ስለ ይልማ ተስፋዬ (ካቻማሊ) ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

ኳስ በእግሩ ሲገባ ቀንሶ አልፎ ከሮጠ እርሱን ማቆም አዳጋች ነው፤ በትልልቅ ክለቦች በዋንጫ የተጀበ የስኬት ዓመታትን አሳልፏል፤ ብዙ መጫወት እያቻለ በአሳዛኝ ሁኔታ በድንገት በጉዳት ሳይጠገብ እግርኳስን ለማቆም ተገዷል። አጥቂ እና ተከላካይ በመሆን ሲጫወት የምናውቀው የዘጠናዎቹ ጀግና ይልማ ተስፋዬ (ካቻማሊ) ማነው?

የጣልያኑ የከባድ መኪኖች አምራች የሆው አይቬኮ ኩባንያ የሚያመርተውና አርባ አምስት ሰው በወንበር የመጫን አቅም ያለው የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በአዲስ አበባ እና በክልል ጎዳናዎች ከዘጠናዎቹ መጀመርያ አንስቶ እየተዘዋወረ ለህብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ባለ ውለታ ሆኗል። የዚህም መኪና ስም ካቻማሊ ይባላል። ያለ ምክንያት የዚህን ጠንካራ መኪና አገልግሎት ለማንሳት አልፈለግንም። በወቅቱ በተክለ ቁመናው ረዝም ያለ ፈጣን ስለነበረ ስለአንድ በዘጠናዎቹ ውስጥ ስለተፈጠረው ድንቅ እግርኳሰኛ ልናወራቹ ወደን ነው።

ስሙ ይልማ ተስፋዬ ይባላል። የተወለደው ከአዲስ አበባ 480 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው እና አነስ ያለች ከተማ በሆነችው በክብረ መንግሥት ከተማ ነው። ከተማዋ በጣም ቆንጆ እና የፍቅር ከተማ ነች። የዛ አካባቢ ሰዎች የአዶላ ወዩ በሚል ስያማዋ ይጠሯታል። ይህንን ተቀፅላ እንደ ሌላ የከተማዋ ስምም ይጠቀሙታል። ይህን ኮከብ ተጫዋች ያስገኘችው ይህች ከተማ ሁሌም በቤተሰብ ዘንድ ተቧድነው ከሌላ ሠፈር አካባቢ ልጆች ጋር የሚጫወቱ የአቶ ተስፋዬ ልጆች ነበሩ። የእርሱ ታላላቅ ወንድሞች በጊዜው ጥሩ ተጫዋቾች ሆነው ሳለ ገፍተው ባይሄዱበትም ይህ ተጫዋች ቤተሰቦቹ ገፋፍተው እና እነሱን በማየት ወደ እግርኳስ ዓለም ገብቷል። በዚህ ያላቆመው ፈጣኑ ካቻማሊ የስምተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ታላቅ ወንድሙ ጋር ሻሸመኔ ከተማ በመሄድ ትምህርቱን እየተከታለ ጎን ለጎን ለክፍል ቡድኖች በሚጫወትበት ወቅት ጎል የማስቆጠር አቅሙን የተመለከቱ አሁን በህይወት የማይገኙት አሰልጣኝ ደጀኔ ጫካ ለሻሸመኔ ከነማ እንዲጫወት አድርገውታል።

በ1988 በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ቀደምት ክለብ በመሆን እና ለብዙ ትውልዶችም ሆነ ተጫዋቾች መፈጠር ምክንያት የሆነው ሀዋሳ ዱቄት ሻሸመኔ ከተማ ለዝግጅት መጥቶ ለወዳጅነት ጨዋታ ከይልማ ተስፋዬ ቡድን ሻሸመኔ ጋር ሲጫወት የተመለከቱት አሰልጣኝ ጋሽ አዳነ ገብረየሱስ ወደ ቡድናቸው ቀላቅለው እንዲጫወት አድርገውታል። ካቻማሌ ለአንድ ዓመት ብቻ በዱቄት በቆየበት ጊዜ ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ዱቄትን ወክሎ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት እጅግ አስገራሚ እንቅስቃሴ በማድረግ እና ጎል በማስቆጠር ከመንግሥት ለውጥ በኃላ አንድ የክልል ቡድን በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ እንዲሳተፍ በማድረግ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር። በወቅቱም ውድድር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል።

ይልማ ተስፋዬ በጥሎ ማለፍ ዋንጫ ላይ ባሰየው መልካም እንቅስቃሴ የብዙዎች የአዲስ አበባ ክለቦች እርሱን ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖራቸውም ምርጫውን የእግርኳሱ ሰው ጋሽ መንግሥቱ ወርቁ ጋር በማድረግ ለሁለት ዓመታት (ከ1989 መጨረሻ አንስቶ እስከ 1991) ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጫውቷል። እንደ ቡድን ውጤታማ ባይሆንም በግሉ በሚያደርገው ጥሩ እንቅስቃሴ ለብሔራዊ ቡድን ለመጫወት የቻለው ካቻማሊ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲጫወት ክፍያ ቢፈፀምለትም በድጋሚ ጋሽ መንግሥቱ ወርቁ ጋር ለመስራት ካለው ፍላጎት የተነሳ የተቀበለውን ብር መልሶ በ1992 ለአንድ ዓመት ቆይታ ብቻ ለኢትዮጵያ መድን መጫወት ችሏል። በመድን ቤትም ያላሰበው ገጥሞት ቡድኑ በብዙ መንገድ ትክክል ያልሆኑ አካሄዶች ሲገጥሙት የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ መድንን በመልቀቅ በአሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ወደሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1993 አምርቷል።

በሀዋሳ ዱቄት፣ አየር መንገድ እና መድን ይልማ የአጥቂ ሥፍራ ተጫዋች የነበረ ቢሆንም ተክለ ሰውነቱን፣ የሸርተቴ አጨዋወቱን፣ ጥሩ የግንባር ኳስ አጠቃቀሙን፣ ፍጥነቱን፣ ጉልበቱን እና የማስተዋል አጨዋወቱን የተመለከቱት አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ወደ ኋላ በመመለስ ከብርሐኑ ፈይሳ (ፈየራ) ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ጠንካራ የተከላካይ መገንባታቸው ይታወሳል። ይህ ጥምረትም በጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ቡድንም ጭምር የተሳካ እንደነበረ ይታወቃል። ፈጣኑ፣ እለህኛው፣ ሜዳ ላይ ቀልድ የማያውቀው፣ ያለውን ነገር ሁሉ ለለበሰው መለያ የሚሰጠው አመለሸጋው ይልማ ተስፋዬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በ1993 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ፣ በ1994 እና 1995 ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ፣ በ1996 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እንዲሁም የሴካፋ የክለቦች ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነሐስ ሜዳልያን በማጥለቅ ታሪክ መስራት የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነው።

በክለብም በብሔራዊ ቡድንም አብሮት በመጣመር የተጫወተው ብርሀኑ ፈይሳ (ፈየራ) ስለ ይልማ እንዲህ በማለት ይናገራል ” ካቻ ይህ ነው የማትለው ከተክለ ሰውነቱ ጀምሮ ለተከላካይነት የሚመጥን፣ በጣም ትልቅ፣ ጎበዝ ተጫዋች ነው። ብዙ ጊዜ አብረን ስላሳለፍን በብሔራዊ ቡድን በነበርንበት ወቅት ለአሰልጣኝ አሥራትን ነግሬው ከአየር መንገድ ድልድይ ሆኜ እንዲመጣ በማድረግ በሳንጆርጅ በጥሩ ጥምረት አሳልፈናል። እኔ እንዳውም በብዙ ነገር ፕሮፌሽናል ይሆናል ብዬ በትልቁ የማስበው ካቻን ነበር። በማኅበራዊ ሕይወቱም ከሰው ጋር ተግባቢ፣ ለሰው አዛኝ፣ ተቆርቋሪ የሆነ መልካም ሰው ነው።” ይለዋል።

በእግርኳስ ዘመኑ በተጫወተባቸው አራት ክለቦች በአመዛኙ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ከነጉዳቱ ሳይቀር ያለ እረፍት በከፍተኛ ወኔ ተጫውቷል። ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ አበርክቶ የነበረው ካቻማሊ በ1994 ብሔራዊ ቡድናችን ከሀገር ውጭ ሩዋንዳ ሄዶ የሴካፋ ዋንጫ ሲያነሳ የኃላ ደጀን በመሆን ባለፈ ከነደሙ (ቁስሉ) ለሀገሩ የተጋደለ ጀግና ተጫዋች እንደነበረ ይታወቃል።

ሌላኛው በቅዱስ ጊዮርጊስ አብሮት የተጫወተው የዘሪሁን ሸንገታ ስለ ይልማ ተስፋዬ ሲናገር ” ካቻ ከኔ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለ። እኔ ከአጥቂ ወደ ተከላካይነት እንደመጣሁት ሁሉ እርሱም ከአጥቂነት ወደ ተከላከይ ነው የመጣው። ካቻ ለለበሰው ማልያ ሟች የነበረ፣ በጣም ፈጣን፣ ሜዳ ላይ ቀልድ የማያውቅ፣ ሥራውን አክብሮ የሚጫወት፣ ከሜዳ ውጭ ሰው መርዳት የሚወድ፣ ትሁት ሰው አክባሪ በጣም ጥሩ ስብዕና ያለው ሰው ነው።”

ችሎታው እየጎመራ በትልቅ ስኬት በዋንጫ የጀመረው የእግርኳስ ሕይወቱ ድርብ ድርብርብ ሆኖ ይቀጥላል በሚል በብዙዎች ተስፋ ቢጣልበትም በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ እግርኳሱ ዓለም ላይመለስ ባሳዛኝ ሁኔታ በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ተጫውቶ ሳይጠግብ እግርኳስን ለማቆም ተገዷል።

በአሁኑ ወቅት ኑሮውን በደቡብ አፍሪካ በማድረግ ቤተሰብ መስርቶ በተሻለ ሕይወት በንግዱ ዓለም ተሰማርቶ የሚገኘው ካቻማሊ በቅርቡ የውጭ ሀገር ሊጎችን በአማርኛ ቋንቋ ከኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ጋር በመሆን በዲኤስ ቲቪ የእግርኳስ ተንታኝነት አገልግሎት ሲሰጥ ተመልክተነዋል። ሶከር ኢትዮጵያም የዚህን የዘጠናዎቹ ኮከብ አጥቂ እና ተከላካይ የእግርኳስ ዘመኑን አስመልክታ ካለበት ደቡብ አፍሪካ በስልክ አግኝታ ያደረገችውን ቆይታ በዚህ መልኩ አሰናድተነዋል መልካም ቆይታ

“በመጀመሪያ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ያደረሰኝ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ። በመቀጠል ለሀገራቸው የበኩላቸውን አድርገው ያለፉ ሰዎችን ለመጪው ትውልድ እንዲጠቅም በማሰብ ስለምታስታውሱ ሶከር ኢትዮጵያዎችን ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።

“ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ያስተዋወቀኝ ነገር ሀዋሳ ዱቄት በፈረምኩበት ዓመት እዛው ሀዋሳ ላይ ቻምፒዮን ሆንን። ሀዋሳን ወክለን የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ ሄድን። ቡድኑ ጥሩ አቋም ላይ ስለነበርን አዲስ አበባ ላይም ብዙ ትልልቅ ክለቦችን አሸነፍን። እኔም በዚያ ጊዜ ላይ ነው በጣም የታወቅኩት። ብዙ የአዲስ አበባ ክለቦች ላይ ጎል አስቆጠርኩ። የጥሎ ማለፍ ዋንጫንም አሸነፍን። አሰልጣኜ ጋሽ አዳነ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት ነበራቸው። እንደውም አማካይ ቦታ ላይ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ‘ከፊት ጣሉለት እርሱ ያደርሰዋል’ የሚል አባባል ነበራቸው። ለኔ እዚህ ቦታ መድረስ ትልቅ ቦታ ነበራቸው በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

“አጭር ቢሆንም የእግርኳስ ዘመኔ ስኬታማ የሚባሉ በዋንጫ የታጀቡ እና በእኔም ዘንድ በስፖርት ቤተሰቡ የማይረሱ አስደሳች ስምንት ዓመታትን አሳልፌለው። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ስመጥር አሰልጣኞች መንግሥቱ ወርቁ፣ አሥራት ኃይሌ፣ ሥዩም ከበደ እና ሰውነት ቢሻው ሥር የመሰልጠን እድል አግኝቻለው። በዋንጫም ረገድ በሀገሪቱ አሉ የሚባሉ ትልልቅ ዋንጫዎችን አንስቻለው። ለሀገሬም በታሪክ የመጀመርያውን የሴካፋ ዋንጫ (ከሀገር ውጪ የተገኘ) በሁሉም ጨዋታዎች በመሳተፍ ዋንጫውን ይዘን ወደ ሀገራችን መመለስ ችያለው። ብዙ ድሎችን በቀጣይ በክለብም በብሔራዊ ቡድን ለማሳካት እያሰብኩ ባለሁበት ሁኔታ ማንሳት የማልፈልገው ጉዳት አስተናግጄ እግርኳስን አቆምኩ እንጂ ጥሩ የሚባል የእግርኳስ ስኬት ነበረኝ።

“በ1991 ጊዮርጊስ ለመግባት ከአሰልጣኝ አሥራት ጋር ተነጋግረን ፊርማዬን አኑሬ ደሞዝ መቀበል ከጀመርኩ ወዲህ አየር መንገዶች መልሰው ቋሚ ሥራ እንደሚሰጡኝና እና እንደሚያስተምሩኝ ቃል ገብተው ስላናገሩኝ ከጊዮርጊስ የወሰድኩትን ገንዘብ መልሼ በአየር መንገድ መቆየት ችያለሁ። በዓመቱ ያስመዘገብነው ውጤት ጥሩ የሚባል አልነበረም፤ እኔ በባህሪዬ ደግሞ ሽንፈትን መቀበል አልወድም። በዚህ የተነሳ የዓመቱ ውድድር ሲጠናቀቅ እጅግ የማከብረው አሰልጣኝ መንግሥቱ ወርቁ መድንን እንደያዘና ከእኔ ጋር መስራት እንደሚፈልግ ሲነግረኝ ተስማምቼ ወደ እሱ አቀናሁ። መድንን በሚታወቅበት በወጣቶች ገንብቶ በ1992 ድንቅ ቡድን ገንብቶ አሳይቷል፤ አስታውሳለሁ በመጀመሪያ ጨዋታ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ ቡናን አሸንፈን። ግን በአንድ ወቅት የተወሰኑ የቡድኑ ነባር ተጫዋቾች በቂ የመሰለፍ እድል ባለማግኘታቸው ደስተኛ አልነበሩም። ታድያ ዕድል ሲያገኙም ከአቅም በታች በመጫወት እና የወጣቶችን ሞራል በመንካት የቡድኑ ውጤት እንዲበላሽ አደረጉ። ብዙ ጊዜ መሰል ድርጊት የሚያደርጉ ተጫዋቾች አሉ ፤ በጣም የሚገርመኝ የሚከፍላቸው ክለቡ ሆኖ ሳሉ እነሱ ግን የሚሰሩት ለሚፈልጉት አሰልጣኝ ወይም ኮሚቴ አባላት ብቻ ነው። ታድያ እነዚህ መሰል ማስተዋል የተሳናቸው ተጫዋቾች ሆነ አሰልጣኞች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። በወቅቱ የነበሩ ተጫዋቾች ሊያስታውሱት ይችላሉ በወቅቱ የቡድኑ ኮሚቴዎቹ አሰልጣኝ መንግሥቱን በአሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔር ቢተኩም የተለየ ውጤት ማስመዝገብ አልቻልንም። ይልቁኑ የባሰ አስከፊ ውጤት ነው የተመዘገበዘው። አሰልጣኝ ብርሃኔ የቡድኑን አጨዋወት ለመቀየር ያደረገው ጥረት ነገሮችን ይበልጡኑ ተበላሸ። ከእኔ ጋርም በግል በአጨዋወቱ መግባባት ባለመቻላችን ክረምት ላይ ቡድኑን መልቀቅ እንዳለብኝ ወሰንኩ።

“ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመግባቴ አስቀድሞ በዚያን ወቅት ነብሱን ይማረውና አሰልጣኝ ሥዩም አባተ እና ገብረመድኅን ኃይሌ ለሚያሰለጥኗቸው ቡድኖች እንድጫወት ቢጠይቁኝም እኔ በወቅቱ ትልቁ ፍላጎቴ የነበረው ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ነበርና ጥያቄያቸውን ሳልቀበል ቀርቻለሁ። በተለይም በትራንስ በኩል ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚሰጡኝ ቃል ቢገቡልኝም፤ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ የደጋፊ ማኅበር አመራሮቹ የፊርማ ገንዘብ እንደሚሰጡኝ ቃል ቢገቡልኝም እኔ ግን ምንም መልስ ሳልሰጣቸሁ ቀረሁ። ከብሔራዊ ቡድን መልስ ከአሰልጣኝ አሥራት ሀይሌ ጋር ተገናኝተን አወራን፤ ቀጥዬም በ1993 ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቀልኩ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለው ጠንካራ ስብስብ እና ከፍተኛ ደጋፊዎች አንፃር መጀመሪያ ወደ እዛ ስትገባ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር ቤት ነው። ትልቁ ነገር ከቡድን የተረዳሁት ሁሌም ወደ ጨዋታ ስትሄድ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ የማይቻልበት ቤት ነው። እርግጥ ሁልጊዜም በሀገራችን የሚገኙ አሉ የሚባሉ ተጫዋቾች እንደመያዙ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ስኬታማ መሆኑ የሚገርም አይደለም። ነገርግን በአፍሪካ ውድድሮች ላይ መፎካከር የሚያስችል አቅም ያለው ቡድን ቢሆንም እኔ በቡድኑ በነበርኩበት ወቅት ለዚያ ውድድር ብዙም ሲዘጋጅ አላስተዋልኩም።

“የቦታ መለዋወጥ የተጀመረው ጊዮርጊስ ከገባሁ በኋላ ነው። ከዛ በፊት በመስመር አጥቂነት ነበር የምጫወተው። በጊዜውም አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ጋር እየተነጋገርን ቦታ እየቀየቀየርኩ መጫወት አለብህ ተብዬ በዚህም መሠረት በመስመር ተከላካይነት፣ በመሐል ተከላካይነት እንደገናም እየተመለስኩ አጥቂ እየሆንኩ እጫወት ነበር። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ተከለካይ ሆኜ እንድጫወት ተደረገ። በጊዜው የተለያዩ ቦታዎች ላይ መጫወት ለእኔ አስቸጋሪ አልነበረም። እርግጥ የመሐል ተከላካይ ሆኜ ስጨወት ጥሩ ነበርኩ። ብዙ ደጋፊዎችም እዛ ቦታ ላይ ሆኜ ስጫወት ነበር የሚወዱኝ። አሠልጣኞችም ተከላካይ ስሆን እንደሚዋጣልኝ ስለመከሩኝ ዋና ቦታዬን እዚሁ አድርጌ መጫወት ቀጠልኩ። ሲጀምርም እኔ ወደ ሜዳ ስገባ የማስበው ቡድኔን ውጤት እንዴት አስገኛለሁ የሚለውን ነው እንጂ በዚህ ቦታ ብጫወት የሚለውን አይደለም።

“አልሸነፍ ባይነት ከነጉዳቴ የመጫወቴ ምክንያት ወደ ሜዳ ከገባው ከእኔ የሚጠበቀውን ሙሉ ለሙሉ አውጥቼ ካልተጫወትኩ ያበሳጨኛል። የምችለውን ሁሉ መስዕዋትነት እከፍላለው፤ ከፍያለሁም። ብሔራዊ ቡድን ላይም አንዴ በክርን ተመትቼ ደሜ እየፈሰሰ ወጥቼ ዶክተር መካሹ እና ወጌሻው ዘላለም ‘መሰፋት አለበት ሆስፒታል መሄድ አለብህ’ ሲሉኝ በጣም ጥሩ ቡድን ስለነበረንም ‘ ጨዋታውን መጨረስ ስላለብኝ እዚህ ጋር መስፊያ ካላችሁ ስፉኝ’ ስላቸው ተገረሙ። ከአስር ደቂቃ በላይ ፈጅቶባቸው ሰፍተውኝ በድጋሚ ወደ ሜዳ ተመለስኩ። ጨዋታው ለፍፃሜ ለማለፍ ነበር። ተመልሼ ገብቼ ውጤታችንን አስጠብቀን ወጣን፤ ዋንጫውንም አንስተን ታሪክ ሰራን። ስብስቡ ከመጀመሪያ አሰላለፍ ጀምሮ እስከ ተቀያሪው የሚገርም መተሳሰብ እና እርስ በእርስ የመረዳዳት ነገር ነበረው። በዛን ወቅት ለዛ ቡድን መዕዋትነት በመክፈሌ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፣ጉዳቴን ከምንም አልቆጠርኩትም ነበር።

“በተፈጥሮ የተሰጠኝ ነው ብዬ ነው የማምነው። ሌላው ካደግኩበት ቦታም አንፃር ቤተሰቦቼ ብዙ ከብቶች ነበሯቸው፤ ወተት በጣም እጠቀም ነበር። ታላላቆቼን በማየትም ስፖርት መስራት የጀመርኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ነው። ሌላው ፍራቻ የሚባል ነገር አወላውቅም። ሰው በጣም አከብራለው ትልቅ ትንሽ የለውም፣ የተማረ ያልተማረ አልልም። ሰውን በሰውነቱ አከበራለሁ። ሰው ጋር አልደርስም ሰውም እንዲደርስብኝ አልፈቅድም። እሱ እሱ ተጨማምሮ ይመስለኛል ጥንካሬውን ይበልጥ ያጎላው።

” የኢትዮጵያ አየር መንገድ መበተኑ በጣም ነው የሚያሳዝነኝ። እንደ ተቋም ትልቅ አቅም ቢኖረውም ቡድኑ መቀጠል አለመቻሉ በጣም ያሳዝነኛል፤ እንደእኔ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ እጦት ነው ብዬ አስባለሁ። አሁንም ቢሆን በአመራሮቹ ዘንድ ቁርጠኝነቱ ካለ ቢያንስ ታዳጊዎች ይዞ ሊንቀሳቀስበት የሚችለውን አግባብ መፍጠር ይቻላል ብዬ አስባለሁ። በዘመናዊ አደረጃጀት ታዳጊዎች ላይ ቢሰራ ለሀገሪቷ ስፖርት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል።

” ካቻማሊ የሚለው ስም የወጣልኝ ዱቄት እያለው ነው። ባህርዳር ሄደን ለጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሼ ግብ አስቆጠርኩ። ይህችን ግብ ሳስቆጥር ከመሀል ሜዳ ረጅም ርቀት በከፍተኛ ሩጫ አድርጌ ተከላካዮችን አልፌ ነበር ግቡን ያስቆጠርኩት። ታድያ በዚች ግብ አሸንፈን ከወጣን በኃላ ምሽት ላይ አንድ ቤት እራት እየበላን አንድ የተጋጣሚያችን የባሌ ፖሊስ ተጫዋች ከአንድ የእኛ ቡድን ተጫዋች ጋር ትውውቅ ስለነበራቸው ከኔ ጋር ሲያስተዋውቀን ‘ይህ ልጅ እኮ ነው ቅድም ግቡን ያስቆጠረው ሲለው እንዴ ይሄማ ካቻማሊ አይደል እንዴ’ ሲል የእኛ ተጫዋቾች ሰሙና በዛው ስሙ መጠርያዬ ሆኖ ቀጠለ። በዚያን ወቅት አንድ ‘ካቻማሊ’ የሚባል ሀገር አቋራጭ መኪና ነበር። በጣም ፈጣን እና ጉልበተኛ መኪና ነበር። እሱን አስታኮ ነው ያ ልጅ ይህን ስም ያወጣልኝ።

“በተጫዋችነቴ የማዝነው ማስታወስ የማልፈልገውን ጉዳት ጉልበቴ ላይ አስተናገድኩበት ገጠመኝ ነው። በወቅቱም እረፍት ከማጣት ይመስለኛል ግጭት መቋቋም ያቃተኝ። ምክንያቱም በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሁሌ ቀዳሚ እየሆንኩ ነበር ያለ እረፍት የምጫወተው። በተጨማሪም ስጫወት ብዙ ራሴን አልጠብቅም መሰለኝ ብቻ በከባድ ግጭት ከባድ ጉዳት አስተናገድኩ። እግርኳስን ሳልጠግበው ያለያየኝ ትልቅ ጉዳት ነበር። እንዳልኩት ሁሌ ቋሚ ስለምሆን ብዙም እረፍት ሳላደርግበት ተመልሼ ወደ ሜዳ ገብቼ መጫወት ቀጠልኩ። ግን ጉዳቱ ሳይሻለኝ ስለሆነ ወደ ሜዳ የተመለስኩት የባሰ ችግር እግሬ ላይ ተከሰተ። ደቡብ አፍሪካ ህክምና ወስጄ ብመለስም ዳግም ወደ እግርኳስ እንዳልመለስ ዶክተሩ የነገረኝ ዕለት ሁሌም የማረሳው አሳዛኝ ገጠመኝ ነው።

“ጉዳት ያጋጠመኝ አርባምንጭ ላይ በነበረ ጨዋታ ነው። የጎዳኝ የአርባምንጭ ተጫዋች አጨዋወቱ በፍፁም ትክክል አልነበረም። የፍራቻ አገባብ ይመስለኛል፤ ዓይኑን ጨፍኖ ነው የገባብኝ ማለት ይቻላል። እግሩን ሰንዝሮ በታኬታው ጡት ቀጥታ ነው ጉልበቴ ላይ የቆመው። እግሬ የሰውነቴ ክብደት በሙሉ አርፎበት ስለነበር በጣም ነው የተጎዳው። ነገር ግን ከሜዳ ወጥቼ የህክምና ዕርዳታ እየተደረገልኝ እያለ በጣም ተበሳጭቼ ስለነበር እያመመኝ ተመልሼ ወደ ሜዳ ገብቻለው። እና ስፖርቱ የማይፈቅደውን ያልተገባ ስህተት ሰራሁ፤ በእርግጥ ግርግር ስለነበር ዳኛውም አላየኝም። ያንን ካደረኩኝ በኋላ በጣም እያመመኝ ስለነበር ቅያሪም አልጠበኩም በዛው ወጣው። ከአርባምንጭ መልስ አንድ ሁለት ሣምንት እረፍት አደረኩ። ቀጣዩ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስለነበር ካለውም ፉክክር አንፃር ገባሁ። ጨዋታውንም ጨርሼ ወጣው፤ እኛም አሸነፍን። ከዛ በኋላ ጊዮርጊስ ከአንድ ትራንዚት ያደርግ ከነበረ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርግ ነበር። እዛ ጨዋታ ላይ ገብቼ እዛው ቦታ ላይ መጠነኛ ግጭት ሲገጥመኝ እግሬ ተናጋ። ልክ ስሜቱ ሲሰማኝ እንደመጀመሪያው ሁሉ ከሜዳ ወጣው። ከዚህ ጨዋታ በኋላ ዩጋንዳ ላይ ጊዮርጊስ የሴካፋ ውድድር ስለነበረበት ወደዛ ሄድኩ። ሴካፋ ላይም ተመሳሳይ ቦታ ላይ ሁለቴ ግጭት ገጠመኝ። ከዚያ በኋላ ግን ለግንባር ኳስ ዘልዬ መሬት ላይ ሳርፍ እግሬ ይከዳኝ ጀመር። ስሜቱ ከባድ ነበር፤ ለሰከንዶች ራሴን እስትም ነበር። እንደዛም ሆኖ ግን እየተጫወትኩ ነበር። በዛው ውድድር በሌላ ጨዋታ ላይ የኛ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ አንድ አጥቂ ኳስ ወደ ግብ ሊመታ ሲል ተንሸራትቼ ኳሱን ሳስጥለው ለኳሱ በሰነዘረው እግሩ እዛው የተጎዳውበት ቦታ ላይ አገኘኝና በጣም አመመኝ። ራሴን ስቼም ከሜዳው ውጪ ህክምና እየተደረገልኝ ስነቃ እኛ ላይ ጎል ሲቆጠር አየሁ። ያ ጨዋታ የመጨረሻዬ ሆነ። ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ከካምፕ ወጣው። የጥቁር አንበሳ እና ያኔ የብሔራዊ ቡድን ዶክተር ከነበረው ዶ /ር መካሹ ጋር እግባባ ስለነበር እሱ ጋር ሄድኩና አንድ ሦስት ዶክተሮች ሆነው እግሬን አዩት። ሆኖም ያኔ ቴክኖሎጂውም ስላልነበር ከአንድ ወር በኋላ ሊያዩት ጀሶ ታሰረልኝ። ነገር ግን ሳምንት ሳይሞላ አቶ አብነት ከእንግሊዝ ሲመለስ ቤቴን ጠይቆ ያለሁበት መጥቶ አየኝ ። ‘እንዴት እግርህ ላይ የግምት ሥራ ታሰራለህ ?’ ብሎ ተቆጣ ፤ በሳምንት ውስጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ህክምና እንዳገኝም አደረገ።

“በዛ ሰዓት ጉዳቱ በጣም ከባድ ጉዳት ነበር። ሃገር ውስጠረም መታከም የሚቻል አልነበረም። ከዛ የቡድን መሪያችን እና የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ወደ ደቡብ አፍሪካ መሄድ አለበት ብለው ወሰኑ። ወዲያም ወደ ሥፍራው እንድሄድ ተደረገ። ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ጉዳቱ ሲታይ ከባድ እንደሆነ እና ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልገኝ ተነገረኝ። ከዛም የመጀመሪያ ቀዶ ጥገና አድርጌ ወደ 2 ወር ቆየሁ። እነዚህ ሁለት ወራት በጣም ከባድ ነበሩ። ግን ሃገሬ አብሬያቸው የተጫወትኩት አንዱዓለም ተስፋዬ እና ዐቢይ ዴኔቦ እዛው አግኝተውኝ በደንብ አስታመሙኝ። እነሱንም በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ። ብቻ ህክምናዬን ጨርሼ የጂምናዚየም እና የውሃ ውስጥ ስፖርቶችን እንድሰራ ታዝዤ ወደ ሃገሬ ተመለስኩ። ስፖርቶቹንም እየሰራሁ በቶሎ ለማገገም ችዬ ዳግም ልታይ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለስኩ። ዶክተሬም በቶሎ በማገገሜ ደስተና ሆኖ ግን ሌላ መጠነኛ ቀዶ ጥገና አደረገልኝ። ከዛም ተከታታይ ህክምናዎችን እዛው ሆኜ ከተከታተልኩ በኋላ ጥሩ ለውጥ መጣ። ግን ዶክተሬ ቀጣይ ሃሳቤ ምን እንደሆነ እና ወደ እግርኳሱ መመለስ እንደምፈልግ ጠየቀኝ። እኔም እግርኳስ ህይወቴ እንደሆነ ነገርኩት። ግን እሱ እግርኳስ ዳግም መጫወት እንደማልችል አረዳኝ። በጊዜው በጣም ግራ ተጋባሁ። እንደውም አስታውሳለሁ ለሦስት ቀናት ምን እንደተፈጠረ አላውቅም ነበር። ከዛ በወቅቱ አቶ አብነት ውጤቱን ሰምተው ደውለውልኝ አፅናኑኝ። ‘ላንተ መሆን አያቅተንም። ተመልሰህ ና’ አሉኝ። ከዛም እሳቸውን ሰምቼ ወደ ሃገሬ ተመለስኩ። ኢትዮጵያ ስደርስ ግን እነሱ ለእኔ ያሰቡት እና እኔ ያሰብኩት ነገር አልተጣጣመም። በወቅቱም መጥፎ ነገሮችን ያደረጉብኝ ነበሩ። እኔም መጥፎ ውሳኔ ለመወሰን ያሰብኩበት ወቅት ሁሉ ነበር። ግን በሰዓቱ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ወሰንኩ። ከጓደኞቼ ጋር ግንኙነት ፈጥሬ እነሱ እንዲቀበሉኝ አድርጌ መጣሁ።

“ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ሳስብም እዛ የሚገኙ ጓደኞቼን አማክሬ ነበር። እነሱ ሃገሩን ስለሚያቁት እና እዛ ያለውን ህይወት ስለጀመሩ ‘ና ችግር የለም’ አሉኝ። ከዛ በቅድሚያ ለሦስተኛ ጊዜ እግሬን ማሳየት ስለነበረብኝ ሄድኩ። እዛም እንደደረስኩ ዶክተሬን አግኝቼ ታየሁ። ዶክተሩም 95 % ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምገኝ ነገረኝ። ከዛም ዳግም ወደ ሃገሬ እንደማልመለስ ስነግረው ‘ችግር የለም እዚሁ እየኖርክ ለምርመራ እኔ ጋር ና። በነፃ አክምሃለው’ አለኝ። እዛውም ሆኜ ህክምናዬን ጨረስኩ። እዛ እያለሁ በእጄ ላይ የነበረው ገንዘብ በቂ ስላልነበር ኢትዮጵያ መንግስት የሸለመኝን መሬት ሸጬ ከጓደኛዬ ጋር በማናውቀው ሃገር ኑሮን መግፋት ተያያዝን። ቀላል አልነበረም፤ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ሁሉንም አለፍነው። ሃገሩ የወንጀለኞች ሃገር ነው። ግን በድፍረት የንግዱን ዓለም ተቀላቅለን ሥራዎችን መስራት ቀጠልን። ብቻ ብዙ ነገሮች አልፈው አሁን ላይ ጥሩ ደረጃ ደርሰናል። አሁን ላይ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነኝ። የመጀመሪያው ልጄ አቤኔዘር ይልማ ዕድሜው 15 ነው። የሁለተኛዋ ልጄ ኑዓሚን ይልማ ትባላለች ዕድሜዋ 8 ነው። የሦስተኛዋ ሀሴት ይልማ ዕድሜ አንድ ዓመት ከ7 ወር ሆኗታል።

“ከምወደው እግርኳስ መለየት ስላልቻልኩ ደቡብ አፍሪካ የሐበሻዎች የጤና ቡድንን ተቀላቅዬ በሳምንት አንድ ጊዜ መጫወት ቀጠልን። ከዛም ቀስ እያልኩ የአሰልጣኞች ኮርሶቸን ወሰድኩ። በዚሀም አሁን ላይ የC እና D ላይሰንስ አለኝ። ከዛም ሃገሬ አብሮኝ ሲጫወት ከነበረው ፍቃዱ በላይ ጋር ኮርሶችን ከወሰድን በኋላ በደቡብ አፍሪካ ከ8-13 የሚገኙ ኢትዮጵያ ታዳጊዎችን በሳምንት አንድ ቀን እያሰለጠንን እንገኛለን። ሌላው እንደ አሜሪካ እና አውሮፓ እዚህ ደቡብ አፍሪካም ኢትዮጵያዊያንን የማገኛኘት እና እንደኔው ኳስ ተጫዋች የነበሩ ነገርግን ጉዳት አስተናግደው የሚያያቸው ያጡ ተጫዋቾችን ለመርዳት ከፍቃዱ እና አስፕሬላ ጋር ሆነን ሁሉ ነገር ጨርሰን ፍቃድ ልናወጣ ስንል ኮቪድ-19 መጥቶ አቋረጠን። ይህንን ነገር ሕይወት ወደ ቀድሞ ቦታዋ ከተመለሰች እንገፋበታለን።

“አሁን ላይ ለሃገራችን እግርኳስ ሩቅ ስሆንኩ የምለው ነገር የለም። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሃገር ቤት ስመጣ ጨዋታዎቸን አይ ነበር። የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ትልቅ ነገር ሆኖ ሳለ ያንን ነገር ማስቀጠል አለመቻላችን ያስቆጨኛል። በተለይ እግርኳችን መሰረት ስለሌለው አንዴ ይወጣል አንዴ ደግሞ ይወርዳል። አንድ ጊዜ ጨከን ተብሎ ታዳጊዎች ላይ ለመስራት መወሰን አለበት። የ8 እና 10 ዓመት ታዳጊዎች ላይ መስራት መጀመር አለብን። ከእዚህ የእድሜ ክልል ተነስተን በመተካካት ታዳጊዎቹ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን የሚደርሱበትን መንገድ መፍጠር አለብን። ከዚሁ ጎን ለጎን ተጫውተው ያለፉ እና በእግር ኳስ አስተዳደር ላይ ጥሩ እውቀት ያላቸውን ወደ መስመሩ በማምጣት ሥራዎች ቢሰሩ ትልቅ ለውጥ እናመጣለን ብዬ አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!