“የዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለት ስልጠናዎች ለባለሙያዎች ይሰጣሉ”

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሁለት ስልጠናዎችን ሊሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በዛሬው ዕለት የ16 ሳምንታት የሊጉን ውድድር ከተሳታፊ ክለቦች ጋር በመሆን ገምግሟል። በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በተከናወነው የግምገማ እና የውይይት መርሐ-ግብር ላይም የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ተቋማቸው የዘንድሮውን ውድድር ላገባደደ በኋላ ሁለት ስልጠናዎችን ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።

“የዘንድሮ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለት ስልጠናዎች ለሀገራችን ባለሙያዎች እንዲሰጡ ለማድረግ እየሰራን ነው። በዚህም ለሁለቱም ፕሮግራሞች የሚያስፈልገውን በጀት መልቲቾይዝ እንዲለቅልን እየተነጋገርን ነው።

“አንደኛው ስልጠና ኮች ዘ ኮችስ( Coach the Coaches) የሚል ነው። ይህም በዋናው ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚያሰለጥኑ አሠልጣኞችን ብቻ የሚያካትት ሳይሆን በታችኞቹም ሊጎች የሚያሰለጥኑ አሠልጣኞችን እንዲያቅፍ እናደርጋለን። ስልጠናዎቹ እውቅና ስላላቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል እንዲሰጡ እናደርጋለን። እንዲታወቅ የምንፈልገው ይህ ስልጠና ካፍ ከሚሰጠው የስልጠና ፕሮግራም ተጨማሪ ነው። ስለዚህ ይህንን ፕሮግራም ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲሰጥ እናደርጋለን።

“ሁለተኛው የዳኞች የማነቃቂያ ስልጠና ነው። እንደምታቁት በሀገራችን በጣም ጎበዝ የዳኝነት ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች አሉ። ስለዚህ የሌሎቹን ዳኞች ብቃት ለማሳደግ በሀገራችን ባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጥ እናደርጋለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ