አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በትላንትናው ዕለት ኤልያስ ማሞን ያስፈረሙት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ዕለት ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።

በሁለተኛ ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጠናክረው ለመቅረብ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች የአሠልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ፊታቸውን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር አዙረዋል። በዚህም የአጥቂ አማካዩን ኤልያስ ማሞን በትላንትናው ዕለት ማስፈረማቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የቡድኑ አሠልጣኝ ዘርዓይ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ታውቋል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ሀብታሙ ወልዴ ነው። ይህ የቀድሞ የኢትዮጵያ መድን፣ መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ የአጥቂ መስመር ተጫዋች የሊጉን ሦስተኛ ደካማ አጥቂ ቡድን ለማጠናከር አዳማ ደርሷል። በዚህም የቡድኑን የአጥቂ መስመር ከአብዲሳ ጀማል ጋር በመፎካከር ለማጠናከር እንደሚጥር ይገመታል።

ሁለተኛው ለአዳማ ፊርማውን ያኖረው ተጫዋች ሚሊዮን ሰለሞን ነው። የቀድሞ የሀምበሪቾ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የመስመር ተከላካይ የነበረው ሚሊዮን የቀድሞ አሠልጣኙ ዘርዓይ ሙሉን በመከተል መዳረሻውን አዳማ አድርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ