ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አአ ከተማ ሲያሸንፍ አቃቂ ቃሊቲ ከሊጉ መውረዱ ተረጋግጧል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ ሰባተኛ ሳምንት አራተኛ ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል ተደርጎ አዲስ አበባ ከተማ 3ለ0 አሸንፏል፡፡ አቃቂ ቃሊቲም ከሊጉ መውረዱ አንድ ጨዋታ እየቀረ ተረጋግጧል።

በቀዳሚው አርባ አምስት ደቂቃ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት አቃቂ ቃሊቲዎች በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ረጃጅም ኳስ ላይ ያተኮሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ተዳክመው ታይተዋል፡፡

በጨወታው የዕለቱ ዳኛ አስናቀች ገብሬ ውሳኔዎች በሁለቱም ክለብ የቡድን አባላት ቅሬታ ሲቀርብበት የታየ ሲሆን ለረጅም ደቂቃዎች ሙከራዎች ሳይታዩት ቆይተው ከሰላሳ ደቂቃዎች በኃላ ጫን ብለው መጫወት የጀመሩት አቃቂዎች እጅጉን ለጎሉ የቀረቡ ዕድሎችን አግኝተው ሊጠቀሙ አልቻሉም። በአአ ከተማ በኩል 33ኛው ደቂቃ ያብስራ ይታይህ ከቀኝ በኩል በረጅሙ የመጣላትን ኳስ አፈትልካ ወታ ወደ ጎል ስትመታ ለጥቂት ወጥቶባታል፡፡

ጎል ለማግኘት ጥረት ያልተለው ክለቡ በሌላ ሙከራ አስናቀች ትቤሶ ከግራ የሜዳው ክፍል የተገኘን የቅጣት ምት ወደ ጎል በረጅሙ ስትልክ ዮርዳኖስ በርሄ ነፃ አቋቋም ላይ ሆና ብታገኘውም አሁንም በመጠቀሙ ረገድ ደካማ መሆናቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ የያብስራ ይታይህን የቀኝ መስመር መቆጣጠር የተሳናቸው አቃቂዎች በተጫዋቿ በሚደረጉ ጥረቶች ግብ ለማግኘት መታተራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ አንድ ደቂቃ ሲቀር ደግሞ ኪፊያ እና ዙለይካ ያደረጉት ቅብብል ቤዛዊት ጋር ደርሶ ተጫዋቿ በቀጥታ መታ የግቡ ቋሚ ነክቶ የወጣባት ሌላው አቃቂ ጫና ለመፍጠሩ ማሳዬ ነበር።

ከእረፍት በኃላ በተቃራኒው ብልጫው ወደ አዲስ አበባ ዞሯል፡፡ የመስመር ተጫዋቾቹን ድንቅነሽ እና ሰላማዊትን ወደ ፊት በደንብ በማስጠጋት ለመጫወት ጥረት ያደረጉት አዲስ አበባ ከተማዎች በተለይ መስታወት አመሎን ወደ ሜዳ ቀይረው ካስገቡ በኃላ በሶስቱ ተጫዋቾች ዕገዛ ደካማ የነበሩትን የአቃቂ ተከላካዮች በመረበሽ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል፡፡

አጀማመራቸው ባያምርም ፍፃሜያቸውን ያሳመሩት አዲስ አበባዎች 75ኛው ሰላማዊት ኃይሌ ከቀኝ በኩል በረጅሙ ስታሻማ የአቃቂ ተከላካይ ስህተት ታክሎበት ቤተልሄም አምሳሉ አስቆጥራው መሪ ሆነዋል፡፡ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ኮሪደራቸውን በአግባቡ የተጠቀሙት የሸገር እንስቶች መደበኛው ዘጠና ተጠናቆ በተጨማሪ ሦስተኛ ደቂቃ ላይ ሰላማዊት ኃይሌ አፈትልካ በግራ በኩል ፍጥነቷን ተጠቅማ ጎል አግብታ 2ለ0 ክለቡን አሸጋግራለች፡፡ የዳኛዋ ፊሽካ ሊሰማ ሽርፍራፊ ሰከንድ እየቀረው በቀኝ በኩል ከመሀል ሜዳ የተሰጣትን ድንቅነሽ በቀለ በግል ጥረቷ ወደ ሳጥን እየገፋች ገብታ ስርጉት መረብ ላይ አሳርፋ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጎ የነበረው አቃቂ ቃሊቲ ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን መውረዱ ተረጋግጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ