የግል አስተያየት | የታዳጊዎች ውድድር ፋይዳ

በታዳጊዎች ሥልጠና ሒደት የረጅም ጊዜ እድገት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የውድድር ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ታዳጊ ተጫዋቾች በውድድር ጨዋታዎች የሚያገኙት ልምድ ለቀጣይ እድገታቸው ከፍተኛ አበርክቶት አለው፡፡ ተጫዋቾች በልምምድ ብቻ ሳይሆን በውድድርም ጭምር እንደሚጎለብቱ አስቀድመው የተረዱት በእግርኳስ እድገት ማማ ላይ የደረሱት ሃገራት ለስልጠና ብቻ ሳይሆን ለውድድር ጨዋታዎችም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፣ ስልታዊ እቅድ በማዘጋጀት፣ ታዳጊዎቹ ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ ሊጫወቱ የሚችሉባቸውን ምቹ ሜዳዎች በመገንባት፣ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ውድድሮች እያዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

በዚህ መልኩ የሚሰሩት ልፋታቸው ፍሬ እያፈራላቸው ነው፡፡ በየጊዜው በትልልቆቹ የእግርኳስ መድረኮች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ደምቀው የሚታዩ ተጫዋቾች የሚታዩትም በእነዚሁ ብርቱ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ጥረት ሆኗል፡፡ ታዳጊዎቹ በእነዚህ ውድድሮች ላይ የደጋፊዎችን፣ የአሰልጣኞችን፣ የተጋጣሚ ቡድኖችን እና የመገናኛ ብዙሃንን ጫና በመቋቋም የጠንካራ ስነ-ልቦና አቅም መገንባት ይችላሉ፡፡ ማሰልጠኛ ማዕከላት የታዳጊዎቹን እድሜ የሚመጥንና የተፎካካሪነትን መንፈስ በውስጣቸው የሚያሰርጹ ደረጃቸውን የጠበቁ የውድድር መርኃግብሮች እንዲኖራቸው የሚጠበቀው ስኬታማ የሆነ ተጫዋቾች ማፍሪያ ዘዴ በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ውድድሮች መልማዮች የነገዎቹን ምርጥ ተተኪ ተጫዋቾች በዛሬዎቹ የታዳጊ ውድድሮች እንዲያስሱ ያግዟቸዋል፡፡ አሳሾቹ መልማዮች፣ የየክለቡ የወጣትና ታዳጊ ቡድኖች አሰልጣኞች በውድድሮች የሚያገኙአቸውን ባለ ክህሎት ታዳጊዎች እድገታቸውን ይከታተላሉ፤ ተገቢው የእድገት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይተጋሉ፡፡

በሃገራችን እግርኳስ የታዳጊዎች ስልጠናም ሆነ የታዳጊዎች ውድድር በቂ ትኩረት ያልተቸረው ጉዳይ ነው፡፡ እንደአሁኑ ከፍተኛ ገንዘብ ለተጫዋቾች በደሞዝ መልክ መከፈል ከመጀመሩ ቀደም ባሉት ጊዜያት በጥቂቱም ቢሆን የተሻሉ ውድድሮች ይዘጋጁ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትኩረት እያጣ የመጣው ይህ የታዳጊዎች ውድድር በከፍትኛ ሁኔታ የቀድሞው ገፅታ ደብዛው እየጠፋ ያለ ይመስለኛል፡፡ በሃገራችን የታዳጊዎች ውድድር በምቹ ሜዳዎች እጦት፣ በአስተዳዳራዊ ችግሮች፣ በክለቦች ፍላጎት ማጣት፣ በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት መነፈግ እና በሌሎችም ችግሮች ተወጥሮ የኋሊት እየሄደ ነው፡፡ “የዚህ አሳሳቢ የውድቀት ጉዞ  መንስዔዎች ምንድን ናቸው?” ለሚለው ጥያቄ በምክንያትነት የሚቀመጡ ነጥቦችን በዛሬው አስተያየቴ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

★ ለታዳጊ ተጫዋቾቻችን ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የመወዳደሪያ ስፍራ እጥረት ለውድድር ጥራት ማሽቆልቆል ዋነኛው መንስኤ ነው፡፡ ” ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ፡፡” እንደሚባለው  ዘመናዊነቱና ደረጃውን መጠበቁ ቀርቶ በከተማችን በቋሚነት ውድድሮች የሚደረጉበት የሳር ሜዳ ማግኘት በራሱ ብርቅ ነው፡፡ ጥቂት ለማይባሉ አስርት ዓመታት በከተማችን የሚካሄዱ የታዳጊዎች ውድድር ሲያስተናግድ የቆየው ጃን-ሜዳ እንኳ በአንጻራዊ ደረጃ በ”ትልልቆቹ” የእግርኳሳችን መድረኮች የሚሳተፉ ብቁ ተጫዋቾችን ማፍራቱ ቢታወቅም ምቹ ያለመሆኑ ጉዳይ ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም፡፡ በርካታ አሰልጣኞች ለዚህ ምስክር መሆን ይችላሉ፡፡ ይህንን ስል በጃንሜዳ ተጫውተው በሃገራችን እግርኳስ በትልልቆቹ ክለቦች የተጫወቱ አልያም እየተጫወቱ የሚገኙ ተጫዋቾች የሉም እያልኩኝ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ሜዳ  በዓለም አቀፍ የእግርኳስ መድረኮች የሚጫወቱ  “ፕሮፌሽናል” ተጫዋቾችን ለማፍራት በምንም መስፈርት ብቁ አይደለም፡፡ ይህን የመሰለ ቦታ  ብቁ የታዳጊ ውድድሮች ማስተናበሪያ ወይም ማዘጋጃ በማድረግ ዘላቂ የሆነ ብቁ ተተኪዎችን ማፍሪያ እንዲሆን ማስተካከል ለከተማው የስፓርት ኮሚሽን ለምን ከባድ እንደሆነበት ማወቅ የሁልጊዜም ፍላጎቴ ነው፡፡ ዘወትር መልስ ከማላገኝላቸው የእግርኳስ ልማት ጥያቄዎቼ አንደኛው ይኸው የጃን ሜዳ ነገር ነው፡፡ የመጫወቻ ሜዳው ላይ ሳር በማስተከል፣ ለጨዋታ ምቹ በማድረግ፣ የተመልካቾች ስፍራ በማዘጋጀት፣ በየታዳጊዎቹ የእድሜ እርከኖች የተከፋፈሉ ውድድሮች በማዘጋጀት ከገንዘብም ሆነ ብቁ ተጫዋቾች በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ሊገኝበት የሚቻል የእግርኳስ ልማት መሰራት ሲቻል ለምን ዝም እንደተባለ ግራ ግብት ይለኛል፡፡ 

★ በከተማችን በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ሜዳዎች ቀስ በቀስ ለተለያዩ አገልግሎቶች መዋላቸው በፌዴሬሽን ሥር ይደረጉ ከነበሩ መደበኛ ውድድሮች ውጪ በየሰፈሩ በሚገኙ ስፓርት ወዳድ ወጣቶች አማካኝነት ይዘጋጁ የነበሩ ውድድሮች እንዲቆሙ አድርጓል፡፡ ይህም በታዳጊ ተጫዋቾቻን እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  በከተማችን የሚገኙ አብዛኞቹ ክለቦች የራሳቸው የልምምድ ሜዳ እያዘጋጁ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉት ግን ሜዳዎቹን ለውድድር ሲፈቅዱ አይታይም፡፡

★ የታዳጊዎች ስልጠናንም ሆነ ውድድርን በተመለከተ በክለቦች ዘንድ ያለውን የአመለካከት ዝንፈት እኔ የአሰራር ክፍተት ማንሳትም ይኖርብናል፡፡ ለትልልቆቹ ተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ በርካታ ሚሊዮኖች የሚያፈሱት ክለቦቻችን ለታዳጊ ተጫዋቾቻችን የረባ ዘላቂ እቅድ ማዘጋጀት አለመቻላቸው በጣም የሚያስተዛዝብ ነው፡፡አብዛኞቹ ክለቦቻችን ወጣት እና ታዳጊ ተጫዋቾች የሚይዙት ፌዴሬሽኑ ስለሚያስገድዳቸው ብቻ ነው፡፡ በዚህም ተተኪ ለማፍራት ሳይሆን ትኩረት ባጣው በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በሚል ብቻ በደካማ የምልመላ ስርዓት የመለመሏቸውን ተጫዋቾች ይዘው ይቀርባሉ፡፡

★ ክለቦቻችንን የሚያስተዳድሩት አንዳንድ አመራሮች በታዳጊ ተጫዋቾች ስልጠና ላይ በቂ እውቀት ስለሌላቸው ተተኪዎችን ለማፍራት የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፈው በዚሁ ዕቅድ መሰረት ከመስራት ይልቅ ውጤትን በዋንጫ ብቻ በመለካት አሰልጣኞቹ እና ተጫዋቾቹ ላይ ያልተገባ ጫና ሲያደርጉ መመልከት ችያላሁ፡፡ በዚህ ችግር ሳቢያ የክለቦቻችን ታዳጊና ወጣት ቡድኖች አሰልጣኞች በረጅም ጊዜ ተተኪዎችን ለማፍራት ከመስራት ይልቅ ለጊዜያዊ “ውጤት” ላይ ታች ሲባዝኑ መመልከት የተለመደ ተግባራቸው ሆኗል፡፡ ይህ ሁኔታ በቀደሙት ጊዜያት አንዳንዶቹ አሰልጣኞች የተጫዋቾችን እድሜ ከማጭበርበር ጀምሮ ሌሎችንም ጊዜያዊ ውጤት ማግኛ ሙያዊ ያልሆኑ ስልቶች እንዲጠቀሙ ግፊት አድርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ የታዳጊና ወጣት ቡድን ተጫዋቾች ውድድር ተጫዋቾች የመጫወት ነፃነት የማያገኙበትና ክህሎታቸውን የማያሳድጉበት የይስሙላ ውድድር የመሆን አደጋ ገጥሞታል፡፡ አሰልጣኞችም አዳዲስ የጨዋታ ስልቶችን በመንደፍ በአመራር፣ ስነ ልቦና፣ ታክቲክ፣ አካል ብቃትና በመሳሰሉት መመዘኛዎች ያላቸውን ብቃት የሚያሳዩበት መድረክ አልሆነላቸውም፡፡

★ የታዳጊና ወጣት ቡድኖች ስልጠና እና ውድድር ላይMRI ን የተመለከተው ጉዳይ መሠረታዊ ነው፡፡ በእግርኳሳችን ከባቢ እድሜ ላይ መሥራት አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ነው፡፡ ይህ የMRI የታዳጊዎች የዕድሜ ምርመራ አሠራርም ችግሮች እየቀረፈ የበለጠ ዘመናዊ አሰራሮችን እንድንከተል ማድረጉ በጣም መበረታታት ያለበት ጅምር ነው፡፡ በምርመራ ሒደቱ ወይም ተግባራዊ ክንውኑ ላይ ግን ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የችግሩ ዋነኛ መነሻ በሃገራችን የታዳጊዎች ውድድር የሚደረግበት ቋሚ የጊዜ ሰሌዳ አለመኖሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ክለቦች ታዳጊዎችን አድካሚ እና አሰልቺ የሆነውን ምልመላ በተለያየ ጊዜ ያካሂዳሉ፡፡ ይህም ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾቹ የMRI የዕድሜ ምርመራ አድርገው ማለፋቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በውል ለማይታወቅ ጊዜ ያለምንም የደመወዝ ክፍያ፣ የላብ መተኪያ፣ ሻወርና የመገልገያ መሳሪያዎች (ትጥቅ) ልምምድ እየሰሩ እንዲቆዩ ይገደዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ልምምዶች ደግሞ ጊዜያቸው ያልተገደበና ከፍተኛ የአካል ብቃት ላይ ስለሚያተኩሩ የተጫዋቾችን ዘላቂ እደገት የሚያቀጭጩ ናቸው፡፡ የMRI ምርመራ የሚደረግበት እና ውድድር የሚጀመርበት ትክክለኛው ጊዜ በውል አለመታወቁ ታዳጊ ተጫዋቾች በትራንስፖርት እና በላብ መተኪያ እጦት ረዘም ላለ ጊዜ እንዲንገላቱ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሌላም ችግር አለ፡፡ በቁጥር በርከት ተደርገው የሚያዙት እነዚህ ታዳጊ ወጣት ተጫዋቾች በክለብ ቦታ ለማግኘት ተስፋ ሰንቀው ረዘም ላለ ጊዜ ከሰሩ በኋላ የMRI ምርመራ ዘግይቶ ሲመጣ ለአንዳንዶች እድሜያቸው ማለፉን በማሳወቅ መርዶ ይሆንባቸዋል፡፡ ይህም ሁለት ችግሮችን አስከትሎ ይመጣል፡፡ አንደኛው ከፍ ባለው የእድሜ እርከን በሌላ ክለብ የሙከራ እድል ለማግኘት የሙከራ ጊዜው ያልፍባቸዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ስነ-ልቦናዊ ተግዳሮቱ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የተጫዋቾች እድገት በየእድሜ እርከኑ ይለያያል፡፡እድሉን አግኝተው ለተገቢው እድሜያቸው በሚመጥነው ደረጃ ባሉበት ክለብም ይሁን ሌላ ክለብ የመጫወት በለስ ቢቀናቸው እንኳ በአዕምሮ፣ በስነልቦ እና በአካልም ብቃት በአንጻራዊነት ስለሚያንሱ በዛ ከተባለ ለአንድ ዓመት ከክለብ ልምምድና ጨዋታ ውጪ ሆነው ያሳልፋሉ ፡፡ ይህ በእድገታቸው ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅእኖ ከፍ ያለ ነው፡፡በጣም ጠንካራ ከሆኑት ውጪ አንዳንዶቹ ወደ ክለብ እግርኳስም ደግመው አይመለሱም፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት፦

★ ክለቦች ተጫዋቾችን መልምለው እንደጨረሱ የMRI ምርመራ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት

★ በርካታ ገንዘብ ለትልልቆቹ ተጫዋቾች የሚያወጡት ክለቦቻችን የታዳጊ ተጫዋቾቻንን የእግርኳስ ህይወት ለመታደግና ተተኪ ተጫዋቾችን በብዛት እና በጥራት ለማፍራት በሌሎች ሃገሮች እንደሚደረገው የተለያዩ የእድሜ ቡዶኖችን እንዲይዙ ማስገደድ፡፡ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች፣ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በታች፣ ከሃያ አንድ ዓመት በታች፣ ከሃያ ሦስት ዓመት በታች ቡድኖችን መገንባት የክለብነት ተልዕኮ አካል ማድረግ

-እነዚህ መፍትሄዎች ምናልባት አሁን በታዳጊ ተጫዋቾቻችን ላይ እየተከሰተ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ጠቃሚ ይሆናሉ ባይ ነኝ፡፡

ሃገራችን ተስጥኦ ባላቸው ታዳጊዎች እጥረት የተጠቃች እንዳልሆነች በታዳጊዎች ላይ እየሰራሁ ስላለሁ እኔ ምስክር ነኝ፡፡ ያሉንን ተስጥኦዎች በአግባቡ መልምሎ፣ ተገቢውን ስልጠና፣ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ የሚፈለገው ቦታ የሚያደርስ መዋቅር ግን አልዘረጋንም፡፡ ይህንን “ሲስተም” እስክንዘረጋ ድረስ በእግርኳሳችን ማየት የሚናፍቁን ለውጦች እንደናፈቁን ይቀራሉ፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!