ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡናዎች ደምቀው ባመሹበት ጨዋታ ከመመራት ተነስተው ወሳኝ ድል አሳክተዋል

ኢትዮጵያ ቡና ከሦስት ጨዋታዎች በኃላ ከማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ወደ አሸናፊነት ሲመለሱ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።

ወላይታ ዲቻ በባለፈው ሳምንት በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ አብነት ይስሐቅ፣ ፍፁም ግርማ፣ እዮብ ተስፋዬ እና ባዬ ገዛኸኝን በማሳረፍ ቢንያም ገነቱ፣ ኬኔዲ ከበደ፣ ናትናኤል ናሴሮ እና ዘላለም አባተን በመተካት ሲገቡ ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከሊጉ መሪ ጋር በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠሩት ጎል ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት የባለፈው ሳምንት ጨዋታቸው ኪያር መሐመድ እና አንተነህ ተፈራን በአስራት ቱንጆ እና በብሩክ በየነ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


በኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ ዳኝነት በጀመረው የምሽቱ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በሚታወቁበት በጥሩ ቅብብሎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን በመግባት ወደ ጎል ለመድረስ ቢጥሩም የመጨረሻ ኳሶቻቸው ጥራት የጎደላቸው በመሆናቸው እና የተከላካዮቻቸው ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ግልፅ የጎግብ ዕድሎችን ለመመልከት ተቸግረን እንድናመሽ አስገድዷል።

በጨዋታው የጎል ዕድሎች ሳንመለከት በአጋማሹ ዘለግ ላለ ደቂቃ ቢቆይም በሁለቱም በኩል የሚደረጉ የተሳኩ ቅብብሎች የጨዋታውን እንቅስቃሴ እንዳይደበዝዝ ለተመልካች ሳቢ እንዲሆን አድርገውታል።

የጨዋታው የመክፈቻ ሙከራም ሆነ ጎልም 37ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ወላይታ ዲቻ በኩል መመልከት ችለናል። የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ራምኬል ጀምስ በሰራው የማቀበል ስህተትን ተከትሎ አበባየሁ ሀጂሶ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ የግቡ ባለቤት ቡዙዓየሁ ሰይፉ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ኳሱን ወደፊት በመግፋት ከሬድዋን ናስርን የመጣበትን ጫና በማሸነፍ ሳጥን ውስጥ በመግባት በግብጠባቂው በረከት አማረ እግሮቹ መሀል አሾልኮ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ በኋላ በ41ኛው ደቂቃ እግሩ ኳስ ሲገባ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ያልታሰበ ነገርን የሚያደርገው ቢንያም ፍቅሬ በፍቃዱን ቀንሶ የመጨረሻ ምቱ ጉልበት አይኑረው እንጂ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢኖራቸውም ከሌላው ጊዜ በእጅጉኑ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል የተቸገሩት ቡናማዎቹ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት በመሄድ አማኑኤል ዮሐንስ በጥሩ መንገድ ለመስፍን ታፈሰ አቀብሎት ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መልካም አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ቡና የበላይነትን እያስመለከተን ሲቀጥል ቡናማዎቹ በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመግባት ጫና ማሳደራቸው ተሳክቶላቸው የአቻነት ጎል በ50ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት አብዱልከሪም ወርቁ ያሻገረውን መስፍን ታፈሰ በግሩም ዝላይ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

አማኑኤል አድማሱን በአንተነህ ተፈራ የቀየሩት ቡናማዎቹ የማጥቃት አቅማቸውን በማሳደግ ተጨማሪ ግቦችን ፍለጋ ጥረት ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ በአንፃሩ የጦና ንቦቹ ከመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው እንቅስቃሴ እየወረዱ ሲመጡ ይበልጡኑ የዘላለም አባተ በጉዳት ተቀይሮ መውጣት የማጥቃት ሚዛናቸው እንዲዳከም አድርጎታል።

የጨዋታው የማጥቃት ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ ቡና አጋድሎ ኳሱን እያንሸራሸሩ በሚያገኙት ክፍተቶች ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ 70 ደቂቃ ደርሷል። በአንፃሩም ወላይታ ዲቻዎችም በመልሶ ማጥቃት አንድ ነገር ለማድረግ ከማሰብ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ አልፈጠሩም።

በዚህ ሂደት 73ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ናሴሮ መስፍን ታፈሰ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካር ከሜዳ እንዲወጣ መሆኑ የበለጠ የጦና ንቦችን ጫና ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በቁጥር ብልጫ የወሰዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች የማሸነፊያ ጎል ፍለጋ በሙሉ አቅማቸው ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 84ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ከግራ መስመር አብዱልከሪም ወርቁ እጅግ በተመጠነ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ መሐመድኑር ናስር ኳሱን በደረቱ አውርዶ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ለኢትዮጵያ ቡና ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል ዕድል በተጨማሪ ደቂቃ መሐመድ ኑር ናስር ከግብጠባቂው ቢንያም ገነቱ ጋር ብቻውን ቢገናኝም በደካማ አጨራረስ ኳሱ ወደ ግብነት ሳይቆጠር የቀረው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም በቡናማዎቹ 2-1 አሸነፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከተጫዋቾቹ ሜዳ ውስጥ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዳገኙ እና ናትናኤል ናሴሮ በቀይ ካርድ መውጣት ተከትሎ የቁጥር ማነስ ብልጫ እንዲወሰድባቸው ማድረጉን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ሲገልፁ ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው በቁጥር በዝተው ድቻዎች መከላከል ማሰባቸው ስራቸውን ከባድ አድርጎባቸው እንደነበረ ገልፀው ከእረፍት መልስ በትዕግስት ኳሱን ይዘን መጫወታችን ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል በተጨማሪም በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ላይ ሆነው ማጠናቀቅ ዕቅዳቸው እንደሆነ አልሸሸጉም።