሳክተዋል፡፡ የኤቷል አሰልጣኝ ፋውዚ ቤንዛርቲ ሱፐር ካፑን ከ8 ዓመት በኃላ ወደ ክለቡ የመለለስ ፍላጎታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ለ23 ጊዜያት ያህል የተካሄደው የካፍ ሱፐር ካፕን የግብፁ አል አሃሊ ስድስት ግዜ በማንሳት ባለሪከርድ ነው፡፡ የአምስት ግዜ የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ ሶስት ግዜ ሲያነሳ ተሸናፊው ኤቷል ደ ሳህል ሁለት ግዜ ዋንጫውን አንስቷል፡፡ ኤቷል ደ ሳህል ለመጨረሻ ግዜ የካፍ ሱፐር ካፕ ዋንጫን ያነሳው 2008 ነበር፡፡

ኤንግልበርት በሚል ስም ይታወቅ የነበረው ቲፒ ማዜምቤ ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም አንስቶ በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ ሲሆን በቀድሞ የካታንጋ አስተዳዳሪ ባለሃብት ሞይስ ካቱምቢ ስር ይተዳደራል፡፡ ክለቡ በ2016 አፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሴንት ሚሸል አሸናፊ ይጋጠማል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *