መረጃዎች| 96ኛ የጨዋታ ቀን

በ24ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎችን አስመልክተን ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ መድን

በ ሰላሣ ዘጠኝ ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዋና አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኛቸው ካገዱ በኋላ የመጀመሪያው ጨዋታቸው ያከናውናሉ።

ከድል ጋር ከተኳረፉ አምስት ሳምንታት ያስቆጠሩት ፈረሰኞቹ ከ 83 የሊግ ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች አስተናግደዋል። በ2014 የውድድር ዓመት በሲዳማ ቡናና ሀድያ ሆሳዕና ተከታታይ ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ለዓመታት ተከታታይ ሽንፈት ሳይቀምስ የቆየው ቡድኑ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ መጥፎ ክብረ ወሰን ላለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።

ፈረሰኞቹ በተከታታይ ባካሄዷቸው አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ ማሳካት የቻሉት ሁለቱን ብቻ ነው፤ ይህንን ተከትሎም ደረጃቸው አሽቆልቁሏል። ከሰባት ሳምንታት በፊት ሊጉን ከመምራት ላይ የነበረው ቡድኑ አሁን ከመሪው ንግድ ባንክ በሰባት ነጥብ ለመራቅ ተገዷል። በነገው ጨዋታም በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ያላቸውን ዕድል ጨርሶ እንዳይጠፋ ከማሸነፍ ውጪ ያለ ውጤት ትርፋማ አያደርጋቸውም።

ከተጋጣሚያቸው በተለየ ስድስት ሽንፈት አልባ ሳምንታት፤ ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው በጥሩ የማሸነፍ ስነ-ልቦና ያሉት ኢትዮጵያ መድኖች በሁሉም መመዘኛዎች ተሻሽለዋል።

በርካታ ዝውውሮች አድርገው በጥልቀትም ይሁን በጥራት ላቅ ያለ ስብስብ የገነቡት መድኖች ተከታታይ ድሎች ባስመዘገቡበት ወቅት በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ አመርቂ ቁጥሮች አስመዝግበዋል። ከዚ ቀደም ከቡድኑ ደካማ ጎኖች አንዱ የነበረው የተከላካይ ክፍል በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ በአማካይ ሁለት ግቦች ካስተናገደበት ወቅት በኋላ ባካሄዳቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ በቡድኑ መልካም ጉዞ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ከዚ በተጨማሪ በመጨረዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመርም ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ ነው፤ ሆኖም ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ የግብ ዕድሎች አባክኖ ቡድኑን ጫና ውስጥ የከተተው የአፈፃፀም ችግራቸው በነገው ጨዋታ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ያሰጋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉና ሞሰስ አዶ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 26 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 19 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 50 ጎሎች ፣ 2 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከሳምንታት በፊት ያሳዩት ጥሩ ብቃት ከቅርብ ተፎካካርያቸው መድን የነበራቸው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችለው የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በወሳኝ ወቅት ያስተናገዷቸው ተከታታይ ሽንፈቶች የመትረፍ ዕድላቸው አጥብቦታል። ወልቂጤ ከተማዎች በ13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ብሏል፤ እስከ መጨረሻ ሳምንታት በፉክክሩ ለመቆየትም በውድድር ዓመቱ ጥቂት ሽንፈቶች ካስተናገደው የሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ነጥብ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ስምንት ግቦች ያስተናገዱት ሰራተኞቹ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በቅድምያ የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው ሁለት ነጥቦች የጣሉት የሊጉ መሪ ንግድ ባንኮች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ንግድ ባንኮች በሊጉ አርባ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ የፊት መስራቸው ጥንካሬውን ማስቀጠሉ ቡድኑ ለዋንጫ እንዲታጭ ከሚያደርጉ ነጥቦች አንዱ ነው፤ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አስር ግቦች ያዘነበው ይህ ጥምረት በነገው ዕለት የተጋጣሚው ትልቅ ፈተና እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው። የሊጉ ጠንካራው የፊት ጥምረት የነገው ተጋጣሚው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ስምንት ግቦች ያስተናገደ እንደመሆኑ ግቦች ለማስቆጠር ይቸገራል ተብሎ አይታሰብም፤ ሆኖም የሰራተኞቹ የመሀል ሜዳ ጥንካሬ ጨዋታውን ሌላ መልክ ሊያስይዘው የሚችልበት ዕድልም አለ። በውድድር ዓመቱ አብዛኞቹ ጨዋታዎች ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረገው የወልቂጤ ከተማ አማካይ ክፍል ለወትሮ የሚታወቅበት አቀራረብ ከመረጠ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሊቸገሩ ይችላሉ። ይህ እንዲሆን ግን ከአማካይ ክፍሉ በተጨማሪ መረቡን ማስከበር ያቃተው የሰራተኞቹ የኋላ ክፍል ከጠንካራው የሀምራዊ ለባሾቹ አጥቂዎች የሚጠብቀው ከባድ ፈተና መቋቋም ሲችል ነው።

በመሪነቱ ለመደላደል አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡት ንግድ ባንኮች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ በተለመደው የመስመሮችና የሽግግር አጨዋወት በሙሉ አቅማቸው አጥቅተው ይጫወታሉ ተብሎ ሲገመት ከተከታዮቻቸው ቀድመው መጫወታቸውም ከፍ ባለ የስነ-ልቦና ደረጃ ለመጫወት ይረዳቸዋል ተብሎ ይታመናል።

በወልቂጤ ከተማ በኩል ቅጣት ላይ የነበሩት ዳንኤል ደምሱ እና ወንድማገኝ ማዕረግ ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ግን አሁንም በቅጣት ምክንያት በጨዋታው አይሳተፍም። በንግድ ባንክ በኩልም በተመሳሳይ ተከላካዩ ካሌብ አማንክዋህ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም።

ዘንድሮ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።