የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለአሰልጣኝ እና ክለብ ኃላፊዎች ጥሪ አደረገ

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ከጨዋታ በፊት እና በኋላ ተፈፀሙ ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ ማብራሪያ እንዲሰጡ አወዳዳሪው አካል ጥሪ አድርጓል።

ነገ ማክሰኞ ታህሳስ 27 ቀን በ07:30 የውድድር ስነ ስርዓት ኮሚቴ ጥሪ ያደረገላቸው የመጀመርያ ሰው የድሬደዋ ከተማ አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ በተለያዩ ቀናቶች በሰጧቸው ድህረ ጨዋታ መግለጫ ዙርያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ነው ጥሪ የተደረገላቸው። አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን ከሜዳው እና ከኮቪድ ምርመራ ቸልተኝነት ጋር በተያያዘ ለመገናኛ ብዙሀን አስተያየት መስጠታቸው ይታወቃል። አሰልጣኙ በድሕረ ጨዋታ አስተያየታቸው የሚከተለውን ቅሬታ ገልፀው ነበር።

“ያው አንግሉ በየጨዋታው ኮከብ ተጫዋች መባል አለበት። ኮከብ መሆን ያለበት አግዳሚው እና ቋሚው ነው ይመስለኛል። እስካሁን ወደ 13 ኳስ ነው አግዳሚ እና ቋሚ የመታብን። እና በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ይሄ ደግሞ ከምን የመጣ ነው የምለው የምንሰራበት መላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የልምምድ ሜዳ ጎላቸው በዘፈቀደ የተሰራ ነው። እግር ወይደለም ኳስ የሚመታው ጭንቅላት ነው። እዛ ላይ ተለማምደው ይመጣሉ እዚህ ስህተት ይሰራሉ። ይሄ ነገር ራሱ ቢታሰብበት ደስ ይለኛል። ሌላው ኮቪድን የተመለከተ የምሰጠው ሀሳብ አለኝ። ወላይታ ድቻን ለመውቀስ አይደለም። ይሄ የህይወት ጉዳይ ነው። ተማርምረን እንመጣለን። የተመረመርንበት ወረቀት እና ቴሴራ ሊተያይ ይገባል። ዛሬ አሁን ቼክ ስናደርግ ከእነሱ ሁለት ያልተመረመረ አግኝተናል። እንዲህ ዓይነት ችግር ስላለ አወዳዳሪው አካል ጥንቃቄ ቢያደርግ ጥሩ ነው፤ የህይወት ጉዳይ ስለሆነ። ”

ሌላው ጥሪ የተደረገላቸው የባህር ዳር ከተማ እና የፋሲል ከነማ ቡድን መሪዎች እና የደጋፊ ማህበር ተወካዮች ሲሆኑ ምክንያቱ ደግሞ በዲሲፒሊን ግድፈት ዙርያ በተለይም ሁለቱ ቡድኖች በተጫወቱበት ወቅት ለተፈጠረው የዲሲፒሊን ግድፈት ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ