ሪፖርት | ፈረሰኞቹ የመጀመርያ ሦስት ነጥባቸውን አሳክተዋል

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ከሰዓትም ሲቀጥል በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ የቀረበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በመርታት የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ሳምንት ከተጠቀመው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሬ ያደረገ ሲሆን በዚህም በከነዓን ማርክነህ እና ደስታ ደሙ ምትክ ሀይደር ሸረፋ እና ሮበን ንጋላንዲ ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ሥስት ለውጦችን በማድረግ ምንያምር ጴጥሮስ፣ ፍሬዘር ካሣ እና ዳንኤል ደምሴ ወደ መጀመሪያ 11 በማካተት ጀምረዋል።

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁሉቱም ቡድኖች ከመከላከል በዘለለ በማጥቃቱ ረገድ ይህ ነው የሚባል የጨዋታ እቅድን ለማሳየት የተቸገሩበት ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች መነቃቃትን ያሳየው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ተደርገዋል። በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ40ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አቤል ያለው በግንባር በመግጨት ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ ተጠቃሽ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል በ44ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ከተከላካይ ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ ጁንያስ ናንጂቡ ከፓትሪክ ማታሲ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በሚያስቆጭ መልኩ ያመከናት እና የተመለሰውን ኳስ ኤልያስ ማሞ ሞክሮ ሄኖክ አዱኛ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅምሩ ቀጥተኛ አጨዋወትን ጨምረው የተመለሱት ፈረሰኞቹ በ57ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከራሱ የግብ የላከለትን ኳስ አዲስ ግደይ ተቆጣጥሮ ለማለፍ ሲሞክር ዘነበ ከበደ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቤል ያለው በማስቆጠር ፈረሰኞችን መሪ ማድረግ ችሏል።

የግቧ መቆጠርን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች በ58ኛ እና በ60ኛው ደቂቃ በፓትሪክ ማታሲ ስህተት ታግዘው ሁለት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን በኤልያስ ማሞ እና ጁኒያስ ናንጂቡ አድርገዋል። በ69ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ጁንያስ ናንጂቡ ከቀኝ መስመር ያሳለፈታን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ የላካትና የግቡን ቋሚ ለትማ የተመለሰችበት ኳስ በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በክረምቱ ያዘዋወሯቸውን አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ከነዓን ማርክነህን ካስገቡ ወዲህ ይበልጥ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለት ግቦችን በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ማስቆጠር ችለዋል። በ79ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት ወደ ግብ የላከውን ኳስ ዘነበ ከበደ በእጅ በመንካቱ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ ሲያስቆጥር በ83ኛው ደቂቃ ደግሞ ፍሬዘር ካሳ በጫና ውስጥ ሆኖ ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ ፍሬው ጋር ሳይደርስ የጊዮርጊስ አቤል ያለው ቀድሞ ደርሶ ያገኘውን ኳስ በተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው ከነዓን አቀብሎት ከነአንም አንድ ተጫዋች አልፎ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የፈሰኞቹን መሪነት አስተማማኝ አድርጓል።

ከግቦቹ መቆጠር በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት አቤል ያለው ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታውን ኳስ ፍሬው ጌታሁን በአስደናቂ መልኩ ሊያድንበት ችሏል። በ88ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በምንተስኖት አዳነ አናት ላይ ያሳለፈለትን ኳስን ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙህዲን ሙሳ ለድሬዳዋ ከባዶ መሸነፍ የዳኑበትን ግብ አስቆጥሯል።

ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ3-1 የበላይነት መጠናቀቅን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ