መረጃዎች | 97ኛ የጨዋታ ቀን

የሃያ አራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ይቀጥላሉ ፤ በዕለቱ የሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎችን አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ከድል መልስ የሚገናኙ ቡድኖች የሚያደርጉት የሮድዋ ደርቢ የዓመቱ ከፍተኛው የተመልካቾች ቁጥር ይመዘገብበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሽንፈቶች አገግመው ሁለት ተከታታት ድሎች ያስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች በሰላሣ ሁለት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ባለፉት የውድድር ዓመታት ሦስት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ያልቻሉት ሀይቆቹ በነገው ዕለት ማሸነፍ ከቻሉ ከ 71 ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ ሦስት ተከታታይ ድሎች ከማስመዝገብ በተጨማሪ የደረጃ መሻሻልም ያስገኝላቸዋል። በሊጉ ሰላሣ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ እና በርካታ ግቦች በማስቆጠር አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ጅማሮ የነበረውን የመከላከል ጥንካሬው ማጣቱ በሰንጠረዡ ወገብ እንዲከርም አስገድዶታል። ቡድኑ ለአራት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ባለማስደፈር መልካም አጀማመር ቢያደርግም ውጤታማነቱን ማስቀጠል አልቻለም፤ አርባ ግቦች ካስተናገደው ሀምበርቾ በመቀጠል በሁለተኛነት መቀመጡም የቡድኑ መከላከል ድክመት ዋነኛ ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም የፊት መስመር ችግሩን በውስን መልኩ የቀረፈው ሲዳማ ቡናን እንደመግጠሙ ክፍተቶቹን አርሞ መቅረብ ይኖርበታል።

በመሃል በንግድ ባንክ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጭ ስድስት ሽንፈት አልባ ሳምንታት ያሳለፉት ሲዳማ ቡናዎች ከወራጅ ቀጠና ስጋት ወጥተው በሰንጠረዡ ወገብ ተደላድለዋል።

በሊጉ ሃያ አንድ ግቦች አስቆጥረው ሃያ ሁለት ግቦች ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ያጎለበቱት የፊት መስመር ጥንካሬ ለቡድኑ መሻሻል ትልቅ አስተዋጾ አድርጓል። ቡድኑን በተረከቡበት የመጀመርያ ሳምንታት የተከላካይ መስመሩ ላይ ትኩረት አድርገው የሠሩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አሁን ጨዋታዎችን ለመቆጣጠር የማይቸገር እና በአንፃራዊነት የተሻለ የግብ ማስቆጠር አቅም ያለው ቡድን ገንብተዋል። አሰልጣኙ ቡድኑን ተረክበው ባካሄዷቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች ላይ ሀምበርቾን ጨምሮ በአራቱ የሸገር ክለቦች ሽንፈት ቢያስተናግዱም ቡድኑን ከተከታታይ ሽንፈቶች አላቀውታል። ከሀዋሳ ከተማ ጋር በሚያደርጉት የነገው ተጠባቂ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣትም በሰንጠረዡ ወገብ ይበልጥ እንዲደላደሉ ይረዳቸዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ሲዳማ ቡናዎችም በተመሳሳይ ሙሉ ስብስባቸውን ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንም ከቅጣት ይመለስላቸዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ድል የተራቡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።

በሃያ ስምንት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች በውጤት ረገድ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ አይገኙም። ካለፉት አስር ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት አምስት ሽንፈትና አራት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል።  የጦና ንቦቹ በውጤቱ ረገድ ቢቀዛቀዙም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ግን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም።  ከተከታታይ የሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ድሬዳዋን በድል የተሰናበተው ቡድኑ የሀዋሳ ቆይታውም በድል መጀመር አልቻለም። ጥሩ የማይባል የድሬዳዋ ቆይታው ለማካካስ እና የደረጃ መሻሻል ለማግኘትም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይለዋል። ይህ እንዲሳካ ግን የውጤታማነት ደረጃው የወረደው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ለውጦችን ይሻል።

በስላሣ አምስት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሰንጠረዡ አናት ከተቀመጡ ሁለት ቡድኖች ጋር ተከታታይ የአቻ ውጤት ካስመዘገቡ ወዲህ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።


በቅርብ ሳምንታት እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ድሎችን ማጣጣም ያልቻሉት ቡናማዎቹ ካለፉት ሰባት መርሐግብሮች ያገኙት ድል አንድ ብቻ ነው። በአሠልጣኝ ነፃነት ክብሬ እየተመራ በጥሩ የድል ጉዞ ላይ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በድሬዳዋ ጥሩ ቆይታ አልነበረውም። ቡድኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጤት ረገድ መንገራገጭ የገጠመውም ይመስላል። እርግጥ ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች የሊጉን መሪዎች ጨምሮ ጠንካራ ቡድኖች ቢገጥምም ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ማስመዝገቡ ግን ቡድኑ ምን ያህል እንደተቀዛቀዘ ማሳያ ነው።

ቡድኑ የፊት መስመር ጥንካሬው ይዞ መዝለቁ እንደ አንድ በጎ ጎን የሚታይ ቢሆንም ለተከታታይ አምስት ሳምንታት ግቡን ሳያስደፍር ከቆየ በኋላ የተቀዛቀዘው የመከላከል አደረጃጀት ላይ አፋጣኝ መፍትሔ ባለማበጀቱ ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በወላይታ ድቻ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበቱት መልካሙ ቦጋለ እና ፀጋዬ አበራ ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ የአናጋው ባደግ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው፤ በሌላ በኩል ቢኒያም ገነቱ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ቡናዎችም በነገው ጨዋታ የጫላ ተሺታን ግልጋሎት አያገኙም።