መረጃዎች| 98ኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ የመገባደጃ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ያላቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው እና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሻሸመኔን ከሀዲያ ያገናኛል።

አዲስ አሠልጣኝ ከቀጠሩ በኋላ ያሳዩት መሻሻል በብዙዎች ዘንድ የተሻለ ግምት እንዲሰጣቸው አስገድደው የነበሩት ሻሸመኔ ከተማዎች ለአምስት የጨዋታ ሳምንታት ሳይሸነፉ ከዘለቁ በኋላ ያስተናገዷቸው ተከታታይ ሽንፈቶች ከወራጅ ቀጠናው እንዳይነቃነቁ አድርጓቸዋል።

ሻሸመኔዎች በቀሪ ጨዋታዎች በሊጉ ለመትረፍ ያላቸውን ዕድል ለመጠቀም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየውን የተከላካይ ክፍላቸውን ብቃት ከማስቀጠል ባለፈ በጉልህ የሚታየውን የፊት መስመር ችግራቸውን መቅረፍ ግንግድ ይላቸዋል።

የሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ለረጅም ጊዜያት በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የመርጋቱ ሚስጥር ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀቱ ነው ፤ ሆኖም በቅርብ ሳምንታት ያሳዩት እንቅስቃሴ ጠንካራው አደረጃጀት በውስን መልኩ መዳከሙን ማሳያ ነው።

ሻሸመኔዎች በቅርብ ሳምንታት ያሳዩት የመከላከል ብርታት እና የቆየው የሀዲያ ሆሳዕና ጥንካሬ መነሻነትም የነገው ፍልሚያ በግቦች የታጀበ ክፍት አጨዋወት ላይኖርበት እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሁለቱም ቡድኖች ጎል ፊት ያለባቸው የስልነት ችግር ከመከላከል ጥንካርያቸው ጋር ተዳምሮ ሌላው ጨዋታው በግቦች ያልታጀበና አካላዊ ፍልምያዎች የበዙበት ሊሆን እንደሚችሉ ቀድሞ መገመት ይቻላል።

በሻሸመኔ ከተማ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ሳምንቱን ሙሉ ልምምድ የሰሩ ሲሆን በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋችም የለም። በአንፃሩ በሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል ግርማ በቀለ ከጉዳት ቢመለስላቸውም ለጨዋታው መድረሱ ግን አጠራጣሪ ነው። መለሠ ሚሻሞ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛል።

ሀምበሪቾ ከ መቻል

በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የሚያልመው መቻል ላለመውረድ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ሀምበሪቾ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ደግሞ የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሃግብር ነው።

በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ከጣሏቸው ወሳኝ ነጥቦች መልስ ወልቂጤ ከተማን አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት መቻሎች ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወሳኝ ነገ ወሳኙን ፍልሚያ ያደርጋሉ።ተፎካካሪያቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚውን የማሸነፉ ጉዳይም ለመቻሎች በነገው ጨዋታ ከማሸነፍ ውጭ አማራጭን ሳይዙ የሚያደርጉት እንዲሆን ያስገድዳል።

የነገው ተጋጣሚያቸው ሀምበሪቾ ደግሞ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል እስከ መጨረሻው ሰዓት ለመፋለም ከነገው ጨዋታ ነጥብ ፈልጎ የሚገባ ቡድን እንደመሆኑም ጨዋታው ፈታኝ ያደርገዋል ተብሎ ይገመታል።

በሀምበሪቾ በኩል ሁለት ቡድኖች ብቻ በሚወርዱበት በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለከርሞ ቆይታቸውን ለማረጋገጥ ጊዜ በተቃራኒያቸው እየሄደ ይመስላል በመሆኑም ከዚህ በኃላ የሚጥሏቸው ነጥቦች የመውረዳቸውን ጉዳይ እርግጥ እንዲሆን ስለሚያደርጉ ከተራራ የገዘፈን የቤት ስራ የመወጣት ዓላማን ይዘው ይጫወታሉ።

ሀምበሪቾዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ መቻል እግር ኳስ ክለብ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ በፅሁፋችን ማካተት አልቻልንም።