ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሲዳማ ቡና

የጅማ እና ሲዳማን ጨዋታ የተመለከተውን ዳሰሳችንን በአዲሶቹ አሰልጣኞች ሀሳብ ላይ ተመርኩዘን እንደሚከተለው እናስነብባችኋለን።

በከተማቸው ከነበረው የሊጉ ቆይታ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ያልተሳካላቸው ጅማዎች በአዲስ አሰልጣኝ ስር የባህ ዳር ጨዋታቸውን ይጀምራሉ። ከአሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ጋር ከተለያዩ በኋላ በምክትላቸው የሱፍ ዓሉ እየተመሩ የቆዩት ጅማዎች በዕረፍቱ ቀናት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን መሾማቸው ይታወሳል። ቡድኑ ከሰኞ ጀምሮ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ስር ልምምዶችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ካለበት የውጤት ማጣት አንፃር በምን ዓይነት የጨዋታ አቀራረብ እና የተጨዋቾች ምርጫ ወደ ሜዳ የመለሳል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል።

ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ ከአዲሱ አሰልጣኝ ጋር ባደረገችው ቆይታ አጭር የልምምድ ጊዜን በማሳለፋቸው እና ቡድናቸውን በፉክክር ጨዋታዎች ለመመልከት ዕድሉ ስላልነበራቸው የተጋነነ ለውጥ ሳያደርጉ እንደሚቀርቡ ለመረዳት ችላለች። ባለፉት ቀናት በነበሩት የቡድኑ ልምምዶች ላይም በአካል ብቃት እና በሥነ-ልቦናው ረገድ መሻሻሎችን ለማምጣት ጥረት ሲያደርጉ መክረማቸውን አሰልጣኝ ፀጋዬ ገልፀውልናል። ከዚህም በመነሳት ውጤቱም ለጅማ እጅግ አስፈላጊው ከመሆኑ አንፃር በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ እንደሚኖራቸው የገለፁት አሰልጣኙ በጉዳት ምክንያት የቤካም አብደላ ፣ ቡዙአየሁ እንዳሻው እና ሀብታሙ ንጉሴ ለጨዋታው መድረስ አጠራጣሪ መሆን እክል ሊሆንባቸው እንደሚችልም አልሸሸጉም።

ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ተጠግተው ያሉት ሲዳማ ቡናዎች ወጣ ገባ አቋማቸው በኢትዮጵያ ቡና የ 5-0 ሽንፈት ከተደመደመ በኋላ በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው ጅማ ጋር ይገናኛሉ። እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ለውጤችን ያደረጉት ሲዳማዎች አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን አሰናብተው የሁለት ጊዜ ቻምፒዮኑን አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌን ካመጡ በኋላ የመጀመሪያውን ጨዋታ ነው የሚያደርጉት።

አሰልጣኝ ገብረመድህን እንደ ጅማው አቻቸው ሁሉ አራት የልምምድ ቀናትን ብቻ በማሳለፍ ነው ለጨዋታው የሚደርሱት። አሰልጣኙ በተለይም ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከጊዜው ማጠር አንፃር የቡድኑ አጨዋወት ላይ ለውጥ ለማድረግ ባያስቡም የተጨዋቾች ቅያሪ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። የመጨረሻውን የቡድኑን ጨዋታ በቪዲዮ የመገምገም ዕድል የነበራቸው አዲሱ የሲዳማ አለቃ ዋነኛው ትኩረታቸው የተጫዋቾችን የተነሳሽነት መጠን መጨመር ላይ እንደነበር እና በልምምድ ወቅትም እንደታዘቡት በዚህ ረገድ ለውጥ ማየታቸውን ጠቁመዋል። ከጨዋታው በፊት ለአሰልጣኙ መልካም ዜና የሆነው የግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እና ጫላ ተሺታ ከጉዳት ማገገማቸው እና ለነገ ሊደርሱ መቻላቸው ሲሆን ይገዙ ቦጋለ ብቻ ጉዳት ላይ የሚገኝ የክለቡ ተጫዋች ሆኗል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን አራት ጊዜ ተገናኝተው ጅማ አባ ጅፋር ሁለቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሁለቱን ጨዋታዎች ያለ ጎል በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። ጅማ 4፣ ሲዳማ 1 ጎል አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-4-2)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ

ሳምሶን ቆልቻ – ሱራፌል ዐወል – ንጋቱ ገብረስላሴ– ሙሉቀን ታሪኩ

ሮባ ወርቁ – ተመስገን ደረሰ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ጊት ጋትኮች – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ያስር ሙገርዋ

ጫላ ተሺታ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

© ሶከር ኢትዮጵያ