DSTv የፕሪምየር ሊጉ የቀጥታ ስርጭት መብት ጨረታው አሸናፊ ሆኗል

የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ በወጣው ጨረታ መሠረት DSTv ቀዳሚ የሆነበትን ከፍተኛ ገንዘብ በማቅረቡ አሸናፊ ሆኗል።

የሊግ ኩባንያው በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ፍቃደኛ ለሆኑ ተቋማት ግልፅ የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት አወዳድሮ መብቱን ለመሸጥ እንደሚፈልግ መግለፁ ይታወቃል። በቀረበው ጨረታ መሠረት ምን ያህል ሚዲያዎች በዚህ ጨረታ ውስጥ ተካተው ስለመወዳደራቸው እርግጠኛ ባንሆንም EBC እና የውጪ ተቋማት መወዳደራቸውን ሰምተናል።

ስማቸው በጨረታው ውስጥ ተካቶ ከተገኙት ተቋማት መካከል ከፍተኛ ገንዘብ በማቅረብ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭቱን ለማስተላለፍ ሁለት የውጭ ሀገር ተቋማት ስማቸው በቀዳሚነት ተቀምጧል።

Canal Plus የተባለው የፈረንሳዩ ግዙፍ ሚዲያ በዓመት 1.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር (በወቅታዊ የምንዛሪ መጠን 52 ሚሊዮን ብር) የሚከፈል እና የአምስት ዓመት (260 ሚልዮን ብር) የውል ኮንትራት አቅርቧል።

DSTv የተሰኘው የደቡብ አፍሪካው ግዙፍ ተቋም በአንፃሩ ከፈረንሳዩ አቻው ለእጥፍ በተጠጋ መልኩ በዓመት 2.7 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር (100 ሚልዮን ብር) እና አጠቃላይ ዋጋው 13.5 ሚልዮን ዶላር (500 ሚልዮን ብር) የሆነ የአምስት ዓመት ኮንትራት አቅርቧል። ይህም የጨረታው አሸናፊ እንዲሆን አድርጎታል።

ይህ እግርኳሱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻግረዋል ተብሎ የሚጠበቀው የስርጭት መብት ስምምነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሥራዎችን ለመስራት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሊግ ኩባንያው ላደረገው ጥረት እውቅና የሚያስቸረው ነው።

በቀጣይ ቀናት በአሸናፊው ተቋም እና በሊግ ኩባንያው መካከል ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ስምምነቱ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የሊግ ኩባንያው ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከቴሌቪዥን ስርጭት መብቱ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በምን መልኩ እንደሚከፋፈል ማብራርያ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!