“ወደ ሜዳ በመመለሴ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ዑመድ ኡኩሪ

በገጠመው ከበድ ያለ ጉዳት ለስምንት ወራት ያህል በጉዳት ከሜዳ ርቆ በቅርቡ የተመተለሰው የግብፁ አስዋን ክለብ አጥቂ ዑመድ ኡኩሪ ከጉዳት ስለመመለሱ እና ስለወቅታዊ አቋሙ ለሶከር ኢትዮጵያ ይናገራል፡፡

የ2006 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ዑመድ በመከላከያ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዋልያዎቹ ጥሩ የውድድር ዘመናት ካሳለፈ በኃላ ነበር በ2007 ወደ ግብፅ ሊግ አምርቶ አል-ኢትሀድ አሌክሳንድሪያን በመቀላቀል የግብፅ እግር ኳስ ሕይወቱን መጀመር የቻለው። በመቀጠል በግብፅ ሊግ ተወዳዳሪ ወደሆኑት ኤንፒ፣ ኤል-ኤንታግ ኤል-አርቢ እንዲሁም ዓምና ጥሩ ዓመትን ወዳሳለፈበት ስሞሀ አምርቶ ተጫውቷል፡፡

ዑመድ ስሞሀን ከለቀቀ በኃላ ወደ አስዋን ስፖርት ክለብ ማምራት ቢችልም በዘንድሮው የውድድር ዓመት በገጠመው ከባድ የጉልበት ጉዳት አዲሱ ክለቡን ላለፉት ስምንት ወራት ያህል ማገልገል ሳይችል ቀርቷል፡፡ ከኮቪድ 19 በኃላ የግብፅ ሊግ በቅርቡ ሲጀመር ከሰሞኑ ዑመድ ተቀይሮ በመግባት ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ለክለቡ ግልጋሎትን ሰጥቷል፡፡ ተጫዋቹም ስላሳለፈው ረጅም የጉዳት ጊዜያት እና ወቅታዊ አቋሙን በተመለከተ ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡

“በአስዋን ክለብ ፈጣሪ ይመስገን ጅማሬዬ ጥሩ ነበር፡፡ በሰባተኛ ሳምንት ላይ ግን ጉዳት አጋጠመኝ፤ አንደኛው ዙር ላይ ማለት ነው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ከሜዳ ለመራቅ ተገድጃለሁ። በኃላም ወደ ሜዳ ለመመለስ የሚያስፈልጉትን ሁሉ አድርጌ ሙሉ በሙሉ ተመልሻለሁ። ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ተቀይሬ በመግባት መጫወት የጀመርኩት። አሁን ያለንበት ሁኔታ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለመጫወት የሚያስችል አይደለም። የሊጉ ሁለተኛ ዙርን ቶሎ ለመጨረስም አሁን ያሉትን ጨዋታዎች በየሦስት ቀኑ ወይም በየሁለት ቀን ልዩነት ነው የሚደረጉት። እናም ከስምንት ወራት ጉዳት በኃላ ጂም በመሥራት እና ከዶክተሬ ጋር በመነጋገር ቡድኑ ጨዋታ ላይ ስለነበረ ቀስ በቀስ ወደመጫወቱ መጥቻለሁ። ያው ቶሎ ወደ ቋሚነት አልገባም፤ እየተቀየርኩ በመግባት ካልሆነ። በይበልጥ ደግሞ ጨዋታ ማድረግ በተለይ የወዳጅነት ጨዋታዎች ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ግን ያ ነገር ስለሌለ በነጥብ ጨዋታዎች አስር ደቂቃ ሀያ ደቂቃ እያለ ቀስ በቀስ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ደቂቃው እየጨመረ እስከ አርባአምስት እስከ ዘጠና ደቂቃ ለመጫወት የሚያስችል ሒደት ላይ ነው ያለሁት። ሙሉ በሙሉ ወደ ሜዳ በመመለሴ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ስሜቴን ካስደሰተኝ ነገር ዋናው ይሄ ነው፡፡ መመለስ መቻሌ ደስተኛ አድርጎኛል።”

ዘንድሮ ከአስዋን ክለብ ጋር የአንድ አመት የውል ቆይታው የሚያበቃው አጥቂው ስለ ቀጣይ ዕቅዱ እንዲህ ይላል።

” ዘንድሮ ዓመቱ ለእኔ ጥሩ ሳይሆን ነው እየሄደ ያለው። ራሴን በደንብ እያዘጋጀው ያለሁትም ለቀጣይ ዓመት ነው፡፡ የዚህ ዓመት ውድድር እያለቀ ነው፤ አሁን ላይ ቢያንስ ወደ ሰባት ጨዋታ ነው የሚቀረው። በዚህ ቀሪ ጨዋታ ይሄን ባደርግ ብዬ ማቀድ አልፈልግም። ከጉዳት እንደመመለሴ ወደ ብቃቴ ለመመለስ በደንብ ጨዋታ ያስፈልገኛል። ስለዚህ ቀሪዎቹን ጨዋታዎችም እንደ ወዳጅነት እና መዘጋጃ ጨዋታዎች ነው የማያቸው። የተወሰነ ደቂቃ ብጫወትም ወደ ብቃቴ ለመመለስ ይረዱኛል። በአጠቃላይ ዕቅዴ ለቀጣዩ ዓመት ነው፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!