ቆይታ ከተስፈኛው ታዳጊ ዱሬሳ ሹቢሳ ጋር…

በዛሬው የተስፈኞች አምዳችን ላይ ከፈጣኑ ሁለገብ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ዱሬሳ ሹቢሳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል ።

ሻሸመኔ ካፈራቻቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ታዳጊው ዱሬሳ ሹቤሳ በሻሸመኔ በሚገኝ ፕሮጀክት ነው የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው። በመላው ኦሮሚያ ውድድር ላይ በአሰላ ፉድ ኮምፕሌክስ መመረጥ የቻለው ዱሬሳ ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ወደ አዳማ ከተማ በማምራት እጅግ ስኬታማ የነበረ ቤሔራዊ ቡድን እስከመጠራት ያደረሰውን የውድድር ጊዜ አሳልፏል። በአዳማ ከተማ 2012 ላይ ወደ ዋናው ቡድን ካዳገ በኋላ ወደ አሪሲ ነገሌ በውሰት በመሄድ በኮሮኖ ምክንያት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በአርሲ ነገሌ ሱፐር ሊጉ ላይ መልካም የሚባል ቆይታን አድርጓል። ዱሬሳ ሹቢሳ ስላሳለፈው የእግርኳስ ህይወት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል ።

የእግርኳስ ዕድገትህ ?

ተወልጄ ያደግኩት በሻሸመኔ ከተማ ነው። እግርኳስን የጀመርኩት እንደማንኛውም ኳስ ተጫዋች ሠፈር ውስጥ ነው። ከዛ ለፕሮጀክት ተመርጬ በሻሸመኔ ሚሽን ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር የምሰራው ፤ ከእነጫላ ተሺታ ጋር። እዛ ቡድን ውስጥ አምስት ስድስት ዓመት ቆይቼ ወደ ታዳጊ ቡድን እንድመጣ ያደረገኝም እሱ ነው። ሻሸመኔ ሚሽን 04  በኋላ መላው ኢትዮጵያ ነው የተጫወትኩት። ኦሮሚያን ወክዬ መላው ኢትዮጵያ ከተጫወትኩ በኋላ ነው ወደ አሰላ ፉድ ኮንፕሌክስ ያመራሁት። አሰላ በነበርኩበት ጊዜ በርካታ ችግሮችን አሳልፈናል። ከዛም ወደ አዳማ ከተማ ታዳጊ ቡድን አመራሁ። አዳማ ከተማ ታዳጊ ቡድን ጥሩ የሚበል ጊዜን ካሳለፍኩ በኋላ ወደ ዋናው ቡድን አሳድገውኝ ወደ አርሲ ነገሌ ከፍተኛ ሊግ አመራሁ። አሪሲ ነገሌ ላይ በርካታ ጨዋታዎችን የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆኜ ነው የተጫወትኩት። ለሊጉ አዲስ እንደመሆኔም ትንሽ ጉዳት አስቸግሮኝ ነበር። ከተቋረጠ በኋላ ግን አገግሜ አሁን በግሌ እየሰራሁ ነው ያለሁት ።

ከቤተሰብ ድጋፍ ያደርግልህ የነበረ ሰው ?

ያው እንደማንኛውም ወላጅ ትምህርት ላይ ትኩረት እንዳደርግ ነው የሚፈልጉ የነበርው ፤ ግን አይቃወሙኝም። አምቦ ዩኒቨርስቲ ነበረኩ። ግን ትቼው ሙሉ ለሙሉ ትኩረቴን ወደ ኳስ አደረኩኝ። በርግጥ አሁንም በኤክስቴንሽን አካውንቲንግ እማራለሁ ፤ አዳማ ጅኔስ ላንድ እየተማርኩ እገኛለሁ። ከቤተሰብ በጣም ድጋፍ የሚያደርግልኝ ሲያድን ሹቢሳ የሚባለው ታላቅ ወንድሜ ነው ፤ በጣም ነው ድጋፍ ያደርግልኛል።

የአዳማ ከተማ ቆይታህ ?

አዳማ ከተማ ያሰለፍኩት ጊዜ በጣም ስኬታማ ነበር። የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አግቢም ነበርኩ። ባይሳካም ቤሔራዊ ቡድን ተመርጬ ነበር። ከዛም ወደ ዋናው ቡድን ካደግኩ በኋላ ወደ አራት ዓመት ፈርሜ ወደ ሱፐር ሊግ በውሰት ሄድኩ። ሱፐር ሊግ እንደነገርኩህ ጥሩ ጊዜ ነበር ፤ የመጀመሪያ ተሰላፊ ነበርኩ። ግን አሰልጣኙ ለየት ያለ ሚና ነበር የሰጠኝ ፤ ከአጥቂ ጀርባ ነበር የሚያሰልፈኝ። ግብ አላስቆጠርኩም ግን ለጎል የሚሆኑ ብዙ ኳሶችን ማቀበል ችዬ ነበር። ከነበርኩበት ክለቦች አሪሲ ነገሌ ትንሽ የተሻለ ነበር። በክፍያ አዳማ እያለን በጣም ብዙ ችግር ነበር። የተስፋ ደመወዝ አነስተኛ ነው። ከቤተሰብ ጋር አንኖርም ፤ ተከራይተን ነበር የምንኖረው። በጣም ፈታኝ ወቅት ነበር። በዛ ሰዓት ከጎኔ የነበረው በረከት ደስታ ነበር። በጣም ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር። በጣም ብዙ ፈተናዎች በነበሩበት ሰዓት ከጎኔ የነበረው እሱ ነበር ፤ ጫላ ተሺታም ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር። ወጣቶች በጣም ብዙ ፈተና ሊያሳልፉ ይችላሉ። ለተስፋ ተጫዋች ያለው ትኩረት በጣም ትንሽ ነው። ስለዚህ ያለውን ችግር እንደምንም ተቋቁመው አንዲያልፉ እመክራለሁ ።

ትልቅ ቦታ የምትሰጣቸው ?

መስፍን አበበ ሻሸመኔ ኳስ እንድጀምር ያደረገኝ ትልቅ አሰልጣኝ ነው። በጣም ብዙ ነገር አድርጎልኛል እና አዳማ እንድመጣ ያደረገኝ አሰልጣኝ ጋሽ ምትኩ ፍቃደ በጣም ለኔ ትልቅ ቦታ አላቸው።

የወደፊት ግብህ ?

ወደፊት ግቤ እንደማንኛውም ተጫዋች ሀገሬን በትልቅ ደረጃ ማገልገል ነው። በትልቅ ደረጃ መጫወት እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያን መለያ ለብሼ የሀገሬን እግርኳስ አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ። በግሌ ከሀገር ወጥቼ መጫወት እፈልጋለሁ። አውሮፓ ሄዶ የመጫወት ግብ ነው ያለኝ።

አርዓያ የሆነህ ተጫዋች ?

ሀገር ውስጥ የማደንቀው አርዓያዬ እና በጣም የምወደው ተጫዋች ሳልሃዲን ሰዒድ ነው። በቦታዬ እንደ ሳልሃዲን ሰዒድ መሆን እፈልጋለሁ። ከሀገር ውጪ የክርስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ