ሲዳማ ቡና የአሰልጣኞቹን ውል አራዘመ

ሲዳማ ቡና የዋና አሰልጣኙ ዘርዓይ ሙሉ እና የረዳቶቹን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ ሲዳማ ቡና ነው፡፡ ክለቡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተፎካካሪ መሆን እንዲችል ደግሞ የዋና አሰልጣኙ ዘርዓይ ሙሉ ድርሻ የጎላ ነበር፡፡ የቀድሞው የክለቡ አምበል ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት ሲዳማን እያገለገለ ሲሆን ውሉ በመጠናቀቁ በከፍተኛ ክፍያ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በክለቡ መቆየቱ ተረጋግጧል፡፡

የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ፣ ስልጤ ወራቤ እና ኢኮሥኮ አሰልጣኝ እና ከ2011 የዘርአይ ሙሉ ረዳት በመሆን ሲያገለግል የቆየው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ስንታየው ግድየለውም ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በክለቡ ቆይታን ያደርጋሉ፡፡ የረጅም ዓመት የህክምና ባለሙያ የነበረው አበባው በለጠም በክለቡ እንደ አሰልጣኞቹ ሁሉ ውሉ ተራዝሞለታል፡፡

ሲዳማ ቡና ኮንትራታቸው የተጠናቀቁ እንዲሁም አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደመቀላቀሉ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ እንደሚገባ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ