ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በድል ግስጋሴው ቀጥሏል

ኢትዮጵያ መድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 በማሸነፍ አራተኛ ተከታታል ድል ሲያስመዘግቡ ፈረሰኞቹ ተከታታይ ሦስተኛ ሽንፈት አስተናግደዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ተገናኝተው ፈረሰኞቹ በ23ኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ አማኑኤል ተርፉ ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ ፣ ዳዊት ተፈራ እና ዳግማዊ አርዓያ ወጥተው ብሩክ ታረቀኝ ፣ በረከት ወልዴ ፣ አላዛር ሳሙኤል እና ተገኑ ተሾመ ገብተዋል። መድኖች በአንጻሩ ሀምበርቾን 2ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ በተመሳሳይ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሰዒድ ሀሰን ፣ አሚር ሙደሲር ፣ አብዲሳ ጀማል እና ጄሮም ፊሊፕን አስወጥተው በርናንድ ኦቼንግ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ብሩክ ሙሉጌታ እና አለን ካይዋን አስገብተዋል።

9፡00 ላይ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግ የመጀመሪያዎቹ የግብ ዕድሎችም 16ኛው እና 17ኛው ደቂቃ ላይ በመድኖች አማካኝነት በቀኝ መስመር ከአብዱልከሪም መሐመድ የተሻገሩትን ኳሶች አንዱን ሚሊዮን ሰለሞን ሳይጠቀምበት ሲቀር ሁለተኛውን ደግሞ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በቀላሉ ይዞበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች አልፎ አልፎ በሚያደርጓቸው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ 23ኛው ደቂቃ ላይም በሄኖክ አዱኛ የቅጣት ምት ሙከራ ተጋጣሚያቸውን መፈተን ሲጀምሩ 33ኛው ደቂቃ ላይም ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ሄኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ዘለቀ በደካማ የግንባር ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እየተቀዛቀዘ በቀጠለው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች 42ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ወገኔ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ብሩክ ሙሉጌታ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ወርቃማውን አጋጣሚ አምክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታውን በጥሩ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች 52ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምሯል። ያሬድ ካሳዬ ከወገኔ ገዛኸኝ የተቀበለውን ኳስ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አሻግሮት ኳሱን ከተከላካዮች ሾልኮ በመውጣት ያገኘው ብሩክ ሙሉጌታ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ፈረሰኞቹ ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተጨዋቾች ቅያሪ በማድረግ መታተራቸውን ሲቀጥሉ 73ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተገኑ ተሾመ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በድንቅ ቅልጥፍና ነክቶት ኳሱ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቷል።

በውጥረት በተሞሉ የመጨረሻ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ብረቱ ፉክክር ሲደረግ ኢትዮጵያ መድኖች 87ኛው ደቂቃ ላይ በያሬድ ካሳዬ አማካኝነት ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ሲመለስባቸው 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጄሮም ፊሊፕ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ አባክኖታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱም ለኢትዮጵያ መድን ተከታታይ አራተኛ ድል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ተከታታይ ሦስተኛ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ቡድናቸው በውጤት ረገድ መሻሻል ላይ ቢገኝም የቡድናቸው እንቅስቃሴ እሳቸው በሚፈልጉት መንገድ እንዳልሆነ በመጠቆም የተጫዋቾቻቸው የስነልቦና ደረጃ ያን ያህል ጠንካራ እንዳልሆነ ሆኖም ማሸፋቸው በቂ እንደሆነ ሀሳባቸውን ሲሰጡ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ደረጄ ተስፋዬ በበኩላቸው በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዳልነበራቸው ገልጸው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ይቀዛቀዙ እንጂ ቀስ በቀስ ወደ ጠንካራ እንቅስቃሴ መምጣታቸውን በመጠቆም በተለይም በረከት ወልዴን በሚጠብቁበት ብቃት ልክ እንዳላገኙት ገልጸው የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ቢገኙም ቶሎ ማገገም እንደሚችሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።