ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ የጨዋታ ሳምንት ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮቹ በተከታዩ ፅሁፋች ተዳሰዋል።

👉ኢትዮጵያ ቡና ወደ ድል ተመልሷል

ከቀናት በፊት በሀዋሳ ከተማ ያልተጠበቀ ሽንፈትን ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ5ኛ ሳምንት መርሐግብር ሰበታ ከተማን 3-2 በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

ያለ አምበላቸው አማኑኤል ዮሀንስ ሰበታ ከተማን የገጠሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው ሰበታ ከተማን ማሸነፍ ችለዋል ፤ ሁለት የኳስ ቁጥጥር መሰረት አድርገው መጫወት ምርጫቸው ያደረጉ ቡድኖች መካከል በተደረገው የአርብ ረፋዱ ጨዋታ ዳዊት እስጢፋኖስ እና መስዑድ መሀመድን የመሰሉ ባለልምድ አማካዮችን የያዘው ሰበታ በተስፈኞቹ ሬድዋን ናስር እና ዊልያን ሰለሞንን በያዘው ኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል በሁለቱም አጋማሾች ተበልጦ ተስተውሏል።

በጨዋታውም በተለይም መሀል ሜዳ የነበሩትን ግንኙነቶች የኢትዮጵያ ቡናዎች የአማካይ ክፍል የተሻለ ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች የሰበታ ከተማ አቻዎቻቸውን ከመቆጣጠር ባለፈ መሀል ሜዳ ላይ ከሚነጠቁ ኳሶች መነሻነት በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል ፤ በዚህም አቡበከር ናስር ሁለት እንዲሁም ሀብታሙ ታደሰ ባስቆጠሯቸው ግቦች አሸንፈው ለመውጣት ችለዋል።

ቡናማዎቹ ከቀናት በኃላ በ6ኛ ሳምንት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አራፊ የነበረውን የከተማ ተቀናቃኛቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስን በሸገር ደርቢ ከመግጠማቸው በፊት ጥሩ የሞራል ስንቅ ሊሆናቸው የሚችል ድልም ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

👉ተስፋ ያሳየው የጅማ አባጅፋር

ሙሉ የአምስት ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን ካደረጉ ስምንት ቡድኖች ውስጥ የሚካተቱት ጅማ አባ ጅፋሮች እስካሁን ሁለት ነጥቦችን ብቻ አሳክተዋል።

አሁንም ባልተከፈለ የተጫዋቾች ደሞዝ መነሻነት መታመስ ላይ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር ከሀዋሳ ከተማ ጋር በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ችለዋል።

ከጨዋታው አንድ ቀን አስቀድሞ የቡድኑ ተጫዋቾች እስካሁን የደሞዛቸው ጉዳይ እልባት ባለማግኘቱ ሜዳ ገብተው የመጫወታቸው ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም በአሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው ጥረት ተጫዋቾቹ ሀዋሳ ከተማ ጋር የነበረውን ጨዋታ አድርገው 1-1 መለያየት ችለዋል።

ያለ በቂ ልምምድ ሆነ የመጫወታቸው ነገር ጥርጣሬ ውስጥ ሆነ መጫወትን ልማዱ እያደረገ የመጣው ጅማ አባ ጅፋር ምኞት ደበበ በ89ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ግብ ለጥቂት በእጁ ገብቶ የነበረውን ድል መልሶ ምኞት ራሱ ባስቆጠራት ግብ ተነጠቀ እንጂ ለማሸነፍም ተቃርቦ ነበር።

ውድድሩ ሲጀምር ወይ በደንብ የማያጠቃ ወይ በደንብ የማይከላከል ዓይነት ቡድን የነበረው ጅማ ይዘግይ እንጂ በዚህ ሳምንት መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ችሏል። በጥብቅ መከላከል ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ትልቅ ጥረት ያደረጉት ጅማዎች አሸንፈው መውጣት የሚችሉበትን ግብም አግኝተው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ተቆጥሮባቸው ነጥብ ተጋርተዋል። በበርካታ የሜዳ ውጪ ጉዳዮች ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ የቡዙአየሁ እንዳሻው ፣ ሳዲቅ ሴቾ እና ሳምሶን ቆልቻ የፊት መስመር ጥምረት በድጋሚ የተጠቀመበትን ጨዋታም ነው ያደረገው። በቀጣይ ጨዋታዎች የአጥቂዎቹ ተደጋጋሚ ጥምረት የተሻለ መናበብን ፈጥሮለት ግቦች ወደ ማግኘቱ ከሄደ እና እንደመጀመሪያ የጨዋታ ዕቅድ ከሀዋሳ ጋር እንደሆነው ሁሉ ለተጋጣሚዎች ክፍተት ላለመስጠት ከሰራ ቡድኑ ነጥብ ማግኛ ዕድል ሊኖረው ይችላል። እንደ ጅማ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ካሉበት ሁኔታ በመነሳት ነጥብ የሚያስገኝላቸውን የትኛውንም አጨዋወት ቢመርጡ የሚያስኮንናቸው አይሆንም።

👉የራሱን ፈተና የተጋፈጠው ሀዋሳ

በአራተኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር። ሀዋሳ በጨዋታው ጥብቅ መከላከልን ምርጫው አድርጎ ተጋጣሚውን አላፈናፍን በማለት ውሎ ነበር።

ተጋጣሚያቸውን ኢላማውን ላልጠበቀ የግብ ሙከራ እንኳን የሚሆን ስህተት አልሰራለት ያሉት ሀዋሳዎች የዚያን ቀን ብቃታቸውን ለተመለከተ አጨዋወቱን ለረጅም ጊዜ ይተገብሩ የነበሩ ይመስሉ ነበር።

በአምስተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ግን ወደ ትክክለኛው አጨዋወታቸው ተመልሰው ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ተጋፍጠዋል። ጅማም የአራተኛውን ሳምንት የእነሱን ዓይነት መልክ ይዞ ጠብቋቸዋል። ሀዋሳዎች በተራቸው የቡናን ቦታ በመውሰድ ግብ ፍለጋ ከአጫጭር ቅብብሎች እስከተሻጋሪ ኳሶች ድረስ የሚችሉትን ያህል ሞክረዋል። አልሳካ ብሏቸው በተቸገሩበት ሰዓት ራሳቸው ላይ ግብ አስቆጥረው ፈተናውን ይበልጥ አክብደውትም ነበር። በመጨረሻ ግን ቢያንስ አንድ ነጥብ የምታስገላቸውን ጎል አግኝተው ነጥብ ተጋርተዋል።

👉ድሬዳዋ ከተማ ተከተታይ ድሉን አግኝቷል

ወላይታ ድቻን የገጠመው ድሬዳዋ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ በተገኙ ሁለት ግቦች ወላይታ ድቻን 2-1 በመርታት የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ባገኙት ሁለት ቢጫ ካርድ ምክንያት ያለፈው ጨዋታ ያመለጣቸው በረከት ሳሙኤልና ዳንኤል ደምሴን ዳግም መልሰው በማግኘታቸው የተጠቀሙ የሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለ በነበሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በሙህዲን ሙሳ እና አስቻለው ግርማ ባስቆጠሯቸው ግቦች ባለድል መሆን ችለዋል።

ጥሩ የሚባል አጀማመር ባለማድረጋቸው ጫና ውስጥ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በተከታታይ ባስመዘገቧቸው ሁለት ድሎች አፎይ ብለዋል።

👉 የቁጥር ብልጫን መጠቀም የተሳነው ፋሲል ከነማ

በመሪዎቹ ተርታ ከሚገኙ ክለቦች መካከል እንደመገኘቱ በውጤት ደረጃ በጥሩ ጎዳና ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ነጥብ በጣለባቸው ሁለት ጨዋታዎች ጨምሮ ባሸነፈባቸውም ጨዋታዎች እንደ ቡድን የነበረው የፍላጎት እና ትኩረት ደረጃ አስተማማኝ አልነበረም። ዐፄዎቹ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ሁለተኛውን አጋማሽ የአንድ ተጫዋች ቁጥር ብልጫ መጠቀም ሳይችሉ ይብሱኑ ከአቻ ወደ ሽንፈት ያመሩ ሲሆን በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ባህርዳር ለአንድ ሰዓት ያህል በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ተጫውቶ በሚገባ ፈትኗቸው በመጨረሻ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ፋሲል ከነማ ለዋንጫ ከሚፎካከሩ ከቡድኖች መካከል አንዱ እንደመሆኑ የአሸናፊነት መንፈሱ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ወጥ መሆን ይኖርበታል። የቡድኑ ከትኩረት ማነስ እና ውጤትን ከማሳካት እርግጠኝነት የሚመነጩ ስህተቶች ኋላ ላይ ፉክክሩ ሲበረታ ውድ የሆኑ ነጥቦችን ካሁኑ እንዲጥል ሲያደርጉ መታየቱም ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ተጋጣሚዎች በካርድ ሳቢያ የተጫዋቾቻቸው ቁጥር አንሶ ከፋሲል በላይ ተነናሽነትን ማሳየታቸው ሁለት ጊዜ መደገሙ ከእነሱ ጥንካሬ በተጨማሪ ከአፄዎቹ ድክመት የመነጨ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

👉ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

አስከፊ በሆነ የውጤት ማጣት ሊጉን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በዚህኛው ሳምንት ሁለት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገበውን ወልቂጤ ከተማን ገጥመው ዳዊት ተፈራ በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠራት ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ ሰንጠረዥ አናት ብርቱ ተፎካካሪነቱ የሚታወቀው ሲዳማ ቡና በክረምቱ በዝውውር መስኮቱ አዲስ ግደይን ለቅዱሰ ጊዮርጊስ አሳልፈው ከሰጡ ወዲህ ግን የቀደመው ጥንካሬያቸው የከዳቸው ይመስላል ፤ እስከዚህኛው ሳምንት ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፉ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በዚህኛው ሳምንት ባስመዘገቡት ውጤት የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

👉 የሀዲያ ሆሳዕና አራተኛ ተከታታይ ድል

በአራተኛው ሳምንት አራፊ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ትናንት አዳማ ከተማን በመርታት አራተኛ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። የሆሳዕና ስብስብ በተለይ በመከላከሉ ረገድ ያለው ጥንካሬ ላይ በተናጠል የጨዋታን ውጤት መቀየር ከሚችሉ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ጋር ተዳምሮ በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ ወጥ ብቃትን እያስመለከተን መጓዙን ቀጥሏል።

ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ ፈተና በሆነበት ሊግ በአራት ሳምንት ጨዋታዎች የ 100% አሸናፊነትን ማስቀጠል ቀላል የሚባል ጉዳይ አይደለም። 1/4 የሚሆነውን የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታዎች ያከናወኑት ሆሳዕናዎች ይህ ብቃታቸው በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ከሚጠበቁ ቡድኖች ውስጥ ሊያካትታቸው የሚችል ነው። በሌላ በኩል ሲታይ ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ ውጪ ደካማ የሊግ አጀማመር ላይ ከሚገኙት ወላይታ ድቻ ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ጋር የተገናኙ መሆኑ ቀጣይ መርሐ ግብሮች ላይ ጠንከር ያለ ፈተና እንደሚገጥማቸው የሚጠቁም ነው። ያም ቢሆን ቀድመው ነጥቦችን መሰብሰባቸው ለቀጣይ ጉዟቸው ትልቅ እገዛ ይኖረዋል።

👉 በርካታ የሆሳዕና ተጫዋቾች የቀድሞው ቡድናቸውን የገጠሙበት ጨዋታ

በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቀድሞው የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች የተገነባው ሀዲያ ሆሳዕና በአዲስ መልኩ ከምንም እየተገነባ የሚገኘውን አዳማ ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በ100% የአሸናፊነት ግስጋሴው ቀጥሏል።

በተለያየ ፅንፎች የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው በዚሁ ጨዋታ የወቅቱ የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አምስት የቀድሞ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች በቋሚነት እንዲሁም ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን በሀዲያ ሆሳዕና መለያ የተጠቀሙ ሲሆን በጨዋታውም ኢይዛክ ኤሴንዴ ፣ ሳሊፍ ፎፋና እና ዳዋ ሆቲሳ ለሀዲያ ሆሳዕና የድል ግቦቹን ማስቆጠር ችለዋል።

በሊጋችን በማሰልጠን ላይ ከሚገኙ አሰልጣኞች በጥንቃቄ መር አጨዋወት የተረጋጋ ቡድን በመገንባት የሚታወቁት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ
ከተጫዋቾቻቸው ጋር የቀድሞው ክለባቸውን መግጠማቸውን አስመልክቶ አስመልክቶ ይህንን አስተያየት ሰጥተዋል። “ከቤተሰብ ጋር እንደመጫወት ነው። አዳማ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ነው። ከህዝብ ጋርም ከአመራር ጋርም የነበረኝ ግንኙነት መልካም ነው። አዳማ ሁሌም መልካም ነገር እንዲገጥመው እመኛለሁ። በተከታታይ ዓመታት ለሜዳሊያ ያበቃሁት ቡድን ነው። ባለው የፋይናንስ ችግር ምክንያት ነው ሁላችንም ለመውጣት የተገደድነው እንጂ ጠልተነው አይደለም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ