የአሠልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-3 ሰበታ ከተማ

የሁለተኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ከሆነው የሀዋሳ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።


ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ብዙ ልዩነቶች ነበሩት። ሰበታዎች ከእኛ በጣም ተሽለው ነበር። በተለይ ኳስን ተቆጣጥረው የተጫወቱበት መንገድ ስኬታማ አድርጓቸዋል። እኛም በዚህ መንገድ ነበር ለመጫወት ያሰብነው ግን እነሱ ከእኛ ተሽለው ነበር። ለዚህም ማሸነፍ ይገባቸዋል።

ስለ ተጫዋች ለውጥ…

የመጀመሪያው የወንድማገኝ ቅያሪያችን የማጥቃቱን እንቅስቃሴ ለማገዝ ነበር። ምክንያቱም እየተመራን ስለነበረ። ያሰብነውም በጥሩ ሁኔታ ነበር የቀጠለው ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠብን። ይህ ደግሞ ትንሽ ወረድ እንድል አድርጎናል። ይህንን ደግሞ አሻሽለን ለቀጣይ ውድድር እንቀርባለን።

በሊጉ ስላደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ እና ቀጣይ የቡድኑ ጉዞ

እንደ መጀመሪያ ጨዋታ የዛሬው እንቅስቃሴ ለእኛ ጥሩ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች ጥሩ ዝግጅት አድርገን መቅረብ አለብን። ምክንያቱም ሌሎቹ ክለቦች በጣም ጠንካራ እንደሆኑ ነው ያየነው። ስለዚህ ያለብንን ችግር አስተካክለን ጠንካራውን ሀዋሳ ከተማን በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ለእኛ ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። የምንፈልገውም ነጥብ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን አሁንም የተወሱ ድክመቶች አሉብን። በተለይ በመከላከሉ እና እንደ ቡድን በመጫወት ረገድ ትንሽ ክፍተት አለብን። ይህንንም ወደፊት ለማስተካከል እንሞክራለን። በዛሬው ጨዋታ ያስቆጠርናቸው አብዛኞቹ ጎሎች ከቆሙ ኳሶች የተገኙ ነው። ይህንን ብዙም አልሰራንባቸውም ግን ዛሬ ውጤት አስገኝቶልናል። እኛ ኳስን ተቆጣጥረን ወደፊት በመሄድ ጎል ማስቆጠር ላይ ነበር በደንብ የሰራነው። ግን በዚህ መንገድ ከሦስተኛው ጎል ውጪ ሌላ ግብ አላገባንም።

በጨዋታው ድንቅ ግብ ስላስቆጠረው ፎአድ ፈረጃ…

ለእኔ ፎአድ የዕለቱ ኮከብ ነው ማለት እችላለሁ። እርሱ ሁለት ኳሊቲዎች ያሉት ተጫዋች ነው። አንደኛው ሁለገብነቱ ነው። በሚሰጠው ቦታ የታዘዘውን ያደርጋል። ሌላኛው ደግሞ ሜዳ ላይ ያለውን አውጥቶ መስጠት መቻሉ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ