ሶከር ሜዲካል | ሆድ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች

በእግር ኳስ ውስጥ በሆድ አካባቢ የሚደርሱ ጉዳቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ባይሆኑም በቅርብ ዓመታት በቁጥር እየጨመሩ መጥተዋል። የተለመደ ጉዳት ካለመሆኑ የተነሳ በቶሎ ላይታወቅ እና ላይታከም የሚችልበት ዕድልም ሰፋ ያለ ነው። ከዚህም በተጨማሪ እንደ አጥንትና ጡንቻ ላይ እንደሚደርሱ ጉዳቶች ግልፅ ምልክት ላይኖረው ይችላል ። የዚህም ምክንያት በሆድ ውስጥ የሚገኙ የሰውነት አካላት ( intra-abdominal organs) ሲጎዱ ወዲያውኑ በቀላሉ ለመለየት ሊከብድ ስለሚችል ነው። ስለ ጉዳዩ የሚኖር በቂ ዕውቀት ችግሩን በፍጥነት ለማወቅ እና ለማከም ይረዳል።

በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት የሆድ ጉዳት በሁለት ዋና ምክንያቶች ሊደርስ ይችላል። በእንቅስቃሴ ውስጥ ከተጋጣሚ ተጫዋች ጋር በሚኖር ግጭት አልያም በከፍተኛ ጉልበት በተመታ ኳስ ሊከሰት ይችላል።

በሆድ ላይ በሚደረግ ቀዳሚ ምርመራ (abdominal examination) የህመም ስሜት እና በኋላም በአንጀት ውስጥ የሚኖር ድምፅ (bowel sounds) መጥፋት ሊታይ ይችላል። ነገር ግን ህመሙ ዘግይቶ የሚከሰት ምልክት የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፋ ያለ ነው። ዘግተው የሚታዩ ምልክቶች በውሰኛው የሆድ ዕቃ ውስጥ ያሉ አካላት ጉዳት ሲደርስባቸው የሚስተዋሉ ሲሆን ከውጭ የሚደርስ ግጭት (blunt trauma) ጉበት ፤ ጣፊያ እና ኩላሊትን ሊጎዳ ከመቻሉ በተጨማሪ ውስጣዊ የደም መፍሰስ ሊያስከትል ስለሚችል ለህይወት አስጊ ነው። ይህ ሲያጋጥም ወዲያውኑ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል መላክ ተገቢ ነው።

በሆድ ውስጥ በሚኖር መድማት (intra-abdominal hemorrhage –> Shock) ሊያጋጥም ይችላል። በዚህን ወቅትም ለዚህ መደረግ ያለባቸው የአተነፋፈስ አካላትን መጠበቅ ፤ ኦክስጅን መስጠት ፤ በደም ስር ፈሳሽ እና መድሃኒት መስጫ መቀጠል እና ተገቢውን ፈሳሽ እና ህመም ማስታገሻ መስጠት እና የደም ግፊት በከፍተኛ መጠን እንዳይወርድ መቆጣጠር ያስፈልጋል።

በFIFA የድንገተኛ ህክምና ሻንጣ ውስጥ እንደዚህ አይነት ጉዳቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ለማከም የሚረዱ መሳሪያዎች ተሟልተው ተቀምጠዋል።

እነዚህ ጉዳቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት በመጀመሪያ ደረጃ ሜዳ ላይ የሚሰጠው ህክምና ወሳኝነት እጅጉን ወሳኝ ሲሆን የተጎዳው ተጫዋችም ለከፋ ነገር እንዳይጋለጥ ከመጠበቅ አንፃር የሚሰጠው ጥቅም ላቅ ያለ ነው። ስፖርተኛው በዚያ ጊዜ የሚያሳያቸው ምልክቶች ስለጉዳቱ መጠነኝነት እና አደገኝነት ስለሚገልፁ በጥልቅ ሊጤኑ ይገባል። የውስጥ የሆድ ዕቃ አካላት የተጎዱ ከሆነ ወይም ተጎድተዋል ተብሎ ከታሰበ ተጫዋቾቹ በጀርባቸው እንደተኙ በአንቡላንስ ሊወሰዱ ይገባል።

ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላም የጉዳቱን መጠን ለመረዳት የተለያዩ ምርመራዎች የሚደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ምርመራዎች መካከል ዋንኞቹ የሚከተሉት ናቸው።

  • የሆድ እና የደረት ኤክስ ሬይ
  • አልትራሳውንድ (FAST)
  • ሲቲ ስካን
  • ኤም አር አይ

ከላይ ከተጠቀሱት ጉዳቶች በኋላ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የሚመለሱበት ወቅት እንደ ጉዳቱ አይነት እና መጠን ይለያያል። ጉዳቱ የጡንቻ አካላትን የሚያጠቃ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ ዕረፍት እና በበረዶ ከማሸት በኋላ ወደ ሜዳ መመለስ ይቻላል። ነገር ግን ጉዳቱ እንደ ጉበት እና ኩላሊት የመሰሉትን የውስጥ አካላት የሚያጠቃ ከሆነ ህክምናው ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀዶ ጥገናም የሚያስፈልግበት አጋጣሚም ሊኖር ይችላል።

ለዚህ ፅሁፍ እንደ ግብዐት የተጠቀምነው መፅሀፍ- Football Emergency- Medicine -Manual-2nd-edition-2015