የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግምገማ ተካሄደ

በሦስት ከተሞች ለአስራ ስድስት ሳምንታት የተደረገው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዛሬው ዕለት ተገምግሟል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚካሄደው የዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ላይ ጅማሮውን በማድረግ በጅማ አቆራርጦ ባህር ዳር ላይ አስራ ስድስት የጨዋታ ሳምንታትን አከናውኗል። በብዙ መልክ ለየት ያለውን የዘንድሮ ዓመት ውድድርንም አክሲዮን ማኅበሩ የተሳታፊ ክለብ ስራ አስኪያጆች፣ አሠልጣኞች እና የቡድን መሪዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ገምግሟል። ከረፋድ ጀምሮ በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በተደረገው ግምገማም የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሠብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል። መርሐ-ግብሩም በመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር 3:20 ላይ በይፋ ጀምሯል።

“ዛሬ የተገኘነው በ16 ሳምንታት የታዩ መልካም ነገሮችን እንዲሁም መታረም ያለባቸው ጉዳዮችን ለመገምገም እና ውይይት ለማድረግ ነው። በዋናነትም ውይይታችን በቀጣይ በሁለት ከተማ ለሚደረገው ውድድርም ግብዓት ይሰጣል ብለን እናስባለን።” የሚል ሀሳባቸውን ካሰሙ በኋላ በቀጣይ በድሬዳዋ እና ሀዋሳ በሚደረገው ውድድር ላይ ክለቦች በኮቪድ-19 ፕሮቶሎል ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

“መንግስት እንዳስታወቀው በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡት ከተሞች ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ናቸው። ስለዚህ ክለቦች በከተሞቹ ለሻይ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ተጫዋቾችን በቀላሉ መልቀቅ የለባችሁም። እኛ በኮቪድ-19 ምክንያት ውድድሩ እንዲቋረጥ አንፈልግም። ስለዚህ ክለቦች ይህንን አውቃቸሁ እንድትንቀሳቀሱ አሳስባለሁ።”

ከቦርድ ሰብሳቢው ንግግር በኋላ በቦታው በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በተቋማቸው እይታ ሊጉ የተደረገበትን መንገድ እንደሚከተለው ገልፀዋል።

“በመጀመሪያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ ለማድረግ በመቻላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግምገማ መሠረት የሊጉ አፈፃፀም መልካም ነው። እንደውም አክሲዮን ማኅበሩ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ይመስል ነበር። ይህ እንዲሳካ ላደረጋችሁ ክለቦች ደግም ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። እንዳልኩት መልካም ጎኖች ይበዛሉ። ግን የተወሰኑ ክፍተቶችም ስለማይጠፉ እነሱ ላይ መስራት ያስፈልጋል። በተለይ ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየም ስታስገቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ። በተጨማሪም የኮቪድ-19 ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት አለባችሁ። ከፌዴሬሽኑ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ነገር የዳኝነት ችግር ነው። ይህ የሚቀረፍ ጉዳይ ነው። የዳኞች ኮሚቴ ጉዳዩን ያስተካክላል። ግን ክለቦች የዳኞች ኮሚቴ ላይ ያላችሁን ነገር ማስተካከል አለባችሁ። ኮሚቴው ላይ ምንም ተፅዕኖ ማድረግ የለባችሁም። በመጨረሻም ብሔራዊ ቡድን የክለቦች ውድድር ነፀብራቅ ነው። ከዚህ ጋር አያይዤ ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ጫፍ ላይ ደርሷል። በዚህም ደግሞ ሁላችሁንም እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን ካከናወኑ በኋላ የ16 ሳምንታት ጨዋታዎችን የተመለከተ ሪፖርት አቶ ዩናስ አቅርበዋል። ግለሰቡ በሪፖርታቸው ውስጥም ውድድሩ በስኬት መጠናቀቁን የሚያጠነክሩ ምክንያቶችን በዝርዝር አስቀምጠዋል። በዋናነትም በቅድመ ውድድር የተሰሩ ዋና ዋና ስራዎችን፣ በውድድር መሐልም የተከናወኑ ፀጥታን የተመለከቱ ጉዳዮች እንዲሁም የአወዳዳሪ አካልን፣ የህክምና እና ኮቪድ፣ የውድድር አመራሮችን እና ክለቦችን የተመለከቱ ዝርዝር ነጥቦችን አንስተው በስፍራው ለተገኙ ሰዎች አብራርተዋል። ከምንም በላይ በውድድሩ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በመጠኑ ካነሱ በኋላ በውድድር ወቅት የተከሰቱ ችግሮችን አንስተዋል።

እንደ ችግር ከተነሱት ጉዳዮች መካከልም በየከተሞቹ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች በሚጫወትበት ወቅት በስታዲየም የሚገባው የተመልካች ቁጥር መብዛት ቀዳሚው ነበር። በተጨማሪም የጎል መረብ ጥራት ማነስ፣ የዳኝነት እንከኖች እና የልምምድ ሜዳዎች ውስንነት በአሉታዊነት የተነሱ ጉዳዮች ነበሩ።

አቶ ዮናስ ካቀረቡት የክፍል አንድ ሪፖርት በኋላ የመርሐ-ግብሩ ተካፋዮች ለሻይ እረፍት ወጥተዋል። ከ15 ደቂቃዎች እረፍት በኋላም የሊጉ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወገኔ ዋልተንጉስ የ16 ሳምንታት ውድድር ቁጥራዊ መረጃዎችን አቅርበዋል። አቶ ወገኔ በሪፖርታቸውም በውድድሩ የተመዘገቡ ካርዶች፣ ጎል አስቆጣሪዎችን እንዲሁም የሀገር ውስጥ እና የውጪ ተጫዋቾችን ያነፃፀሩበትን ትንተና በቁጥሮች በማስደገፍ አቅርበዋል። ግለሰቡ ሪፖርቱን ካቀረቡ በኋላ ክለቦች የቀጣይ ዓመት የቤት ስራቸውን ከአሁን ጀምሮ እንዲሰሩ አደራ ብለዋል። በዋናነትም የመወዳደሪያ ቦታዎችን በተመለከተ ክለቦች በቀጣይ ዓመት የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

መርሐ-ግብሩ ቀጥሎም ከ5:30 ጀምሮ በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች እንዲነሱ መድረኩ ለተሳታፊያን ክፍት ሆኗል። መድረኩንም የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ መርተዋል። በተሰጠው ዕድል መሠረትም በስፍራው የነበሩ የክለብ ሥራ አስኪያጆች፣ የቡድን መሪዎች እና አሠልጣኞች የተለያዩ ሀሳቦችን ወደ መድረኩ ሰንዝረዋል። በዋናነትም የዘንድሮ የውድድር ቅርፅ በቀጣይ ዓመት ይቀጥል፣ የዳኝነት ችግሮች ይስተካከሉ፣ የተቀያሪ ተጫዋቾች ቁጥር ይጨምር፣ ጨዋታዎች ወደ ምሽት ይገፉ፣ ለቀጣይ ውድድሮች የልምምድ ሜዳዎች ይመቻቹ፣ ቴክኒካል ሪፖርቶች ለአሠልጣኞች ይሰጡ እንዲሁም የወራጆችን እና የትግራይ ክለቦችን የተመለከቱ ሀሳቦች ተጠቃሽ ናቸው።

ለተነሱት አንኳር ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም ተከታዮቹ ምላሾች ተሰጥተዋል።

“የጨዋታዎቹን መርሐ-ግብሮች ለማውጣት መሠረታችን ዲኤስ ቲቪ ነው። ዲኤስ ቲቪ ያመጣልንን ነገር ደግሞ ለመጠቀም እነሱ የሚያስተላልፉበትን ሰዓት ማየር አለብን። በተለይ የቅዳሜ እና የእሁድ አማራጮች በጣም ጠባብ ናቸው። እነሱ እንደውም ቅዳሜ እና እሁድ 5 እና 8 ሰዓት እንዲሆን ጠይቀውናል። እኛ ግን ይህ አይሆንም ብለን እየተነጋገርን ነው። የጨዋታ ሰዓቶቹ ወደ ማታ እንዳይገፉ ደግሞ መታየት ያለባቸው ነገሮች አሉ። እርግጥ ድሬዳዋ ጥሩ የሆኑ ፖውዛዎች ተክላለች። እኛም ሄደን እንዳየነው ለዐይን በቂ የሆነ ብርሃን ምሽት ላይ በስታዲየም አለ። ግን ጨዋታዎቹን በምሽት ለማስተላለፍ የካሜራዎቹ የብርሃን መጠን ፍለጋ መታየት አለበት። ለሰው ዐይን በቂ ነው ብንልም በካሜራስ ዐይን የሚለው መፈተሽ አለበት። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ሳምንት የምንደርስበት ነገር ይኖራል።” አቶ ወገኔ

“የቅያሪ ተጫዋቾች ቁጥር ለምን እና በምን መልኩ ይሆናል የሚለው መታየት አለበት። ጉዳዩም ከቡድን ስብስብ ጥልቀት እና ከሰዓት ማባከን ጋር ልያያዝ ይችላል።” አቶ ዮናስ

“ዳኖች ስለበዙ የጥራት ችግር አለ። መሠረታዊ ስህተቶችንም የሚሳሳቱ ዳኞች አሉ። ይህ ደግሞ በትልቅ ሊግ ደረጃ መታየት የለበትም። ይህ ደግሞ እንዳልኩት ከጥራቱ ይልቅ ብዛቱ ላይ ስላመዘንን የመጣ ይመስለኛል። እኛም ይህንን ለማስተካከል እንጥራለን። ዋናው ነገር ማስተማር ነው። የትም ሀገር ብትሄዱ የማይሳሳት ዳኛ የለም። ተመልካች በሌለበት የሚሳሳት ዳኛ ግን የጤና አይደለም። ስለዚህ ወደፊት የዳኞቻችን ጥራት ላይ እንሰራለን።” አቶ ልዑልሠገድ

“የዘንድሮውን ውድድር በስድስት ከተሞች ለማድረግ ነበር ያሰብነው። ግን በምታውቁት ምክንያት መቐለ ላይ ውድድር ማድረግ አልቻልንም። ከድሬዳዋ ቀጥሎ ሊጉ የሚከናወነው ሀዋሳ ላይ ነወ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሀዋሳ ለግምገማ የሄደው ልዑክ ውስጥ እኔ ነበርኩ። ዋናው የሀዋሳ ስታዲየም ገና ስላላለቀ ውድድሩ እንዲካሄድ ያሰብነው የዩኒቨርስቲው ስታዲየም ላይ ነው። ይህ ቢሆንም ግን በከተማዋ የሚስተካከሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ይህንንም ወደፊት እንዲስተካከል እያደረግን እንሄዳለን።

“የትግራይ ክለቦችን ጉዳይ አሁን ላይ ለመመርመር ዝግጁ አይደለንም። ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ቢኖር ሁሉም ክለብ ለሻምፒዮናነት እና ላለመውረድ ይጫወት። ስለዚህ የትኛውም ክለብ መውረድ ካጋጠመው ይወርዳል።” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ


© ሶከር ኢትዮጵያ