ሪፖርት | ሮድዋ ደርቢ አቻ ተጠናቋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው ተጠባቂው የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

በተጠባቂው የሮዱዋ ደርቢ ኃይቆቹ ፈረሰኞቹን 2ለ1 ካሸነፉበት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ቸርነት አውሽ ወጥተው ሲሣይ ጋቾ ፣ ማይክል ኦቱሉ እና ኢዮብ ዓለማየሁ ገብተዋል። ሲዳማዎች በአንጻሩ ወላይታ ድቻን 2ለ1 ከረቱበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አቤኔዘር አስፋው እና ቡልቻ ሹራ በአበባየሁ ዮሐንስ እና በይገዙ ቦጋለ ተተክተው ገብተዋል።

09፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት በተጀመረው የደርቢ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በሚደረጉ ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴዎች እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች እንደ ተጠባቂነቱ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ፉክክር ተደርጓል።

ጨዋታው 17ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ሰለሞን ወዴሳ ያስጀመረውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ለታፈሰ ሰለሞን አመቻችቶለት በድንቅ ሁኔታ የሰውነት ሚዛኑን በመጠበቅ ኳሱን ወደ ሳጥን ያስገባው ታፈሰም በግሩም አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎት ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችሏል።

ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት ሲዳማዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ ማይክል ኪፖሩል ከግራ መስመር ካደረገው ሙከራ ውጪ በአጋማሹ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ብልጫ የነበራቸው ኃይቆቹ በአንጻሩ 38ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተባረክ ሄፋሞ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በመታተር ተጭነው መጫወት የቻሉት ሲዳማዎች ሦስት ሙከራዎችን አድርገው ሁለቱን የመሃል ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ሲያግድባቸው የአቤኔዘር አስፋውን ሙከራ ደግሞ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ይዞበታል።

ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴው እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች ከማይክል ኪፖሩል በተነሱ ኳሶች ሁለት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ከቻሉ በኋላ 71ኛው ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ብርሃኑ በቀለ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በዛብህ መለዮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

አጋማሹን ሲጀምሩ ታፈሰ ሰለሞንን በሆድ ሕመም ምክንያት ለማስወጣት የተገደዱት ኃይቆቹ አልፎ አልፎ ከሚያደርጓቸው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ባሻገር መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ ተወሰዶባቸው የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል።

በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ብርሃኑ በቀለ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ የግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት ያገኘው ደስታ ደሙ በቀላሉ ግብ አድርጎታል።

መጠነኛ ፉክክር በተደረገባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች በሲዳማ በኩል ተቀይሮ የገባው ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን 81ኛው እና 84ኛው ደቂቃ ላይ በደካማው የግራ እግሩ ያደረጋቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሲይዝበት በኃይቆቹ በኩል ደግሞ ዓሊ ሱሌይማን 88ኛው ደቂቃ ላይ በደካማ እግሩ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረው ኳስ ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ እንደተወሰደባቸው አምነው ባደረጉት የታክቲክ ለውጥ ከዕረፍት መልስ ጨዋታውን መቆጣጠር መቻላቸውን ገልጸው ውጤቱ በቂ እንደሆነ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ያመከኗቸው ኳሶች እና የታፈሰ ሰለሞን በሕመም ምክንያት መውጣት በሁለተኛው አጋማሽ ጫና ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።