የኢትዮጵያ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድር ላይ አይሳተፉም?

በዚህ የውድድር ዓመት በካፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦች እንደሌሉ ቢወሰንም በቀጣይ የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ውድድሮች ላይ የመሳተፋቸው ነገር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ በትላንትናው እለት የ2020/21 የቻምፒየንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ውድድሮች የሚደረጉበትን የጊዜ ሰሌዳ አስታውቋል። ካፍ መርሐ-ግብሩን ሲያወጣ ጎን ለጎን በተሳታፊ ክለቦች አግባብነት ጋር በተያያዘ ያስተላለፈው ኮስታራ መልዕክት ለበርካታ የአህጉሪቱ ክለቦች የራስ ምታት የሚያመጣ ይመስላል። በተለይ በብዙ የመመዘኛ መስፈርቶች አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የሚያስችላቸው ቁመና የሌላቸው የሃገራችን ክለቦች አጣብቂኝ ውስጥ የሚገቡ ይመስላል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ጋር በመሆን በኮቪድ-19 ምክንያት የተቋረጠው የዘንድሮ የውድድር ዘመን እንዲሰረዝ እና በቀጣይ ዓመት በካፍ የቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ዋንጫዎች ላይ የሚሳተፍ ክለብ እንዳይኖር መወሰኑ ይታወቃል። ይህ ቢሆንም ግን ካፍ በ2020/21 በሚደረጉት እነዚህ ሁለት የአህጉሪቱ ትልቅ የክለቦች ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን የእግርኳስ ፌዴሬሽኖች እስከ ጥቅምት 10 እንዲያሳውቁ የጊዜ ገደብ ሰጥቷል። ይህንን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ እና የሊግ ካምፓኒው ሃሳባቸውን ቀይረው በውድድሮቹ ተሳታፊዎች እንዲኖሩ ቢፈቅዱ እንኳ ክለቦቻችን በውድድሩ ላይ የመሳተፋቸው እድል ጠባብ ይመስላል።

ካፍ በቅርብ ዓመታት በክለብ ላይሰንሲንግ ጉዳይ ላይ የተለያዩ መስፈርቶችን አውጥቶ በየሃገሩ የሚገኙ ክለቦች መስፈርቶቹን እንዲያሟሉ ማዘዙ ይታወቃል። እርግጥ መስፈርቶቹ ቢወጡም በአህጉራችን ካሉ ደካማ ክለቦች አንፃር ካፍ ጉዳዩን አለዝቦት ቆይቷል። ነገርግን ትናንት የቀጣይ ዓመት የውድድሮቹ የጊዜ ሰሌዳን ሲያወጣ በአህመድ አህመድ የሚመራው ተቋም በጉዳዩ ላይ ኮስታራ አቋም እንዳለው አስታውቋል። ይህንን መልዕክት ይዘንም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ሃላፊ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ አቅርበናል።

“በካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርት መሰረት 5 ነጥቦች በዋናነት ተቀምጠዋል። እነሱም ስፖርታዊ መስፈርት (የእድሜ ቡድኖችን በሁለቱም ፆታ የመያዝ)፣ ህጋዊነት፣ መሠረተ ልማት፣ አስተዳደራዊ መዋቅር እና የገንዘብ አቅም የሚሉ ናቸው። እነዚህ አምስት ነጥቦች የየራሳቸው የሆነ ነጥብ አላቸው። ለምሳሌ መሠረተ ልማትን በተመለከተ ክለቦች ያላቸው ነገር ከ25% እንዲታይ ይደረጋል። ከመመስረቻ መነሻ ሰነድ ጀምሮ ያለ የክለቡ ህጋዊ ቁመና ጋር በተያያዘ ደግሞ ከ12% የሚያዝ ነጥብ አለ። እነዚህ እና በውስጣቸው ያሉ መስፈርቶች ታይተው ከ79% በላይ ያሟሉ ክለቦች ላይሰንሱን ይወስዳሉ።

“በአጠቃላይ 4 ደረጃዎች አሉ። አንደኛው ከ79% በላይ የሚያገኙ ክለቦች ላይሰንሱን በቀጥታ እንዲወስዱ ይደረጋል፣ ሁለተኛው ላይ ያሉ ደግሞ በጊዜ በማስጠንቀቂያ እንዲወስዱ ሲደረግ በሦስተኛው ደረጃ ያሉ ክለቦች በበኩላቸው በዚህ ጊዜ ይወስዳሉ ተብሎ የሚቀመጥ ነው። የመጨረሻው ደረጃ ላይ የተቀመጠ ክለብ ግን ምንም ግልጋሎት እንዳያገኝ ይደረጋል። እነዚህን የእኛ ሃገር ክለቦች ያሟላሉ የሚለው ማሰብ እና የትኛው ደረጃ ላይ ናቸው የሚለውን መጠየቅ ምላሹን ይሰጠናል።

“እኛ እንቅስቃሴያችን የነበረው ክለቦቹ የተቀመጡትን መስፈርቶች እንዲያሟሉ ነው። አሁን ላይ ኮቪድ-19 መጥቶ አቋረጠን እንጂ ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነበር። በተለይ የስታዲየሞችን አግባብነት ተከታትለን ወደ ሌላኛው መስፈርት ልናመራ ስንል ስራዎች ተስተጓጎሉ። ከዚህ መነሻነት የክለቦቹን አግባብነት ሙሉ ለሙሉ አጣርተን አልጨረስንም። ነጥብም አልሰራንም። ስለዚህ ይህ ክለብ ያሟላል ይህ አያሟላም ማለት አልችልም።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!