ለሁለት ዓመታት ያልተከናወነው ውድድር ዳግም ሊመለስ ነው

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ2010 በኋላ ያልተደረገውን ውድድር በሐምሌ ወር ዳግም እንደሚጀምር ገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ16 ሳምንታት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ግምገማ በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል እያከናወነ ይገኛል። የሥነ-ስርዓቱ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በሀምሌ ወር ፌዴሬሽናቸው ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የታዳጊዎች የውድድር ዳግም ለመጀመር እንዳለመ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቱ የመክፈቻ ንግግራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት በመጪው ሀምሌ ወር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከ17 ዓመት በታች ውድድር እንደሚጀመር ተናግረዋል። በዚህም በአስራ ሁለቱም ክልሎች የሚገኙ እና በፕሪምየር ሊጉ ላይ የሚወዳደሩ አስራ ሦስቱም ክለቦች በግዴታ ክለብ እንዲይዙ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ክለቦች በትክክለኛው የእድሜ እርከን ተጫዋቾችን እንዲያዋቅሩ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የበላይነት የሚደረገው ይህ ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ 2010 ላይ መደረጉ ይታወሳል። በወቅቱ ባቱ ላይ የተደረገውን ውድድርንም ሀዋሳ ከተማ በአሸናፊነት ማገባደዱ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ