የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን በተመለከተ መግለጫ ተሰጠ

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የወሰነውን “የብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞችን ውል አላራዝምም “ጉዳይን በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት መግለጫ ተሰጥቷል።

ከ8 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ የሴቶች እና ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሶፊያ እንዲሁም ውላቸው እንደማይታደስ የተገለፀላቸው ሦስቱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ተገኝተዋል።

መግለጫውን የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ካስጀመሩት በኋላ ክቡር ፕሬዝዳንቱ ስለተፈጠረው ጉዳይ መጠነኛ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸውም መግለጫው የተዘጋጀው በስፖርት ወዳዱ ማኅበረሰብ ዘንድ የተፈጠረውን ግርታ ለማጥራት ታስቦ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ካነሱ በኋላ የአሰልጣኞቹን ውል ላለማደስ ስለወሰኑበት ሒደት ገለፃ አድርገዋል።

“በዋናነት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ይህንን ውሳኔ የወሰነው በኮቪድ-19 ምክንያት ነው። ይህ ወረርሽኝ በዓለም ላይ ያላመጣው ተፅዕኖ የለም። እግርኳሱም በዚሁ ወረርሽኝ ተጎድቷል። ይህንን ተከትሎ በሃገራችን የሊግ ውድድሮች ቆመዋል። እኛ ብቻ ሳንሆን ካፍና ፊፋም አህጉራዊ ውድድሮችን ከመከወን ቆጥበዋል። እኛም ይህንን በመረዳት ውላቸው የተጠናቀቁ እና በቅርቡ የሚጠናቀቁ አሰልጣኞቻችንን ውል ለማደስ አልፈለግንም። ሲጀምር ኮንትራት የማደስ እና ያለማደስ ውሳኔ በሁለቱ አልያም በአንዱ ስምምነት ላይ ሊመረኮዝ ይችላል። ይህንን ተከትሎ ውድድር በሌለበት ጊዜ የአሰልጣኞቹን ኮንትራት ማደስ አስፈላጊ ሆኖ ስላልታየን ውሳኔውን ወስነናል። ነገርግን እንደሚወራው ፌደሬሽኑ በገንዘብ ችግር አደለም የአሰልጣኞቹን ውል ላለማደስ የወሰነው። በተጨማሪም ይህንን ውሳኔ ስንወስን የውጤትን ነገር ግንዛቤ አላደረግንም።” ብለዋል።

ከክቡር ፕሬዝዳንቱ መጠነኛ ማብራሪያ በመቀጠል የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ብርሃኑ ግዛው ሃሳቡን ለብዙሃን መገናኛዎች አጋርቷል። ብርሃኑም በንግግሩ ከ6 ወራት በፊት ወደ አሰልጣኝነት ሲመጣ የገባውን ቃል አስታውሶ አስተያየቱን ለግሷል።

“እኔ ወደ ቦታው ስመጣ አግባብ ባለው መንገድ ነው። እንደመጣሁም ፊርማዬን ከማኖሬ በፊት አላማዬን አስረድቼ ነው። በዚህም ለአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን እንደማሳልፈው ካልሆነ ግን በራሴ ፍቃድ ቦታውን እንደምለቅ ተናግሬያለሁ።” ብለዋል።

አሰልጣኝ ብርሃኑ ቀጥለው በተለይ ከዚህ በፊት የነበረውን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቅጥር እና ስንብት ሂደት በተመለከተ ሀሳብ አንስተዋል። በንግግራቸውም በፊት የነበረው አሰራር በጣም ብልሹ እንደነበረ አስታውሰው የአሁኑን ሂደት ገልፀዋል።”እኔ ከዚህ በፊትም ለ6 ጊዜያት የብሄራዊ ብድን አሰልጣኝ ሆኜ ነበር። በአንዳንዱ አጋጣሚ እንደውም በሚያስቁ ብልሹ አሰራሮች ስሾም እና ስነሳ ቆይቻለሁ። በተለይ አሰልጣኞች የምንባረርበት መንገድ እጅግ ጥሩ ያልነበረ ነው። አሁን ግን በጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አማካኝነት በክብር ጥሪ ቀርቦልን በግልፅ ያለው ነገር የተነገረን ሂደት መልካም ነው።”

ከአሰልጣኝ ብርሃኑ በመቀጠል ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ፍሬው ሃይለገብርኤል ስሜቱን ለጋዜጠኞች አጋርቷል።

“እኛ ስራውን ጀመርን እንጂ አልቋጨንም። ሁለት ጨዋታ ብቻ ቢሆንም ያከናወነው በቡድኑ ውስጥ ጥሩ መነሳሳት ፈጥረናል። ይህንን ተከትሎ ኮቪድ መጣና እቅዳችንን አፋለሰብን። እርግጥ ውሌ ቀደም ብሎ አልቋል። ግን ፌደሬሽኑ በጽህፈት ቤቱ አማካኝነት ጠርቶን ያለውን ነገር አስረድቶናል። በዚህም ባለው ነገር ተስማምተን ተለያይተናል። ግን እኔ ውድድሮች ተቋርጠው ስራዬን አላቆምኩም ነበር። በቴክኖሎጂ እየታገዝን ተጨዋቾች በግላቸው ልምምድ እንዲሰሩ ስናደርግ ነበር።” በማለት ተናግሯል። ፍሬው ጨምሮም ሁሉም አካል ከዚህ በኋላ በቀጣይ ስለሚኖር እና ስለሚፈጠር ነገር ማሰብ እንዳለበት በማሳሰብ ሃሳቡን ቋጭቷል።

በመቀጠልም ላለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ የሚገኙት እና ውላቸው ከፊታችን ሃምሌ 30 በኋላ እንሚጠናቀቅ የታወቀው ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

“በቅድሚያ ፌደሬሽኑ ይህንን መግለጫ ስላዘጋጀልን አመሰግናለሁ። በመቀጠል እኔ ወደዚህ ቦታ ስመጣ በዋናነት ቃል የገባሁት በወጣቶች የተገነባና ተሻጋሪነት ያለው ቡድን ለመገንባት ነው። በግሌ ይህንንም እያደረግን ነበር ብዬ አምናለሁ። ከምንም በላይ በ2 ዓመት ቆይታዬ ጥሩ ጊዜ እንደነበረኝ መግለፅ እፈልጋለሁ። በተለይ ፌደሬሽኑ ስራዬ ላይ ጣልቃ ሳይገባ የነበረበን መንገድን ማድነቅ እፈልጋለሁ። ይህ ነገር እንደ ባህል እንዲቀጥልም እሻለሁ።” ብለዋል።

አሰልጣኙ ጨምረውም ከሜዳ ውጪ ቡድኑ የነበረውን ሃገራዊ አስተዋጽኦ በማንሳት ሃሳባቸውን ቀጥለዋል።”እንዳልኩት በሜዳ ላይ ቡድኑ እድገት ላይ ነበር። በተጨማሪ ከሜዳ ውጪም ቡድኑ የተለያዩ ማህበራዊ ሃላፊነቶችን እንዲወጣ አድርገናል። ከዚህ ውጪ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እንደመሆኔ ውድድር በተቋረጠበት ጊዜ ስልጠናዎችን ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ስንሰጥ ቆይተናል። ይህም አሰልጣኖችን ለማብቃት ረድቷል። በተለይ ደሞ አሜሪካ ከሚገኘው አሰልጣኝ አምሳሉ ጋር በመሆን ከቤኔፊካ፣ ሪያል ማድሪድ እና ቼልሲ አሰልጣኞችን በመጋበዝ ስልጠናዎችን ሰጥተናል። በቀጣይም እስከ ሃምሌ 30 ድረስ ውል ስላለኝ ስራዬን በአግባቡ ለመስራት እጥራለሁ። በስተመጨረሻ ግን በፌደሬሽኑ ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞችን እንዲሁም በባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አዲስ አበባ እና መቐለ የነበሩ የቡድኑ ደጋፊዎችን እና ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲያግዙኝ የነበሩ የሃገሬ አሰልጣኞችን አመሰግናለሁ።” በማለት ሃሳባቸውን ከጠቀለሉ በኋላ በቀጣይ ሃገራቸው በምትፈልጋቸወረ ቦታ ላይ ለማገልገል ፍቃደኛ እንደሆኑ ገልፀዋል።

ሶስቱ አሰልጣኞች ሃሳባቸውን ካካፈሉ በኋላ አቶ ኢሳያስ መልሰው መድረኩን በመያዝ ተጨማሪ ሃሳቦችን አንስተዋል። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ፌደሬሽኑ የገንዘብ ችግር እንደሌለበት፣ የአሰልጣኞቹን ኮንትራት ለማቋረጥ ሳይቸኩሉ መቆየታቸውን፣ ከመንግስት ጋር በኢትዮጵያ እግርኳስ መፃኢ ህይወት ዙሪያ እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ ፌደሬሽኑ አንድ ተቋም ለሃገሩ እንደሚያስብ እነሱም ለሃገራቸው እንደሚያስቡ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ሃሳቦች ከመድረክ ከተነሱ በኋላ በቦታው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛዎች ጥያቄ እንዲጠይቁ እድል ተመቻችቷል። በዚህም የተለያዩ ጥያቄዎች ተጠይቀው ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷል።

በተሰነዘሩት ጥያቄዎች መሰረትም በቀጣይ ፌደሬሽኑ ከመንግስት በሚሰጥ አቅጣጫ መሰረት ሂደቶችን እንደሚያስኬድ፣ ከፊፋ እስካሁን የገንዘብ ድጋፍ እንዳልተደረገ፣ ፌዴሬሽኑ የነበረበትን እዳ ከፍሎ እንደጨረሰ፣ መርሃ ግብር የወጣላቸው ከ20 ዓመት በታች ጨዋታዎች በመንግስ ፍቃድ አማካኝነት እንደሚከወኑ እና ቀጥይ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኖቹ በቴክኒክ ክፍሉ አማካኝነት ተመርጦ ስራ አስፈፃሚው እንደሚያፀድቅ ተገልጿል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ