ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ድል በመመለስ ወደ ዋንጫው የሚያደርገውን ግስጋሴ ገፍቶበታል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዓመታት በኋላ በአንድ ውድድር ዓመት ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበበትን ድል ሲያሳካ ወልቂጤዎች አራተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል።

በተከታታይ ሽንፈት እያስተናገደ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ በመቻል 3-0 ከተሸነፈበት ስብስቡ ጌቱ ኃይለማርያም እና ፉአድ አብደላን በመሳይ ጳውሎስ እና በዳንኤል ደምሱ በመተካት ለዚህ ጨዋታ ሲዘጋጅ በአንፃሩ ባለፈው ሳምንት ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 2-2 በሆነ አቻ የወጣው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሌብ አማንኩዋህ በእንዳለ ዮሐንስ ብቻ በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል።


የሊጉን ሰባተኛ ጨዋታ የሚያደርገው ወጣቱ ፌዴራል ዳኛ ሃይማኖት አዳነ በመራው በዚህ ጨዋታ ንግድ ባንኮች ከመጀመርያው ደቂቃ ጀምሮ ኳሱን በመቆጣጠር በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ፊት በመሄድ ተጭነው መጫወት ቢጀምሩም የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ አስራ ሰባት ደቂቃ መቆየት አስፈልጓቸው ነበር። በዚህም ኪቲካ ጅማ ሳጥን ውስጥ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን በመቀነስ በግራ እግሩ የመታውን በጎሉ ቅርበት በነፃ አቋቋም የሚገኘው ሳይመን ፒተር በቀላሉ ጎል ማስቆጠር የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ያሰቡት ወልቂጤ ከተማዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ በመቆጣጠር ጎል እንዳይስተናገድባቸው ማድረግ የቻሉት እስከ 27ኛው ደቂቃ ነበር። ከእንዳለ ዮሐንስ ወደ ሳጥን የተሻገረውን ኳስ የወልቂጤው ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ በተገቢው ሆኔታ  ኳሱን ባለማራቁ ምክንያት በቦታው የነበረው ሱሌማን ሀሚድ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ንግድ ባንኮች ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ ተረጋግተው ጨዋታውን በመቆጣጠር ተጨማሪ የጎል ዕሎችን ለመፍጠር ጥረት ለማድረግ ቢያስቡም ስኬታማ ሳይሆኑ ይልቁንም በአጋማሹ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ወልቂጤዎች የማጥቃት ፍላጎት በማሳየት የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። በዚህም በ38ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደምሱ ከሳጥን ውጭ የሞከረው እንዲሁም በተጨማሪ ደቂቃ አዳነ በላይነህ ከግራ መስመር በኩል በጥሩ ሁኔታ ያሻገረው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ሳምሶን ጥላሁን በግራ እግሩ ከሳጥን ውጭ የመታው ለጥቂት በግቡ አናት የወጣበት ተጠቃሽ ነበር።

ከዕረፍት መልስ የቀጠለው ጨዋታው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን ፈጣን ሁለተኛ ጎል እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። በ48ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከአዲስ ግደይ የተነሳውን ኳስ የተቀበለው ፉዓድ ፈረጃ አጥብቆ መሬት ለመሬት መትቶት በተስፋዬ መላኩ ተሸርፎ አቅጣጫውን በመቀየር ወደ ጎልነት ተለውጦ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስገኝቷል። ጎሉም ለፉዓድ ፈረጃ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎል ሆኖ ተመዝግቧል።

ወደ ጨዋታው እንዲመልሳቸው የተሻሉ የኳስ አቅርቦቶች እንዲሁም የጠሩ ኳሶችን ለአጥቂዎች ማድረስ ያልቻሉት ወልቂጤዎች ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ብዙም የተዋጣለት ሳይሆን የጨዋታው  ደቂቃ እየገፋ ሊሄድባቸው ችሏል። በንግድ ባንኮች በኩል ጥንቃቄ በመምረጥ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር ጨዋታውን ለመግደል ቢያስቡም ይሄነው የሚባል ነገር ማሳየት ሳይችሉ የጨዋታው ደቂቃ 80ኛው ደቂቃ መድረስ ችሏል።

የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎችም ይበልጡኑ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ወደ ኋላ በማፈግፈግ መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ንግድ ባንኮች ራሳቸውን ጫና ውስጥ የከተቱበት ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 89ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ ቡድኑን ከሽንፈት ያልታደገች ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሊጉ መሪ ንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በአስተያየታቸው ያሰብነውን አላሳካንም፣ ጥንቃቄ መርጠን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ብናስብም ራሳችን በሰራነው ስህተት ጎል ተቆጥሮብናል ሲሉ ያም ቢሆን ሜዳ ላይ ቡድናቸው ጥሩ እንደነበር አንስተው በቀሪ ጨዋታዎች ቡድኑን በሊጉ ለማቆየት ጠንክረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ መጥፎ የሚባል እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን እና በሚፈልጉት መልኩ ጨዋታውን ተቆጣጥረው መውጣታቸውን ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ የመጨረሻው አስር ደቂቃ ውጤት ለማስጠበቅ የማፈግፈግ ሂደቱ በተወሰኑ መልኩ ጫና ውስጥ የከተታቸው ቢሆንም ማሸነፋቸው ጥሩ መሆኑን ጠቁመው በመጨረሻም የዋንጫው ፉክክር ገና መሆኑን እና አምስት ቡድኖች የዋንጫ ዕድሎች እንዳላቸው ተናግረዋል።