ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አርባምንጭ እና ድሬዳዋ በድል የውድድር ዓመቱን አጠናቀዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ አርባምንጭ ከተማ አቃቂ ቃሊቲን፤ ድሬዳዋ ከተማ ጌዲኦ ዲላን አሸንፈዋል።

3፡00 ላይ ግርጌ ላይ የሚገኙት አቃቂ ቃሊቲ እና አርባምንጭ ከተማ የተገናኙበት ጨዋታ ቀዳሚው መርሀግብር ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት መውረዱን ያረጋገጠው አቃቂ ቃሊቲ እንዲሁም ላለመውረድ እየታገለ ያለው አርባምንጭ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ብርቱ የሆነ ፉክክርን ያሳዩበት እንደነበር በሜዳ ላይ ቡድኖቹ ያሳዩት እንቅስቃሴን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ኳስን መሠረት ባደረገ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማሳየት አቃቂዎች ሻል ቢሉም መልሶ ማጥቃትን መሠረት አድርገው የተንቀሳቀሱት አርባምንጭ ከተማዎች የአቃቂን የመከላከል ድክመት በአግባቡ በመጠቀሙ ረገድ ተሳክቶላቸዋል፡፡ 14ኛው ደቂቃ ላይ ድርሻዬ መንዛ ከግራ ወደ ቀኝ የጣለችላትን ኳስ መሠረት ማቲዮስ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኗን ቀዳሚ ስታደርግ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሰርካለም ባሳ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ከመስመር በኩል ስትሰጣት ድርሻዬ መንዛ ከመረብ አዋህዳ የአርባምንጭን የጎል መጠን ወደ ሁለት አሳድጋለች፡፡ 35ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ስንዱ ዳምጠው ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር የግብ መጠኑን አሳድጋለች፡፡

39ኛው ደቂቃ የአቃቂው አሰልጣኝ ጥበቡ ወርቁ በተደጋጋሚ ዳኛ እየበደለኝ ነው በማለት ከአራተኛ ዳኛዋ ጋር በፈጠሩት ዕሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ግን አራተኛ ዳኛዋ ማዕረግ ጌታቸውን እጆግ በሚገርም ትዕትና ይቅርታ ሲጠይቅ አስተውለናል፡፡

የዕረፍት መውጫ ደቂቃዎች ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረትን ያደረጉት አቃቂዎች በጭማሪ ደቂቃ ቤዛዊት ንጉሤ በግንባር ገጭታ ባስቆጠረችው ጎል ልዩነቱን አጥብበው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከመጀመርያው ጋር ተመሳሳይ መልክ በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በተደጋጋሚ በረጃጅም ኳስ ለአጥቂዎቻቸው በማድረስ ጥቃት ሲሰነዝሩ የነበሩት አርባምንጮች 62ኛው ደቂቃ በሰርካለም ባሳ አራተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኃላ ድርሻዬ መንዛ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አምስተኛ ጎልን ከመረብ አሳርፋለች፡፡

የቀሩትን የመጨረሻ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ጫናን ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት አቃቂዎች በቤዛዊት ንጉሤ ጎል ልዩነቱን ቢያጠቡም ተጨማኪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በአርባምንጭ 5ለ2 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ጨዋታውን ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማም ነጥቡን አስራ አምስት ያደረሰ ሲሆን በሊጉ ለመቆየት ዛሬ ከሰአት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ያለው አዳማ ከተማ መሸነፍን ይጠባበቃል፡፡

በመቀጠል 5፡10 ላይ የተገናኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ናቸው፡፡ ከወገብ በታች ሆኖ ላለመጨረስ ተቀራራቢ ነጥብ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች አንፃራዊ የሆነ ብልጫን በተጋጣሚያቸው ላይ አሳይተዋል፡፡ ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ትንቢት ሳሙኤል ጎል ብታስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራባታለች፡፡ በድሬዳዋ የሙከራ ብልጫ የተወሰደባቸው ጌዲኦ ዲላዎች መሀል ሜዳው ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴን በማድረግ ወደ አጥቂዎቹ ሲልኩ ቢታዩም ወደ ድሬዳዋ ግብ ክልል ሲደርሱ የአጠቃቀም ስህተት ይታይባቸው ስለነበር ጎል ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡

ወደ መስመር አዘንብለው በይበልጥ በፀጋነሽ ወራና ላይ አብዛኛዎቹን የማጥቃት አማራጫቸውን ያደረጉት ድሬዳዋዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋነሽ ወራና ከሳጥን ውጪ አክርራ መታ ግብ ጠባቂዋ መስከረም መንግስቱ እንደምንም አድናባታለች፡፡ሰላማዊት ጎሳዬ ሁለት ጊዜ አግኝታ ካመከነቻቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ውጪ የጠራ አጋጣሚን ለመፍጠር የተቸገሩት ጌዲኦ ዲላዎች እንደ ድሬዳዋ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢሆን ገና በጊዜ ግብ በተቆጠረባቸው ነበር፡፡

ፀጋነሽ ወራና፣ ትንቢት ሳሙኤል እና ቁምነገር ቡድናቸውን መሪ ለማድረግ ጥረትን አድርገዋል፡፡ በተለይ 25ኛው ደቂቃ ትንቢት አሾልካ ሰጥታ ቁምነገር አንድ ለአንድ ብትገናኝም በጨዋታው በርካታ የድሬዳዋን ኳሶችን ስታመክን ከጅምሩ ጀምሮ የነበረችው መስከረም መንግስቱ በግሩም ሁኔታ አድናባታለች፡፡

38ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱ ዋና ዳኛ አስናቀች ገብሬ የሰጠችውን አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት ልዩነት ፈጣሪ ሆና የዋለችሁ ፀጋነሽ ወራና ከመረብ አዋህዳው ክለቧን መሪ አድርጋለች፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኃላ በመልሶ ማጥቃት ቱሪስት ለማ ዲላን አቻ አደረገች ተብሎ ሲጠበቅ በማይታመን መልኩ ስታዋለች፡፡

ከእረፍት መልስ ጌዲኦ ዲላዎች የተጫዋች ለውጥ ካደረጉ በኃላ በመጀመሪያው አጋማሽ የተንፀባረቀባቸውን ክፍተት በሚገባ አሻሽለው የቀረቡ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ መከላከሉ አመዝነው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሙከራን አድርገዋል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ አምበል ሀሳቤ ሙሶ በሳጥን ውስጥ በእጅ ኳስ በመንካቷ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት እፀገነት ግርማ ብትመታውም አበባየው ጣሰው መልሳባታለች፡፡

ዲላዎች ብልጫን ወስደው ጎል ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም በመከላከሉ አስጠብቀው ለመውጣት የሞከሩት ድሬዳዋዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታው 1ለ0 አሸንፈው በመውጣት አምስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ፈፅመዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ