ወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኙን አሰናበተ

አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ከወላይታ ድቻ አሰልጣኝነት ሲሰናበቱ በምትኩ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ክለቡ ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡

በ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ደካማ የስድስት ሳምንታት ጉዞን ያደረገው ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ጋር በይፋ መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ ክለቡን ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በመረከብ ሲመራ የነበረው የቀድሞው የወላይታ ሶዶ የስፖርት መምህሩ እና ከዚህ ቀደም የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ረዳት በመሆን ክለቡን የተቀላቀለው ደለለኝ በተሰረዘው ዓመት ከመጋቢት ጀምሮ ክለቡን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት በሚመራበት ወቅት በክለቡ ባስመዘገበው ውጤታማነት መሠረት ዘንድሮ ለአንድ ዓመት በቋሚ የዋና አሰልጣኝነት ተሹሞ በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ክለቡን ሲመራ ተመልክተናል፡፡ ሆኖም ከተደረጉ የአዲስ አበባ የስድስት ሳምንታት የክለቡ ጨዋታዎች ድቻ አንድ ብቻ አሸንፎ አምስቱን ደግሞ ለመሸነፍ ተገዷል፡፡ የክለቡ ቦርድም ክለቡ ያደረጋቸው ጨዋታዎችን ከገመገመ በኃላ አሰልጣኙን ተጠያቂ በማድረግ ከውሳኔ በመደረሱ ከምክትሉ ግዛቸው ጌታቸው ጋሮ ጭምር እንደተሰናበቱ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እያሱ ነጋ አረጋግጠውልናል፡፡

ወላይታ ድቻ የስንብት ውሳኔውን ተከትሎ በአዲሱ የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ያሰናበተ የመጀርያው የፕሪምየር ሊግ ቡድን ሆኗል።

ከአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ጋር የተለያየው ወላይታ ድቻ አዲስ ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር በዛሬው ዕለት የቅጥር ማስታወቂያን ያወጣ ሲሆን የትኛው አሰልጣኝ በመስፈርቱ መሠረት ለተከታታይ ሦስት ቀናት መወዳደር እንደሚችል በማስታቀወቂያው ተገልጿል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ